>
7:45 am - Wednesday December 7, 2022

በፍትህ ቀን፤ በግፍ ታስረው በእስር እየተሰቃዩ ላሉ ዜጎች ፍትህ እንጠይቃለን!  (ያሬድ ሀይለማርያም)

በፍትህ ቀን፤ በግፍ ታስረው በእስር እየተሰቃዩ ላሉ ዜጎች ፍትህ እንጠይቃለን! 
ያሬድ ሀይለማርያም
ሕውሃት ያሰረውን ፈቶ እና ማዕከላዊን ዘግቶ በአዳዲስ የፖለቲከኛ እና የህሊና እስረኛ አዳዲስ እና ነባር ማጎሪያዎችን በግፍ በታሰሩ እና አስከፊ የእስር ሁኔታ ውስጥ ባሉ እስረኞች ሞልቶ ስለ ፍትህ ማውራት አይቻልም!!!
መንግስት እያንዳንዱን የጳጉሜን ቀናት የፍትህ፣ የሰላም፣ የኩራት፣ የፍቅር እያለ ቀናቶቹን ስያሜ ሰጥቶ እያከበረ ይገኛል። ሃሳብና ተግባር ከተገናኙ ይህ አይነቱ ብሔራዊ ንቅናቄ ይበል የሚያሰኝ ነው። ችግሩ የምንመኘው እና መሬት ላይ ያለው እውነታ የሚቃረን ሲሆን ግን ይህ አይነቱ ጥሪ ከፖለቲካ ፍጆታ የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም። የፍትህ ቀንን ምክንያት በማድረግ መንግስት የዘጋውን የዜጎች ማሰቃያ የነበረውን ስፍራ፤ ማዕከላዊን ለጎብኚዎች ክፍት አድርገው ሲያስጎበኙ በመገናኛ ብዙሃን አይተናል። ይህ በራሱ ትልቅ እርምጃ ቢሆንም የፍትህ መረጋገጥን ግን አያሳይም። ዛሬም ዜጎች ያለ በቂ ማስረጃ በፖሊስ እየተያዙ በፖሊስ ጣቢያዎች እና በማሰልጠኛና ወታደራዊ ካንፖች ውስጥ ታስረው እየማቀቁ እንደሆነ ማስረጃዎች በበቂ ሁኔታ ያሳያሉ።
+ ቁጥራቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከኦሮሚያ እና ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ተይዘው በሰንቀሌ ፖሊስ ማሰልጠኛ እና በጦላይ ወታደራዊ ማሰልጠና ካምፕ ታጉረው ለወራት ያህል ያለ ምንም የፍትህ ሂደት እየማቀቁ ይገኛሉ። ከእነዚህ እስረኞች መካከል አብዛኛዎቹ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ አባላት መሆናቸውን ፓርቲው ትላንት ለኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በላከው ደብዳቤ ላይ ገልጿል።
+ በቅርቡ በባህርዳር እና በአዲስ አበባ የተከሰተውን የባለሥልጣናት ግድያ ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንዲሁ ያለ ምንም በቂ ማስረጃ በአማራ ክልል፣ በአዲስ አበባ እና በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ውስጥ ታስረው በአስከፊ የእስር ሁኔታ ውስጥ እየማቀቁ እንደሚገኙ ከቤተሰቦቻቸው እና ከሌሎች ምንጮች የሚወጡ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ። በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽ ውስጥ ብቻ ከዘጠና በላይ የሚሆኑ የአማራ ተወላጆች ታስረው ለእንግልት እየተዳረጉ ይገኛሉ።
+ ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩን ጨምሮ፤ ሁለት የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኞች፣ የሲዳማ ሚዲያ ጋዜጠኞች፣ የባልደራስ ምክር ቤት አባላት እና ሌሎች በአደባባይ ሃሳባቸውን በመግለጽ የሚታወቁ ግለሰቦች በተመሳሳይ የእስር ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።
+ የኦፌኮ አባላትን ጨምሮ በርካታ የአብን አባላትም እንዲሁ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ታስረው እየተጉላሉ መሆኑን ድርጅቶቹ ጭምር በተደጋጋሚ ሲገልጹ ተሰምቷል። ምርጫ በሚታሰብበት በዚህ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ያነጣጠረ እስር ሂደቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ይወስደዋል።
ከላይ የተጠቀሱትን እስረኞች ጉዳይ በተመለከተ መንግስት ሁለት አስከፊ የሆኑ የፖለቲካ  ውሳኔ ስህተት እና የሕግ ጥሰት ፈጽሟል።
፩ኛ. ዜጎችን በገፍ አፍሶ በወታደራዊ ካምፖች ውስጥ የማጎር እርምጃ ቀደም ሲል በህውሃት ዘመን በተለይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀባቸው ወቅቶች ተደጋግሞ ይፈጸም የነበረ ከፍተኛ የመብት ጥሰት ነው። መንግስት ዜጎችን አርማላሁ፣ አስተምራለሁ በሚል ሽፋን ያለ ምንም የፍትህ ሂደት በወታደራዊ ካምፖች ውስጥ ማጎር ከየት ያገኘው ስልጣን እንደሆነ አይታወቅም። አላማው ዜጎን ማነጽም ሊሆን አይችልም። ማንም ሰው ወንጀል ከሰራ በአግባቡ ታስሮ እና ሕግ ፊት ቀርቦ ጉዳዩ በገለልተኛ ፍርድቤት እንዲታይ የማድረግ ኃላፊነት መንግስት በሕገ መንግስቱ እና በአለም አቀፍ ድንጋጌዎች ተጥሎበታል። ይህ ወደ ጎን በመተው እየተደረገ ያለው ሕገ ወጥ እርምጃ ቀጣይ አፈና እንጂ ሥርዓት ማስከበር ሊሆን አይችልም።
፪ኛ. ሁለተኛው እና ከባዱ ስህተት ደግሞ ከላይ የተጠቀሱትን ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮችን እንዲሁም የባልደራስ አባላት ላይ በጸረ ሽብር ሕጉ መሰረት ክስ ሊመሰርትባቸ መዘጋጀቱ ጉዳይ ግልጽ የፖለቲካ አፈና መሆኑን ያሳያል። ሲተች እና ሲወገዝ በነበረ ሕግ ዜጎችን በተለይም ሃሳባቸውን በአደባባይ ሲገልጹ እና ሰላማዊ ትግልን ሲሰብኩ የቆዩ ሰዎችን ሽብርተኛ ብሎ መክሰስ ኦዴፓ ከህውሃት ሥልጣኑን ከነአፈና በትሩ የተረከበ መሆኑን ነው የሚያሳየው።
በጦር ካምፕም ሆነ በተለያዩ ማጎሪያዎች ውስጥ ያለ አግባቡ ታስረው እየማቀቁ ያሉትን ዜጎች በአስቸኳይ በመፍታት የፍትህን ቀን ብታከብሩ ሃሳባችው የሰመረ ይሆናል። ሕውሃት ያሰረውን ፈቶ እና ማዕከላዊን ዘግቶ በአዳዲስ የፖለቲከኛ እና የህሊና እስረኛ አዳዲስ እና ነባር ማጎሪያዎችን በግፍ በታሰሩ እና አስከፊ የእስር ሁኔታ ውስጥ ባሉ እስረኞች ሞልቶ ስለ ፍትህ ማውራት አይቻልም። ወንጀል በአደባባይ የፈጸሙ ሰዎች በየሜዳው እንደልባቸው እየትንጎማለሉ ንጹሃን ዜጎችን በገፍ እያሰሩ የሕግ የበላይነትንም ማስፈን አይቻልም።
በግፍ የታሰሩ ሰዎች በአፋጣኝ ይፈቱ!
Filed in: Amharic