>

መኩራቱንስ እንኩራ፤ ግን በምናችን?!? (ያሬድ ሀይለማርያም)

መኩራቱንስ እንኩራ፤ ግን በምናችን?!?
ያሬድ ሀይለማርያም
ዛሬ በአገራችን የኩራት ቀን እየተከበረ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመስቀል አደባባይ በኩራት ባዕሉን እያከበሩ መሆኑን የመንግስት መገናኛዎች ገልጸዋል። እሰየው ነው እንኩራ። ነገር ግን አንድ ጥያቄ አለኝ፤ የምን ኩራት? በምን ኩራት?
በዘር ተቧድነን፣ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን አርክሰን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን ከቄያቸው አፈናቅለን፣ በመቶ ሺ ዜጎች በየጎዳናው ላይ አፍሠን፣ ሌሎች ሺዎችን ለአረብ አገር ባርነት ዳርገን፣ ንጹሃን ዜጎችን በየማጎሪያው አጉረን፣ እርዳታ የሚፈልጉ ሚሊዮን እርሃብተኞችን ጉያችን ታቅፈን፣ አውርተን መግባባት አቅቶን በልዩነት ግንብ ታጥረን፣ አገራይ ራዕይ ሳይኖረን በመንደር ቅዠት ተጠልፈን፣ ያስረከቡንን ትልቅ አገር ቁርስራሽ ልናደርግ በክልል ተካለን፣ የአገር ባለውለታ ጀግኖችን በጎለደፈ አፋችን አንቋሸን፣ በባንዲራ አንስማማ፣ በቋንቋ አንስማማ፣ በአገር አንድነት አንስማማ፣ በኃይማኖት አንስማማ፣ በታሪካችን አንስማማም፣ ላለመስማማት ተማምለን፣ በፍርሃት ቆፈን ተሸብበን ለገዢዎች እያረገድን ከህሊናችን ተጣልተን፤ የምን ኩራት?
የኩራታችን ነገር አንድ በቅርቡ ያነበብኩትን በUniversity of California የተደረገ ጥናት አስታወሰኝ። ጥናቱ ኩራት ላይ ያተኮረ ሲሆን ሁለት አይነት ኩራት አለ ይላል።
+ Authentic pride: When a person feels authentic pride, he or she was more likely to score high on extraversion, agreeableness, genuine self-esteem and conscientiousness.
+ Hubristic pride: It is self-aggrandizing self-esteem rather than genuinely feeling really good about yourself, and it is sort of underlying insecurity to it and competitiveness.
እንግዲህ የእኛ ኩራት በራስ ሥራ ላይ የተገኘ በእውነተኛ ስኬት ላይ የተመሰረተ እርካታ ነጸብራቅ (Authentic pride) ወይስ እራስን በባዶ በመቆለል እና በውነተኛ ስኬት ላይ ያልተመሰረተ ባዶ የማስመሰያ ስኬት ወይም የተጋነነ ለራስ ያለ ምልከታ ያመነጨው ኩራት (Hubristic pride) ፍርዱን ለባለኩራት ቀኖች እተዋለሁ።
ለማንኛውም የጥናቱ አንድ ደስ የሚለው ነገር ሁለቱም ኩራቶች በማህበረሰብ ውስጥ በጎ መቀራረብን እና ጠንካራ ግንኙነትን ለመፍጠር አዎታዊ ገጽታ ያላቸው መሆኑን ይጠቁማል። ስለዚህ በየትኛውም ምክንያት እንኩራ አንከስርም። የበለጠ ለማትረፍ ግን እውነተኛ የኩራት ቀን እንዲሆን ተግተርን በጎ በጎውን እንስራ።
መልካም ሰንበት!
Filed in: Amharic