ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ አንለይ
* ኦርቶዶክስን ከብሔር ጋር አቆራኝቶ ጥላቻን ማስፋፋት!!!
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት በሀገሪቱ የነበረው ሽኩቻና ውጥረት እንዲሁም የሕዝቡ ጭንቀት ያሳሰባቸው ኢትዮጵያውያን ብዙ ነበሩ፡፡ ብዙዎች መፍትሔ የመሰላቸውን ከማድረግ ወደ ኋላ እንዳላሉ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ በወቅቱ ለመፍትሔ ይሯሯጡ ከነበሩት አካላት አንድ የሽማግሌዎች ቡድን ለመመሥረትና ባለሥልጣናትን በማናገር ወደ መግባባትና ሰላም ለማምጣት ሕብረ ብሔርና ሕብረ ሃይማትን ታሳቢ ያደረገ የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን ማሰባሰብ ይጀመራል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ከኮሚቴዎቹ ሁለቱ እገዛ እንዳደርግ ሲያወያዩኝ የነገሩኝ ሽማግሌዎችን ሲያናግሩ ከገጠማቸውና ካስገረማቸው ታሪክ አንዱ የሚከተለው ነበር፡፡
ለሽማግሌነት ከታጩት አንዱ በትውልድ የወለጋ ኦሮሞ የሆኑ በትምህርት ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸው በሃይማኖት ደግሞ የፕሮቴስታንት አንድ ቅርንጫፍ ፓስተር ናቸው፡፡ ፓስተሩ አሁንም በሕይወት ያሉ ናቸው፡፡ እኒህ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አብዛኛው የልዩነት ምንጭ ተንኮለኛ ነጮች እንደሆኑ የራሳቸውን ገጠመኝ መሠረት አድርገው ይናገራሉ፡፡ እርሳቸውና ሌሎች ሦስት የቅርብ ጓደኞቻቸው በወጣትነታቸው ወደ ፕሮቴስታንት የለወጧቸው የጀርመን ሚሺነሪዎች እንደነበሩና ዋና የስብከት መንገዳቸውም ጸረ ሴማዊነትን (አማራና ትግሬ ጥላቻን) ማዕከል ያደረገ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ፓስተሩ በወቅቱ የነበራቸውን ስሜት ሲገልጡ በተለይ ለአማራ ካሳደሩባቸው ጥላቻ የተነሣ እርሳቸው ከሦስት ጓደኞቻቸው ጋር ሆነው ሲያድጉ አየር ሃይል ገብተው ጀት አብራሪ ሆነው አማራውን በአውሮፕላን ለማርከፍከፍ ይመኙ እንደነበር ለመግለጽ በፍጹም አልተሰቀቁም ነበር፡፡ እንደ ፓስተሩ ገለጻ ከሆነ እርሳቸውን ከዚህ ስሜትና ጥላቻ ያወጧቸው በኋላ ያገኟቸው የስዊድሽ ሚሽነሪዎች ናቸው፡፡ ፓስተሩ ያንን በጥላቻና ለበቀል በተገፋፋ ስሜት ውስጥ ሆነው አንድን ብሔር ለማጥፋት የነበሩበትን ወቅት በማስታወስ ዛሬ ይጸጸታሉ፡፡ የእነዚያ ነጮችን ተንኮልና አሁንም የቀጠለውን ሥራቸውንና ሀገራቸው ኢትዮጵያ የገባችበትን ሁኔታም እያዩ ያዝናሉ፤ ተከታዮቻውንም ከዘረኝነት እንዲወጡ ይሰበካሉ፡፡
