>

በእስክንድር ነጋ ላይ የተፈጠረው ጫጫታ እንደምታ ምንድነው? (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

በእስክንድር ነጋ ላይ የተፈጠረው የጫጫታ እንደምታ ምንድነው?
ሞሀመድ አሊ መሀመድ
ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ውስጥ መስጊድ ሲፈርስና በሙስሊሞች ላይ ድብደባ ሲፈፀም ባልደራሱ እንዴት አላወገዘም ብለን ነበር። በርግጥ ዘግይቶም ቢሆን (ሙስሊሞች ቅሬታቸውን ከገለፁ በኋላ) እነስክንድር ነጋ የፈረሰውን መስጊድ ሲጎበኙ አይተናል። ያኔ ባልደራሱ “በሃይማኖት ጉዳይ ምን አገባው” አላልንም። ያኔ ጥያቄያችን የነበረው የነእስክንድር ባልደራስ የሙስሊሙን ጉዳይ እንዴት ነው የሚያዬው የሚል ነበር።
አሁንስ በኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ላይ እየተፈፀመ ያለውን ሴራ አይቶ እንዳላዬ ዝም ብሎ ማለፍ ይኖርበት ይሆን? ምናልባት ይኸኛው በእምነቱ ተከታዮች መካከል የተፈጠረ የውስጥ ችግር ነው ሊባል ይችል ይሆናል። ነገር ግን (ከሲኖዶሱ ዕውቅናና ይሁንታ ውጭ) የመንግሥት አዳራሾች እየተመቻቹላቸውና በመንግሥት ሚዲያዎች ሽፋን እየተሰጣቸው “አዲስ አበባ የኦሮሞ ነው” የሚል ሙግት የሚያቀርቡት የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ አንቀፅ ወይም ድንጋጌ መሠረት አድርገው ነው? ይህን አካሄድ በድፍኑ (in a nutshell) ሃይማኖታዊ ነው ብሎ እንዴት መውሰድ ይቻላል? ከዚህ ጀርባስ የነማን እጅ ሊኖር ይችላል? ይህን ታሳቢ በማድረግስ “ከቤተ-ክርስቲያን ላይ እጃችሁን አንሱ” ማለት ምንድነው ስህተቱ?
ባልደራሱ በፖለቲከኞች ላይ ጫና ለመፍጠር እንደሚንቀሳቀስ ቡድን (pressure group) በኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ላይ እየተፈፀመ ያለው ድርጊት እንደሚያሳስበውና; መንግሥት; እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንዲህ ዓይነት sensitive ጉዳዮችን በተገቢው ጥንቃቄ መያዝ እንዳለባቸው ቢገልፅ ምንድነው ስህተቱ? እስክንድር ነጋ በየትኛውም ጉዳይ ላይ መግለጫ እንዳይሰጥ መንጫጫትና አፍ ለማዘጋት መሞከር ምን የሚሉት ነው?
ከዚህ በፊት በአዲስ አበባን ጉዳይ ለመምከር እንዴት ባህርዳር ይሄዳል? በሚል የተፈጠረውን ጫጫታ የምናስታውሰው ነው። ሆኖም ግን; ቀደም ሲል እነለማ መገርሳ (TeamLema) በተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ዙሪያ ለመምከር ባህርዳር ሲሻገሩ “እሰይ – አበጃችሁ” ብለን አጨብጭበን ነበር። ታዲያ አዲስ አበባ ላይ አዳራሽ እየተከለከለ “መስጊድ እንደገባች ውሻ” የሚዋከበው እስክንድር ነጋ ባህርዳር ሂዶ ከህዝብ ጋር ቢመክር ምንድነው ስህተቱ?  ወይስ የባህርዳር ህዝብ የሀገሪቱ መዲና የሆነችው የአዲስ አበባ ጉዳይ አይመለከተውም? የአዲስ አበባ ጉዳይማ ሁሉም ይመለከተዋል። እናስ የዚህ ሁሉ የጫጫታ አንደምታ ምንድነው?
Filed in: Amharic