>
9:48 am - Tuesday July 5, 2022

ዐብይ አህመድ፡ ያንዳርጋቸው ፍራንከንስቲን (መስፍን አረጋ)

ዐብይ አህመድ፡ ያንዳርጋቸው ፍራንከንስቲን

 

ያሳደኩት ውሻ ጃስ ብየው ነክሶ
ደሙ ጣመውና ሲጨርስ ላልሶ
እኔኑ ነከሰኝ ዙሮ ተመልሶ፡፡

መስፍን አረጋ

የኦነጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦቦ ዐብይ አህመድ በወያኔ የስለላ ድርጅት ውስጥ ይሠራ በነበረበት ጊዜ ክሌወኪል (double agent) በመሆን ለግንቦት ሰባትም ይሰልል እንደነበር መረጃወች እየወጡ ነው፡፡ ነገሮቸን በጥሞና ሳሰላስላቸው ደግሞ ዐብይ አህመድ የገንቦት ሰባት ሰላይ ብቻ ሳይሆን በግንቦት ሰባት (በተለይም ደግሞ ባንዳርጋቸው) ተፈጥሮ፣ ከግንቦት ሰባት ቁጥጥር ውጭ በመውጣት ራሱን ግንቦት ሰባትን እየበላ የሚገኝ የግንቦት ሰባት (በተለይም ደግሞ ያንዳርጋቸው) ፍራንከንስቲን (frankenstein) ይመስለኛል፡፡

ዐብይ አህመድን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ያበቃው ብአዴን (በተለይም ደግሞ ደመቀ መኮንን) ነው፡፡ የጊዜውን ብአዴን ደግሞ ግንቦት ሰባት ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮት እንደነበር  ያደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ስለዚህም ብአዴን ዐብይ አህመድን እንዲመርጥ ያግባባውና ያሳመነው ግንቦት ሰባት የመሆኑ እድል በጣም ከፍተኛ ነው፡፡

ግንቦት ሰባት ዐብይ አህመድን ፈጥሮት ከሆነ፣ የፈጠረው ዐብይ አህመድን ተጠቅሞ ስልጣን ከያዘ በኋላ ዐብይ አህመድን ለማስወገድ ብቻና ብቻ ነው፡፡ በዚህ እሳቤ መሠረት ዐብይ አህመድ የባሕር ዳሩን ጭፍጨፋ በፍጥነት ካላከናወነ ለስልጣኑ ክፉኛ እንደሚያሰጋው በምክር መልክ ያስፈራራው አንዳርጋቸው ባይሆን እንጅ ቢሆን አያስገርምም፡፡

ዐብይ አህመድ የሚጓዝበትን ፍኖትካርታ (roadmap) ያዘጋጀው እሱ ራሱ መሆኑን አቶ አንዳርጋቸው ባንደበቱ ነግሮናል፡፡ አንዳርጋቸው ደግሞ ፍኖትካርታ የሚያዘጋጀው በስተመጨረሻ የራሱን ድርጅት ግንቦት ሰባትን (ይልቁንም ደግሞ እሱን ራሱን) ለስልጣን ለማብቃት እንጅ ለዐብይ አህመድ አስቦ አይደለም፣ ፖለቲከኛ ለኔ እንጅ ለሱ አያውቅምና፡፡

የአንዳርጋቸው ኢዜማ በትረ ስልጣን ለመጨበጥ ያቀደው በዜግነት ፖለቲካ ነው፣ ያለው አማራጭ ይሄውና ይሄው ብቻ ነውና፡፡ ከጦቢያ ትላልቅ ብሔረሰቦች ውስጥ ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በዜግነት ፖለቲካ የሚያምነው ደግሞ አማራ ብቻ ነው፡፡ ያማራ ሕዝብ ደግሞ የኦሮሞንና የትግሬን ሕዝብ ድምር የሚበልጥ የጦቢያ ብዙሃን ሕዝብ እንደሆነ አንዳርጋቸው አሳምሮ ያውቃል፡፡ ስለዚህም ኢዜማ በዜግነት አጀንዳ ስልጣን ለመያዝ የሚያስፈልገው ያብዛኛውን አማራ ድምጽ ማግኘት ብቻ ነው፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እስካለ ድረስ ግን ግንቦት ሰባት/ኢዜማ ያማራውን አብላጫ ድምጽ እንደማያገኝ (ስለዚህም ስልጣን እንዳማረው እንደሚቀር) ባሕርዳር ለመሰብሰብ ሂዶ ተንከሳክሶ ከተመለሰ በኋላ ቁርጡን አውቆታል፡፡

ስለዚህም ኢዜማ ስልጣን ይይዝ ዘንድ በከፍተኛ ፍጥነት ያቆጠቆጠው ያማራ ብሔርተኝነት በዘመቻ ቁንጸላ ባጭሩ መቀጠፍ ወይም መቀጨት ነበረበት፡፡ ይህ ማለት ደግሞ እነ አሳምነውን ባሕርዳር ላይ የረሸነው፣ አብንን የሚያዳክመው፣ ባልደራስን የሚያዋክበው፣ አስራት ሚዲያን የሚያፍነው ዐብይ አህመድ ቢሆንም፣ ምክረ ሐሳቡን ለግሶት፣ ዘዴውን ዘይዶለት አይዞህ የሚለው ግን ፍኖትካርታውን ካዘጋጀለት ካንዳርጋቸው ውጭ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም፡፡

ከባሕርዳር ጭፍጨፋ ማግስት ግን ዐብይ አህመድ ገነነና ገንቦት ሰባትን (አንዳርጋቸውን) ከማይፈልግበት ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ በዚያች መከረኛ ዕለት በኋላ ግንቦት ሰባት ለዐብይ አህመድ ረዳት መሆኑ ቀርቶ ሸክም ሆነበት፡፡ ግንቦት ሰባት ፖለቲካዊ ባላንጣወቸን በዐብይ አህመድ አስበልቸ ዐብይ አህመድን እበላዋለሁ ሲል፣ ዐብይ አህመድ ከተጽኦኖው ወጣና ራሱን ግንቦት ሰባትን ይበላው ጀመር፡፡ ዶ/ር ሰናይ ልኬ ፓለቲካዊ ባላንጣወቸን በኮለኔል መንግሥቱ አስበልቸ ኮለኔሉን አበላለሁ ሲል እሱ ራሱ ተበላ፡፡ የአቶ አንዳርጋቸውም እጣ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ‹‹ያማራ ሕዝብ ትግል ከየት ወደየት›› የሚል መጽሐፍ እንዳልጻፈ ሁሉ፣ አማራ የሚባል የለም፣ እኔም አማራ አይደለሁም ቢል ራሱን ይበልጥ ያስንቃል እንጅ ከመበላት (ከፖለቲካዊ ጨዋታ ሙሉ በሙሉ ከመወገድ) አይድንም፡፡

መስፍን አረጋ  Email:  mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic