>

ከአሮጌ ጥላቻችን ጋር ወደ አዲስ ዓመት... ??! (አሰፋ ሃይሉ)

ከአሮጌ ጥላቻችን ጋር ወደ አዲስ ዓመት… ??!
አሰፋ ሃይሉ
ሰሞኑን የማዕከላዊ እስረኛ ማሰቃያ ክፍሎች ግድግዳ ላይ የተፃፉ የሰቆቃ መዝገቦች ለምን ተፋቁ? ለምን ግደግዳው ቀለም ተቀባ? የታሳሪዎቹ ስቃይና ሕመም ለትውልድ መማሪያነት እንዳለ መተው ነበረበት! ወዘተ ወዘተ የሚሉ የቁጭት ስሞታዎችን ከተለያዩ ሰዎች አንደበት አድምጬያለሁ።
በአንድ በኩል እውነት ነው። ያ የግፍ ጠባሳ በቦታው ቢቀመጥ የክፋት መታሰቢያ ይሆን ነበረ። ያ ሥፍራ በአንድ በክፉ ወቅት በጣም የቅርብ የቤተሰቤ አባል ለወራት በኤሌክትሪክ ሾክ የተሰቃየበት ሥፍራ ነበረ። አጋጣሚ ሆኖ አልገባሁበትምና ተዘጋ ሲባል ብጎበኘውም ብዬ አስቤ ነበረ። እና እንደ አዲስ የኪራይ ቤት አጠፉት በቀለም ሲሉኝ ግራ ተጋባሁ።
አሁን ግን ረጋ ብዬ ሳስበው እንኳንም አጠፉት ብዬ የግድግዳውን ስቃይ ማጥፋታቸውን አደነቅኩት። ምክንያቱም እንዳለ ቢቀመጥ ለአሁኑና ለወደፊቱ ዜጋችን ምንድነው የሚያተርፍለት? ጥላቻ። እና ቂም ነው። ግርፋቱና ስቃዩ ከሰው ልብ ውስጥ አልጠፋ ብሎ መለብለቡ ሳያንስ ያን ክፋት ለምን በግድግዳዎች ላይ ህያው አድርገን ለማቆየት እንሻለን? መቆየት አልነበረበትም።
ያለፈን ቂም ይዘን እያስታወስን መጪውን አዲስ ዘመን ከነአሮጌው ጥላቻ ብንሻገር – ተሻገርን አያሰኘንም። ከጥላቻችን ፈቀቅ ሳንል ወደ አዲስ ዘመን መሻገር የለም። ቂምን አንጠልጥሎ ፀሎት የለም። እና። እንኳንም አጠፉት።
በዚሁ መርህ ተመርተን አዲሱን ዘመናችንን ብሩህ የፍቅር እና የ “መደመር” (ክሊሼ ስለሆነብኝ ይህን ቃል ባልጠቀመው ብመርጥም) የ”መደመር” አዲስ ዓመት ለማድረግ ቆርጠን ከተነሳን – እንዴት ጥላቻን ተራራ አሳክለን በሕዝቦች መሐል ከነቆለልንበት የጡት ቁራጭ ጋር ይህ የመደመር ግብ እንዴት ሊሳካልን ይችላል?
ጥላቻን ከአሮጌው ዓመት ተሸክመን ወደ አዲሱ ዓመት እያሻገርን እንዴት ወደ አዲስ ዘመን ተሸጋገርን ብለን በሰው ፊት መቆም እንችላለን? ሁሉም ከሥኬቱና ከውቡ ነገር ይልቅ ቂሙንና ቁርሾውን ተራራ አሳክሎ ማቆምን ከመረጠ – መጪው ትውልድ በየት ቀዳዳ አልፎ ነው ፍቅርን ማሰብ የሚችለው?