በመጀመሪያው ሥራቸው ቀላል የማይባል ቁጥር ቢያገኙም ለእነርሱ ግን የገመቱትን ያህል አልነበረም፡፡ ያም ቢሆን በእነርሱ ጥንካሬ ሳይሆን በእኛ ድክመት እንደሆነ ያውቁታል፡፡ ስለዚህም የተሻለ ዘዴ መጠቀም ነበረባቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ፓስተሩ እንዳሉት ኦርቶዶክስ ልክ ኢትዮጵያዊና የሴማውያን በማስመሰል በተለይ ጀርመኖች በሀገራቸው በጀርመን በነበራቸው የሴማውያን ጥላቻ ስድስት ሚሊዮን በላይ አይሁድን እንዳስፈጁት በኢትዮጵያም ሴማዊነት አላቸው ያሏቸውን እንዲጠሉና በተለይ ኦሮሞዎቹ ሴማዊነት እነርሱን የማይነካ በማስመሰል የልዩነት ግንቡን መገንባት ጀመሩ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ብዙ ዐይነት የመከፋፈያና የማስጠላት ስራዎች ሠሩ፡፡ ይህም ሁለት ደረጃዎችን እንዲያልፍ ተደርጓል፡፡
የመጀመሪያው በዚያው ፕሮቴስታንት ወደ መሆን የተለወጠውን ጸረ ሰሜን እንዲሆን የአቢሲንያ ትርክትን በብዙ ጥናቶች ታግዞ ማስፋፋትና የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኃይሉን ነጥቆ ምዕራባዊ አስተሳሰብን ተሸክሞ ብቻ እንዲኖር መገፋፋት ነበር፡፡ ይህ ኦሮሞውን ከሌላው ጋር ሊያገናኙ የሚችሉ ነገሮችን ሁሉ በመቁረጥ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ቁቤ ፊደልን መጠቀም የተጀመረው በወለጋ ጉዲና ቱምሳ የመካነ ኢየሱስ ሴክረተሪ በነበረበት በንጉሡ ዘመን እንደነበረ ከራሱ ከጉዲና ቱምሳ የሕይወት ታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ አካል ቅኝቱ በሙሉ ጸረ ኦርቶዶክስ ፣ ጸረ ሴማዊነትና ጸረ ኢትዮጵያ ጭምር እንዲሆን በብዙ መንገድ ተሠርቶበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኅትመት የበቁ ብዙ ማስረጃዎች አሉ፡፡ ሆኖም በዚህ ሥራው ብቻ የሚፈልገውን ውጤት ማምጣት በታሰበው መጠን ማምጣት እንዳልቻለ ሲረዳ ወደ ሁለተኛው ደረጃ ከፍ ተደረገ፡፡
በዚህ ሁሉ ሒደት ኦርቶዶክሳዊነትን ያልተዉ ጠንካራ ኦሮሞዎች አሁንም ብዙ ስለሆኑ ኦርቶዶክሳዊነታቸውን ሳይተዉ ጸረ ሴማዊነቱን ቢቀበሉ የመለያየት ሒደቱ ይፈጥናል የሚል ነው ሁለተኛው፡፡ ለዚህ አሁንም ሁለት ስልቶች ተግባር ላይ ውለዋል፡፡ አንዱ ዋቄ ፈታ የተባለ ባሕላዊ እምነትን በማስፋፋት በተለይ ጠንካራ ኦርቶዶክሳዊነት ያለውን እንደ ሰላሌ ያለውን አካባቢ ኦርቶዶክስ የኦሮሞ ባሕል ጠላት እንደሆነች ኦሮሞውን እንደምትንቀው በመቀስቀስ በጥላቻ ማስወጣት ፤ ሊወጣ ያልቻለውን ደግሞ ኦርቶዶክስነቱን እንደያዘ ከሰሜኑ እንዲገነጠል ማገዝ ዋና ዋና ስትራቴጂዎች ሆነው ተተገበሩ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቀሲስ በላይ መኮነን በቃልም በመጽሐፍም ከሚያስተጋቧቸው ነገሮች መካካል ሀሉም በሚባል መልኩ የዚህ ስልት ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ጥቂቶቹን እንመልከት:_
