>

የወቅቱ "ሰርካለም ፋሲል!!!" (መስከረም አበራ)

የወቅቱ “ሰርካለም ፋሲል!!!”
መስከረም አበራ
ጭካኔ ያስጨክነኛል! እስከምጨክን ግን ጊዜ እወስዳለሁ፡፡ጨካኝ ጭካኔን የመረጠበት አንዳች ምክንያት ይኖረው ይሆን መጨከን ብቻ መፍትሄ ሆኖ አግኝቶት ይሆን፣ጨካኝ በቆመበት ቦታ ሆኜ ባየው ካልጨከነ የሚበላሽ ነገር ይኖር ይሆን በሚል በጨካኝ ላይም ቢሆን ቶሎ ላለመጨከን ከደመነፍሴ ጋር እሟገታለሁ፡፡ይህን የማደርገው አንዴ ጭካኔ ከገባኝ ለመመለስ ስሜቴ እሽ ስለማይለኝ ነው፡፡
በህወሃት መራሹ ኢህአዴግ  የመጨረሻ ዘመናት በጨካኙ ላይ የመጨከን ደረጃ ላይ ደርሼ ነበር፡፡ይህ ስሜቴ የኢህአዴግ ባለስልጣን ቀርቶ አሽቃባጭ ደጋፊ ሳይ ጭምር ደስ የማይል ስሜት እንዲሰማኝ ያደርገኝ ነበር፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሰኝ የህወሃት መራሹ መንግስት  የተከማቼ ጭካኔ ላይ አንድ ሁለት ቀን በማምነው የቪኦኤ ሬድዮ የሰማኋቸው ታሪኮች ናቸው፡፡
አንደኛው አንድ አባት የሶስት ልጆቻቸው ሬሳ እንደከሰል በማዳበሪያ ተጠቅልሎ  በራቸው ላይ እንደቆመላቸው ሲናገሩ የሰማሁት ታሪክ፣ ሁለተኛው በማዕከላዊ የደረሰበት ሰቆቃ በፍርድቤት በሰው መሃል ልብሱን አውልቆ ሃፍረተ ሰውነቱን እስከማሳየት ያደረሰውን ታሳሪ ታሪክ ስሰማ እና ሶስተኛው ብዙዎቻችሁ የምታውቁትን እናትን የልጇ አስከሬን ላይ አስቀምጦ የመደበደቡ ታሪክ ነው፡፡
 እነዚህ ታሪኮች ቀድሜ ካነበብኳቸው ጭካኔዎች ጋር ተደምረው ሰው ባልሆኑ ፍጡራን እየተመራን እንደሆነ ይሰማኝ ጀመረና ጥላቻየም ሰውን ሳይሆን የሆነ አውሬን የምጣላ እስኪመስለኝ ድረስ የመረረ ሆነ፡፡ በአውሬ የመሰልኳቸው ሰው መጥላት ዘና ብዬ የምቀበለው ስሜት ስላልሆነ ነው፡፡
ለማንኛውም እነዚሁ ሰዎች ተሸሻልን ብለው፣ የባሰባቸውም ከስልጣን ተባረው አዲስ ዘመን የመጣ፣ ጫፍ የወጣ ግፍም አንሰማም የሚል ተስፋ ነበረኝ፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ዛሬም ሰዎች በገፍ ታፍሰው ይታሰራሉ፣ለአንዱ የተፈቀደ ነገር ለሌላው ወንጀል ሆኖ እንትን ቲቪን ለምን መሰረትክ የሚል ነገር መመርመሪያ መስቀለኛ ጥያቄ ሆኖ መጥቷል፡፡ሰው ሊጠይቅ የሄደ ሰው እንኳን ማርያም አመጣችህ ተብሎ በዛው እስርቤት ይዶላል፡፡
ከዚህ ሁሉ ብሶ እያሳዘነኝ ያለው ግን የነፍሰ-ጡሯ የጀነራል አሳምነው ፅጌ ባለቤት የወ/ሮ ደስታ ነገር ነው፡፡ይህች ሴት ከታሰረች ሁለት ወር ሊጠጋት ነው፡፡የትኛውም ፍርድቤት ቀርባ ወንጀሏ ሲነበብ እና ስትከራከር አላየንም፡፡ክስ ተመስርርቶባት ወደ መደበኛ ማረሚያቤት አልተወሰደችም፡፡ሁለት ወር ለሚጠጋ ጊዜ ፖሊስ ጣቢያ ታጉራለች፡፡ ከሁሉም በላይ ነፍሰጡር ነች፤የህክምና ክትትል ያስፈልጋታል፣ባሏን ያጣች ሃዘንተኛ በዛ ላይ ነፍሰ-ጡር ሴት ወንጀልሽ ይህ ነው ሳትባል እስርቤት መታጎሯ እጥፍ ድርብ ግፍ ነው፡፡
ከሴት ያልተወለደ የለም፤እናት የሆነ ሴት ሁሉ ደግሞ እርግዝናን እና የስሜቱን ክብደት ያውቀዋል፡፡የሰውን ልጅ ያክል ነገር በሆዷ የያዘች ሴት ስንት ወር ሙሉ ፖሊስ ጣቢያ ያጎሩ ግፈኛ የለውጥ አመራር ተብየ ወንዶች  ከሴት የተወለዱ፣በሚስቶቻቸው በኩል እርግዝና ምን እንደሆነ የሚያውቁ ናቸው፤ሴቶቹ የለውጥ አመራር ነን ባዮች ደግሞ በየደረሱበት ስለ ሴት ልጅ መብት የሚቀባጥሩ፣ልጅ አርግዞ መውለድም እንዴት ያለ ጫና ያለው ነገር እንደሆነ የሚያውቁ ናቸው፡፡ግን ሁሉም የዚች ምስኪን ሴት ነፍስ አያሳስባቸውም፡፡ለአልጀዚራ ዶክመንተሪ ቃል ለማሳመር የምትለፋዋ ወ/ሮ መዓዛም ይህን ሳታውቅ ቀርታ አይደለም፡፡የግለሰብ ጉዳይ አይመለከታትም እንዳይባል ስለ ግለሰብ ሴት እስረኞች ያላትን ተቆርቋሪነት በአልጀዚራ ስታወራ አይቻለሁ፡፡ይህች ሴት ግን ነገስታት በክፉ አይን ስላዩዋት ብቻ ጆሮ ዳባ ትባላለች፡፡ይህን የመሰለ ጭካኔ የሚያስጨክን ሃገራዊ ፋይዳ ያለው ምክንያት የላቸውም-ተራ ጥላቻ እና ቂም በቀል እንጅ!
አንድም እናት በወሊድ እንዳትሞት የሚፈልጉት የጠላታቸው ሚስት እስካልሆነች ድረስ ነው፡፡ይህች ሴት ግን በሚታመነውም በማይታመነውም ስሙን ሲያክፋፉት ምን ያህል እንደሚጠሉት የሚሳያሳብቅባቸው የጀነራል አሳምነው ሚስት ነች! ስለዚህ አንድም እናት እንዳትሞት  ከሚባልላቸው ሴቶች ውስጥ አይደለችም ፤ቢሻት ትሙት! ይህች ሴት በህወሃት መራሹ ዘመን እስርቤት አርግዛ እስርቤት ስትዎልድ ከሞት አፋፍ የተመለሰችውን ሰርካለም ፋሲልን የምትመስል የተረኛ አምባገነን መከረኛ ነች፡፡ፈጣሪ አብሯት ይሁን እንጅ ምን ይባላል?
በጣም የሚያሳዝነው ይህች ሴት ይህን ሁሉ መከራ የምታየው የአሳምነው ሚስት ስለሆነች ብቻ ነው፡፡ እንጅ የሰራችው ወንጀል ቢኖር አንቀፅ ተጠቅሶባት ስትከሰስ እንሰማ ነበር፡፡ይህ ጭካኔ የኢህአዴግ ሰዎችን አረመኔነት ፣ተበቃይነት እና ግብዝነት የሚያሳይ ነገር ነው፡፡ ነገሩ እነዚህ ባለጊዜዎች ምን ያህል ጀነራል አሳምነውን ይጠሉት እንደነበረም ያሳያል፡፡የፈለገ ቢጠሉት አሁን እሱ ሚስቱ መታሰሯን አውቆ የሚያዝንም መፈታቷን ሰምቶ የሚደሰት ሰውም አይደለም-ከአፈር በታች የሆነ በድን እንጅ! ነገሩ ሁሉ ሬሳ መበቀል ድረስ የሚሄድ ኢህአዴጋዊ ክፋት ነው፡፡ ከዚህ ሌላ አንድ ምስኪን ነፍሰጡር ሴት የሚጠሉት ሰው ሚስት ስለሆነች ብቻ አስሮ ማንገላታት ምን ይባላል?የዚች ሴት ጉዳይ የዛሬ ሳምንት  በጋዜጣ ወጥቶ ስመለከት ቢያንስ የልጅቷን ሮሮ ሰምተው አንድ ነገር ያደርጉ ይሆናል በሚል ነበር ቀናትን የጠበቅኩት፡፡ግን ነገስታት ልባቸው ይራራ ዘንድ ተራ ሰው አይደሉምና በጭካኔያቸው ላይ ተመቻችተው ተኝተዋል፡፡ይህ የሰው የማይመስል ጭካኔ ኢህአዴግ የሚባል ወትሮም አስቀያሚነቱ የሚታየኝ ፓርቲ ምን ቢኳኩሉት የማያምር የአውሬዎች ስብስብ መሆኑን ይናገራል!
Filed in: Amharic