እናስበው እስቲ? አፄ ዮሐንስ የጎጃምን መነኮሳት እመይቶቸን ሁሉ ሳይቀር ነው ቆራርጦ ያስቀራቸው። አዝማሪ እስካሁን ይገጥምባቸዋል በአንዳንዶቹ የሀዘን ስንኞች። አፄ ቴዎድሮስ የከዳቻቸውን የወሎ ባላባት እና ያመፁባቸውን የሸዋ ነገሥታት ከነተከታዮቻቸው ለመቀጣጫ እንዲሆን እጅ እጃቸውን ነስተዋቸው ነው የተመለሱት።
የአኖሌውን ጡት ምኒልክ ቆረጡ የሚለው ተረት ተረት መሆኑን ሟቹ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አስረግጠው ስለነገሩን ልለፈውና – አጤ ምኒልክም እንዲሁ ከወገን ከድተው ለነጭ ወራሪ ያደሩትን አስካሪ ባንዳዎች እጅ እግራቸውን ነው የነሷቸው።
ወያኔም እግሩን የቆረጠችውን አሳዛኝ ሰው ኦህዴዶች አዲሱን ስማቸውን ሊቀይሩ ሰሞን በአደባባይ ሲሸልሙትና ሲያፅናኑት ነበረ። በቀደመው ዘመን የጉጂ ኦሮሞ ተዋጊዎች ጀግንነታቸውን ለማስመስከር የሰለቡትን የወንድ ብልትና የሴት ጡት ብዛት ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው።
በቃ በዚህች ምድር ላይ ያልሆነ የለም። ሁሉም – ክፉው ሁሉ – ከነበጎው – በጊዜው ሆኗል። ሆኗል ግን አልፏል። አልፏል ብቻ ሳይሆን ባለፈው የጋራ ታሪካችን የሆኑትን ነገሮች ሁሉ አልፈን ይኸው ለዛሬ በቅተናል። ዛሬስ ላይ ቢሆን ቄሮ በቡራዩ ላይ የተለተለው የጋሞዎች አካል በፎቶግራፍ ሁሉ እኮ የተቀረፀ ነው። ያንንንም ግን አልፈን ይኸው ከዓመት ዓመት እየተሻገርን አለን። ከነጥላቻችን እንዳለን አለን።
ግን ግን ልክ ለአኖሌ ተብሎ እንደተተከለው የተቆረጠ ጡት ያንን ሁሉ ከዘመናት እስከ አሁን ለተቆረጠው የወገናችን የአካል ክፍል ሁሉ ተራራ የሚያካክል ሀውልት እየሠራን ብናቆም የሚተርፈን የሰው አካል ክፍል ቅርፅ ይገኝ ይሆን?! የተቆረጠ እጅ ኃውልት። የተቆረጠ እግር ኃውልት። የተቆረጠ ጡት ኃውልት። የተቆረጠ አንገት ኃውልት። የተቆረጠ ጡት ኃውልት። የተሰቀለ ሰው ኃውልት። የተቆረጠ ብልት ኃውልት። በቃ ሀገሪቱን የታወቀች የጥላቻ ቄራ አድርገናት ቁጭ።
ለዚያ ሁሉ የተቆራረጠ የሰው ልጅ አካል የምናወጣውን ኃይልና የፈጠራ ሀሳብ ጥሩ ነገር ላይ ብናውለው መልካም አዲስ ዓመትን አንቀዳጅበት ይሆን??!!
እና በቃ – አሮጌውን ጥላቻ አዝሎ – የአምናን የካቻምናን ቂም አንጠልጥሎ – አዲስ ዓመት ተሸጋገርን ማለት – ቆራጣ ቀልድ ነው። ቀልማዳ ወሬ።
በመጀመሪያ የገነባነውን የጥላቻ ኃውልት እናፍርስ። በጋራ ለተቀዳጀናቸው ሥኬቶች የጥንካሬያችንን፣ የአዲስ ተስፋ ብሥራታችንን ማሳያ አዳዲስ ኃውልቶችን ለማነፅ እንዘጋጅ። ያን ስናደርግ አዲስ ዓመት በአሮጌ ጥላቻ አይደፈርስም። ያን ስናደርግ አዲስን ዓመት – አዲስ ዓመት ብለን በሙሉ አፋችን መጥራት እንችላለን።
ካልሆነ ግን ሁሉም የይስሙላ ድራማ ብቻ ነው።
“ዓለም ትያትር ነች፥ ሰዎቿም ተዋናዮች ናቸው” ያለው ማን ነበረ? አቡነ ጃዋር ይሆን?
ማንኛውም – ፈጣሪ ከክፉ ሁሉ ይጠብቀን።
ሀገራችንን ይባርክ።
መልካም አዲስ ዓመ..ል!!!
መልካም በዓል!
Filed in: Amharic