በአዋልድ መጻሕፍት ላይ በተለየ በራዕየ ማርያም ላይ የተደረሰው ብዙ ጊዜ ብዙ ፖለቲከኞች ጭምር የሚያነሡት ቢሆንም እኔ በዝርዝር አልሔድበትም፡፡ ምከንያቱም አንደኛ ድርሰቱ የውጭ ሀገር ስለሆነ፣ ሁለተኛ በትርጉም ወቅት የተፈጠረው ችግርም የተቋም ሳይሆን የራሱን ግላዊ መረዳት የጫነበት በትክክል እንኳ የማናውቀው የተርጓሚው ግለሰብ ከመሆኑም በላይ በጉዳዩ ላይ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እና ዶክተር አምሳሉ ተፈራ ጥናትና ማብራሪያ ስላደረጉበት እርሱን መመልከት የሚበቃው ነው፡፡ እነርሱ ለማየት ፈቃደኛ አይደሉም እንጂ በትርጉም ሒደት በሌሎች ጉዳዮች ላይም ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚያ ሁሉ አብረው በጥናትና በሳይንሳዊ ዘዴ መፍታት ደግሞ የሁሉም ድርሻም ግዴታም ሆኖ ሳለ ነገሩን ለጥላቻና ለፖለቲካ መጠቀም በእግዚአብሔርም በታሪክም ለዚያውም በሌላ ሳይሆን ነገ በአግባቡ በተማሩና በሚመራመሩ የኦሮሞ ልጆች ተጠያቂ ከመሆን በፍጹም አያድናቸውም፡፡ ምክንያቱም ምንም ያህል በበጀትና በፖለቲካ ኃይል ታግዞ ቢደከም እውነትን መቅበር አይቻልምና፡፡
እኔ ትኩረት ያደረግሁበት ግን መጻሕፍቶቻችን አተኩረን ካየናቸው እውነተኛ ትችትና እንደ ስድብ ሊቆጠር የሚችል ነገር ከራሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጀምሮ በሁሉም ሕዝብና በብዙ አካባቢዎች ላይ የምናገኝ መሆኑን ለማስታወስ ያህል ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የተመረጠውን የአይሁድ ሕዝብ እናንተ “የእፉኝት ልጆች” ደጋግሞ ተናግሯቸዋል፤ ወንጌልም መዝግቦታል፡፡ ራሱ ጌታችንም አይሁድን በብዙ መንገድ ገስጾአል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ አሕዛብ የተባለውን የቀረውን ዐለምም እንዲሁ፡፡ ለምሳሌ ዮሐንስ መጥምቅ ራሱ እሥራኤልን “እግዚአብሔር ለአብርሃም ከእነዚህ ድንጋዮች ልጅን ሊያስነሣለት ይችላል” ብሎ የቀረውን ዐለም ሁላችንም ጨምሮ ድንጋይ ብሎታል፡፡ ጌታችንም ሐዋርያትን “እንደ በጎች በተኩላዎች መካከል እልካችኋለሁ” ሲል ተኩላ ያለው እንዳለ ዐለሙን ነበር፡፡
ከክርስትናው በኋላም ይህን የመሰለ አገላለጽ በየትኛውም ዐለምና ሕዝብ ነበረ፤ አሁንም አለ፤ ወደፊትም ይቀራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በእኛ ሀገር የክርስትና ታሪክ ውስጥም ነበረ፡፡ ለምሳሌ በወንጌል “ከናዝሬት መልካም ነገር ይወጣልን” የሚለውን የናትናኤልን ቃል የኢትዮጵያ ሊቃውንት ጎንደር ላይ ሆነው ሲተረጉሙ አቅርበው ናዝሬት አንደ ጭልጋ የወንበዴ ሀገር ነበረች ብለው የጎንደሯን ጭልጋ ገልጸዋታል፡፡ በገድለ አቡነ አሮን ላይ ደግሞ ጻድቁ ከነበሩበት ከበጌ ምድር ጋይንት ወደ መቄት ሲጠሩ ከነበሩበት ቦታ ሲወጡ ጌታችን በዙሪያህ ካለው ሁሉ ነገር ሃምሳ ሃምሳ ሆኖ ይከተልህ ሲላቸውና ዛፎቹ ሳይቀር ሲከተሏቸው ሃምሳ አጋንንትም ተከተሏቸው፡፡ ለምን ሲሏቸው አጋንንቱም ሃምሳ ሃምሳ ይከተልህ ከተባለ እኛም እዚህ ነበርንና እንከተልሃለን ሲሏቸው እርሳቸውም የአጋንንቱን ደካማነት ለማሳየት ብለው “ከአንድ ጋይንት ሃምሳ አጋንንት” ብለዋል ተብሎ እስከዛሬ ድረስ ይነገርላቸዋል፡፡ ከዚህም በላይ ቅዱስ ላሊበላ ጎጃም አካባቢ የገጠመውን ፈተና የገለጸበት የሚባልም አባባል አለ፡፡ ወደቅዱስ ላሊበላ በእግር በመጓዝ ጎጃም ከፍተኛውን ቁጥር የያዘውም ለዚህ ነው የሚሉ ብዙ የጎጃም ሰዎችን ሰምቻለሁ፡፡ ከዚህም በላይ በእነ ገድለ ዜና ማርቆስና ገድለ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ገድለ ተክለ ሃይማኖትና ሌሎች የመካከለኛው ክፍለ ዘመን ገድላት ላይ የሰሜኑ የተለያየ አካባቢ ማኅበረሰብ እንዴት እንደተገለጸ ለሚያይ ሰው አሁን ኦሮሞ በሚባለው ሕዝብ ላይ እንኳን የተለየ ነገር ሊባልና በሰሜኑ የተባለውን ያህል እንዳልተባለ ለመረዳት በጣም ቀላል ነበረ፡፡ ሆኖም ነገሩ የተጠነሰሰው ሆነ ብለው መለያየት በሚፈልጉት ስለሆነ የእኛም ሰዎች ነገሩን ሳያነብቡና በጥልቀት ሳይመረምሩ፣ በዐለም አቀፍ ያለውን ሁኔታም ሳይመረምሩ እንዲህ የተንኮለኞችን ፕሮፓጋንዳ አብረው መንዛታቸው በእጅጉ ያሳዝናል፡፡
ኦሮሞን ጵጵስና አታጭም የሚለው እንኳ አንዳንድ ጊዜ የሚነሣ በመሆኑ እንጂ ዋናው ጉዳይ አሁን ኦሮሚያ ላይ ለምን የሌላ ብሔር ተወላጅ ጳጳሳት ይኖራሉ የሚል ነው፡፡ ለጵጵስና በማጨት በኩል ከመጀመሪያዎቹ አምስት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት መካከል አንዱ የሆኑት ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ይህን ውድቅ ያደርጉታል፡፡ መርሳት የሌለብን ግን እርሳቸውም ሆኑ ሌሎች የተሾሙት ብሔራቸውን ወክለው አለመሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም በእኛ ደካማ ሀሳብ እነርሱን ፈርጀን አምላካችንንም እነርሱንም በሰማይም ሆነው ቢሆን እንዲያዝኑብኝ እኔ በግሌ አልፈልግም፡፡
በጣም የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ ጵጵስናም ሆነ ማንኛውም ክህነት የሚሰጠው ለአገልግሎት ብቁ የሆነ ክርስቲያን በማግኘት ክርስቶስን ለመላክና ለማገልገል እንጂ ለራሱ ማኅበረሰብ ወኪል እንዲሆን አይደለም፤ መቼም ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ፍጹም ነጭ ክህደት ስለሆነ በሌላ ጊዜ ለብቻው እመለስበታለሁ፡፡ የሌላ ብሔረሰብ ተናጋሪዎች ለምን በክልላችን ይኖራሉ የሚለውም በተፈጥሮው ፖለቲካዊ ቢሆንም ለሃይማኖት ግን አሁንም ክህደት ነው፡፡ ለምን ከሐዋርያትና ከተላውያነ ሐዋርያት ውስጥ ከቅዱስ ያዕቆብ ዘኢየሩሳሌም በቀር በሀገሩ ያስተማረ የለም፡፡ ዐለም ሁሉ የተሰበከው በሌላ ሀገር ዜጋና ሐዋርያ ነው፡፡ ይህም ሰፊ ስለሆነ እዚህ ላይ ባቆመው ሳይሻል አይቀርም፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ኦሮሞው ደሴን ማዕከል አድርገው በሴሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ የተሾሙት አሁን በቅርቡ አቡነ ሰላማ ዘሰላሌ በጎንደር የተሾሙት ጉዳዩ የብሔር ስላልነበረ ነው፡፡ ትግሬው አቡነ መቃርዮስ ጎጃም ላይ ተሹመው የሸዋው አማራ አቡነ ኤፍሬም ትግራይ ላይ ተሹመው የነበሩት ጉዳዩ ልዩ ስለነበረ ነው፡፡ በዚህም አሁንም በዚህ የሃምሳ ዐመት ታሪካችን እንኳ ብዙ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ሆኖም ከዘመነ ኢህአዴግ ወዲህ ቤተ ክርስቲያናችን ለዚህ ተጽእኖ በከፍተኛ ሁኔታ መጋለጧንም መካድ አንችልም፡፡ በዚህ ደረጃ ለመባባሱ አንዱ አስተዋጽኦ አድራጊም ነው፡፡ እኔን የሚያሳዝነኝ ግን በአሁኑ ኦሮሚያ የፕሮቴስታንት ፓስተሮችና የእስልምና ኡስታዞች የየብሔሩ ተወላጆች ብቻ አለመሆናቸውን የሚያውቁ ከእኛ ወገን የሆኑት አንዳንዶቹ እንደዚህ በጥላቻ መንጎዳቸው ነው፡፡ መቼም እንዲህ ያለ የከረረ ጥላቻ እንኳን ለጽድቅና ለሃይማኖት ለፖለቲካም ተገቢ አለመሆኑ እየታወቀ እዚህ የደረሰው በእነማን ሀሳብ ተጽእኖ ውስጥ ቢወድቁ እንደሆነ ለማየት የሚቻል ይመስለኛል፡፡
በኦሮሞ ስም አቡነ ገመቹ፣ አቡነ ቶሎሳ እያለች ጳጳስ አትሰይምም የሚለው ደግሞ አስቂኝም ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም ኦርቶዶከስ ነኝ የሚል ሰው ቢያንስ ይህን ሊስተው ስለማይገባ ነው፡፡ የሌሎች ቀጥታ ሰለባና ተጽእኖ ውጤት መሆኑን ከሚያሳዩት ነገሮች አንዱ ይህ ነው፡፡ ምክንያቱም በአሰያየም በኩል ለፓስተር የሚቻለው ለጳጳስ አይቻልምና፡፡ በእኛ ጳጳሳት የሚሰዩመባቸው ስሞች ከዚህ በፊት በተጋድሎ አሸንፈው በቅድስናቸው በተመሰከረላቸው ጻድቃን ስም ስለሆነ ጻድቅነታቸው እንጂ ትውልዳቸው አይጠየቅም፡፡ ከእኛ ጳጳሳት ውስጥ ኢትዮጵያዊ ስም አለ ከተባለ ሦስት ብቻ ይመስሉኛል፡፡ እነዚህም ያሬድ፣ ተክለ ሃይማኖት እና ዜና ማርቆስ ናቸው፡፡ እነዚህም በሦስቱ ኢትዮጵያውያን ቅዱሳን ምክንያት ነው፡፡ ሌሎቹ በሙሉ የውጭ ቅዱሳን ስሞች ናቸው፡፡ ከስሞቹ መካካል (ጴጥሮስ፣ ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ፣ ማትያስ፣ … ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ፣ ዳንኤል፣ አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ፣ … ከመሳሰሉት የሐዋርያትና የነቢያት ግሪካዊ አጠራር ዕብራዊ ስሞች ቀጥሎ እነ ጎርጎርዮስ፣ ባስልዮስ፣ ያሉት የእስያ ስሞች ናቸው፡፡ እነ አረጋዊ፣ ገሪማ የመሳሰሉት ደግሞ (ስሙ በኢትዮጵያውያን የተሰጣቸው) የሮማውያን ቅዱሳን ስሞች ናቸው፡፡ ዲዮናስዮስ የግሪክ ፣ አትናቴዎስ፣ ዲዮስቆሮስ፣ ቴዎፍሎስና ቄርሎስ ደግሞ የግብጻውያን ስሞች ናቸው፡፡ ሌሎችም አንዲሁ ናቸው፡፡ አሁን በትግራይ የበዙት ኪሮስና አረጋዊ የምዕራባውያን ስሞች መሆናቸውን የእኛ ዘመን ሰው ስለማያውቅ ኪሮስ የሚባል የለገጣፎ ቤተ ክርስቲያን እንኳ ብዙ ፈተና ታይቶበታል፡፡ ስለዚህ ገመቹም ሆነ ቶሎሳ የሚባል ጻድቅ ከተገኘ ምንም ጥርጥር የለውም ይሰየም ነበር፡፡ ስለዚህ ስምን የተመለከተ እንቅስቃሴ ልክ እንደ ፕሮቴስታንቱ ሐዋርያዊ ትውፊት አልባ የአሰያየም ሂደትን ለመከተል መጠየቅ በእጅጉ አስቂኝ ነው፡፡ ልክ ቶሎሳ ገመቹ የሚባል ጳጳስ እንደሌለው ሁሉ ሓጎስ፣ መለስ፣ አበበ፣ ተስፋየ፣ ቦንገር፣ ድባቤ በሚባሉት ዓይነት ስሞችም ጳጳስ አልተሰየመባቸውም›› በስማቸው የሚታወቅ ቅዱስ እስከ ሌለ ድረስ ወደፊትም ሊሰየምባቸው እንደማይችል መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡
የኦሮሞን መሬት ወርራለች የሚለው ለመስማትም ይከብዳል፡፡ ለመሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቱ መሬት ላይ የተሠራችው ኦሮሚያ ውስጥ ብቻ ነው እንዴ? ሰሜን ኢትዮጵያስ አየር ላይ ነው እንዴት ያለችው? ወይስ በኦሮሚያ መስጊዶች የተሠሩት ከሳውድ አረቢያ በተጫነ መሬት ነው? የፕሮቴስታንቶች ማምለኪያዎች የተገነቡትስ ከአውሮፓ በመጣ መሬት ነው እንዴ? ምንነው ይህን ያህል ጥላቸው ከፋ? እነዚህን የማነሣቸው ጉዳዮቹ ከምንም በላይ ምን ያህል ፖለቲካዊ እንደሆኑ ለማሳየት እንጂ አብያተ ክርስቲየኖቹ ሲሰሩ እነዚያ ደጋግ የኦሮሞ የቀድሞ ክርስቲያኖች እንዴት መሬታቸውን በስለት ጭምር እንደሰጡ ይታወቃል፡፡ አሁንም ለሕይወታቸው ሳይቀር ሳይሳሱ ታላቅ ተጋድሎ የሚያደርትን ማስነቀፍም ባልተገባ ነበር፡፡
የኦሮሞን ባሕል አታከብርም የሚለውም እንደ ስያሜውና እንደመሬቱ ያለ ደካማ ጥያቄ ነው፡፡ የሚያዩትን የቤተ ክርስቲያን ባሕል የሰሜነኞች አድረጎ ማየት ይህ የመጀመሪያው ትልቅ ድክመት ነው፡፡ በሰሜን ያሉት አብያተ ክርስቲያን ባሕሉን ከመጽሐፍ ቅዱስና ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ያገኙት ለማንም የተሠወረ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ከሁለት ዐመት በፊት ያረፈው ኒዮርክ ውስጥ የቅዱስ ቭላድሚር የሩሲያ የነገረ መለኮት ሴሚናሪ መምህር የነበረውና በትውልዱ አሜሪካዊ የሆነው ቶማስ ሆፕኮ ኢትዮጵያን ከጎበኘ በኋላ ሀገሩ ሔዶ ሲያስተምር በዐለም የጠፋውን የክርሰትና ትውፊት በተለይ የመቀደሻ ነጩን ልብስና ነጭ ለብሶ ማስቀደስን ኢትዮጵያ በማየቱ ቀንቶ ሄዶ ያስተማረበት እና እኛም የግሪኮች ብርቅርቅ ልብስ ይቅርብን እያለ የለመነው እኮ ባሕሉ የአማሮችና የትግሬዎች ሳይሆን የጥንቷ የሐዋርያዊቷ ቤተ ክርስቲያን ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ የሆነውም ክርስቲያኑ ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን ለመምሰል ሲጥር ባሕሉ አደረጎት በኑሮውም ቤተ ክርስቲያንን ለመምሰል ጣረ እንጂ ከአማራና ከትግሬ ቤተ ክርስቲያን የወሰደችውም ምንም ነገር የላትም፣ ሊኖራትም አይችልም፡፡ እነርሱ ቤተ ክርስቲያንን ለመምሰል ጣሩ እንጂ ቤተ ክርስቲያናቸው እነርሱን እንድትመስል ጥረው አያውቁም፡፡ በዐለምም ላይ የሆነው ይሔው ነው፡፡ አሁን ግን ይህን ባሕል የሚጠሉት የሌሎች ሃይማቶቹን ፕሮፖጋንዳ ይዞ መነሣት ሞኝነቱ በብዙ መንገድ ይገለጣል፡፡ ይህ ከልብ የሚያሳስባችሁ ከሆነ አሁንም እስኪ ኦሮሚያ ውስጥ ያለውን እስላምና ፕሮቴስታንት ተመልከቱት፡፡ እነርሱ ዐለም አቀፍ የየእምነቶቻውን ባሕል ይዘው ተንኮለኞቹ እናንተን ኦርቶዶክስነትን እንድትጠሉት ይህን ሲሏችሁ እንዴት እውነት መሰላችሁ?
“የሹም ሰነፍ ባይለፈልፍ”
በአጠቃላይ የሚነሡት ነገሮች በሙሉ ከእምነት ማስፋፋት ጋር የሚገናኝ አንድም ጉዳይ አላቸው ብየ በግሌ አላስብም፡፡ ከዚህም በላይ ፖለቲካውንና ሌላውን ጫና በማሳረፍ በኦሮሚያ ውስጥ ያለችው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከተቻለ ሙሉ በሙሉ አንድትጠፋ ካልሆንም በብዙ መከራ ክርስቲያኖቹ ተማርረው እንዲጠፉ ለማድረግ ከሚሠራው አካል ጋር በትንቅንቅ ያሉትን የእውነተኞችን የኦሮሞ ኦርቶዶክሶች ጥያቄ እንዲህ በሌላ መርዛማ ነገር ማዳፈኑ በእጅጉ ያንገበግባል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ባለ ሥልጣናቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የሚያዝኑና የሚቆረቆሩ በመምሰል የሚሠሩት ደባና ተንኮል ያሳዝናል፡፡ እውነቱ ግን በጊዜው መገለጡ አይቀርም፡፡ የሚፈልጉትን እያደረጉና እያስደረጉ፣ እንደገና ደግሞ ወደ ቤታችን እየመጡ የተለያየ ነገር መናገሩም ያሳዝናል፡፡ በዚያውም ላይ ጧት የተናገሩትን ማታ አለመድገም፤ በአንዱ የሚያቀርቡትን አመክንዮ በሌላው መናድ ሁሉ አስገራሚ ነው፡፡ እንኳን ሌላው ሥልጣንንና ባለሥልጣንነትን እንዲህ ማስናቅም ያሳፍራል፡፡ ሊቃውንቶቻችን “የሹም ሰነፍ ባይለፈልፍ” እንዳሉት ሥራቸውን እየሠሩ እዚያው ዝም ቢሉ ያምርባቸው ነበር፡፡ ነገ ከልካይ የሌለው የእግዚአብሔር ፍርድ ሲገለጥ ግን እንኳን ሠሪዎቹ የተሳሳተና የንቀት ምክር ከሚያማክሩት አንሥቶ በጀርባ ሆነው ሴራ እስከሚተበትቡት ድረስ ሁሉም ነገ ይጋለጣል፡፡ ዘመኑ የመረጃና የቴክኖሎጂ ዘመን ነውና የሚቀር ነገር እንደማይኖር ለመረዳት ያን ያክል አስቸጋሪ ነገር የለምና፡፡
ለመሆኑ እነዚህን ሁሉ ችግሮች የሚፈጥሩ ነጭ ሚሽነሪዎች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን እንዲህ የሚጠሏት ለምንድን ነው? ኦሮሚያ ውስጥ ያለው እውነተኛው የኦርቶዶክሳውያን ችግር ከሌሎቹ አካባቢዎች ካለው በምን ይለያል? እንዴትስ ሊፈታ ይችላል? በችግሮቹ ሰበብ ፖለቲካዊ ግብ ይዘው የተነሱት ሰዎች ፖለቲካዊ የእምነት ተቋም መመሥረት ቢችሉ ፍጻሜው ምን ሊመስል ይችላል? በሚቀጥሉት ጊዜያት እመለስበታለሁ፤ ይቆየን፡፡