>

በስዊድን መነጽር ኢትዮጵያዬን ስመለከታት!!! (ታዬ ቦጋለ አረጋ)

በስዊድን መነጽር ኢትዮጵያዬን ስመለከታት!!!
ታዬ ቦጋለ አረጋ
 
 * የውሻ መብት ከሚከበርባቸው ሀገሮች መጥተው – የሰዎችን ሰብአዊ መብቶች የሚጋፉ ክፉዎች ስናይ – ሳንወድ በግድ እንድንጀግን የግድ ይለናል።
 
እኛ ወገናችን ዛሬን እንኳ እንዳይኖር እናናክሳለን። በደል ፈጥረን ቂም እናወርሳለን። እሳት ለኩሰን ወገን እንዲቃጠል እንሰራለን። ፀፀት ተሰምቶን ንስሓ ገብተን ይቅርታ በመጠየቅ ፈንታ – ለተጨማሪ ጥፋት እናደባለን። በወገን ደም እንቆምራለን
የትላንቶቹ የስዊድን አበውና እመው የዛሬ ልጆቻቸውን ከዘመናት በፊት አሳድገው አልፈዋል። የዛሬዪቱን ስዊድን ከምዕተ ዓመታት በፊት በምናባቸው ዐይተው አልፈዋል።
*
የኢትዮጵያ መጋኞች እዚህ በሰለጠነው ዓለም –  በሚገርም ህብር ውስጥ  – በቅንጦት እየተንደላቀቅን – ያቺን ጉሊት ጠርጋ፣ ጭራሮ ለቅማ፣ በጪስ ተጨናብሳ ዐይኖቿ የሞጨሞጩ እናት፣ የዛሬ 6,000 ዓመት በተሠራ ማረሻ  እርፍ ጨብጦ እጁ መጅ ያወጣ፣ ዐይኖቹ የጎደጎዱ አባት = የሰቆቃና ሲቃ ምንጭ እንሆናለን።
*
ለለውጥና እድገት – ወጣቱን አፍ ከልብ አሰናኝተን ከማትመም ይልቅ – በየቀኑ የመሀከለኛውን ዘመን የብሔረሰብ፣ የሀይማኖት፣ የመንጋ የበረት አስተሳሰብ እያመጣን፦ ብሔረሰብን በጎሳ፤ ሰማያዊውን ህይወት እንኳ ለየብቻ ለማስመለክ አማኝ እንከፋፍላለን።
ለሀገር ውለታ የዋለቺውን የቅርስ የስነምግባር የእምነት የመቻቻል አስተማሪ እናት ቤተክርስቲያን በጥላቻ እንዘምትባታለን።
የጥላቻችን ጠርዝ ማሳያ =  ቋንቋ ከመግባቢያነት ውጭ ተወስዶ – በአማርኛ መጸለይ ከአማራ ጋር ተያያዘና፦
“ከእንግዲህ በፈጣሪና በኦሮሞ መሀከል አማራ ጣልቃ አይገባም”
የሚል የስንፍና ቃል – በብልግና ተፀንሶ – አጀንዳውን ባቀበለው ወያኔ እና ያለማቋረጥ በሚዘውረው ‘ዲጂታል ወያኔ’ – አምሳለ ወያኔ በሆነው ጥፍጥፍ የእጅ ሥራው ሸኔ – እየሾረ – በተጃመለው መንጋ እየታጀበ – በወገን መሀከል የጥላቻ ድባብ ሰፈነ።
*
 ምሁራን ለአንዳች ልዩ ግኝት ሳይሆን ለጥላቻ ራሳቸውን “አጀገኑ”
የአጀንዳዎቹ አቀባባዮችና ለጥፋት የሚተጉት ሰይጣናውያን መኖሪያ የምዕራቡ ዓለም መሆኑ በምክንያት ያስቆጫል።
ዛሬ ስዊድን ውስጥ ማን የተባለው ፀረ-ኢትዮጵያ እንደሚኖር ለራሳችሁ የቤት ሥራ ሰጥቼ – ወደ ጀመርሁት የስዊድን ወግ ልመለስ፦
*
ከአውሮፓ ከተሞች በስፋት አራተኛ የሆነቺው ስዊድን በርካታ አስገራሚ ገፅታዎች አሏት። በውሀ የተከበበችው ይህች ድንቅ ሀገር “የስካንዲኔቪያ ሼኒስ” እየተባለች ትንቆለጳጰሳለች። በዋና ከተማዋ የሚታየው ርጋታ፣ መሽቀዳደም የማይታይበት የትራፊክ ፍሰት፣ የተሽከርካሪን ህግ ብቻ ብንወስድ ጥፋት አጥፍቶ መሰወር አይሞከርም። የመንገድ ትራፊክ ህግ የጣሰ አሽከርካሪ 2,000 ክራውን (ክሮነር) ይቀጣል። ትራፊክ ፖሊስ በህጉ ጣልቃ ገብቶ መደራደር አይችልም። (ሥርአቱ የዘመነ ስለሆነ ለሌብነት እድል አይሰጥም።)
 በተሽከርካሪ ውስጥ ያለ ተሳፋሪ በሙሉ የመኪና ቀበቶ ማሰር ግዴታው ነው። ከ18 ዓመት በላይ እድሜ ያለው ተሳፋሪ ‘ቤልት’ ካላሰረ – ሾፌሩ (አሽከርካሪው) ከደሙ ንፁህ ነው = ተሳፋሪው ራሱ ይቀጣል።
*
በዓለም ትልቁ Open Air Museum እዚሁ በሀገረ ስዊድን ይገኛል።
 ስዊድን ውስጥ ወንጀል ፈፅመው – መልካም እንክብካቤ ባለበት የማረሚያ ቤት ለመታሰር ከእነ ላቲቪያ ሉቴንያ ኤስቶኒያ ወዘተርፈ ወደ ስዊድን የሚመጡ ወንጀለኞችም አሉ። መነሻቸው እንክብካቤ ፍለጋና እስር ቤት ውስጥ የሚሰጠውን የኪስ ገንዘብ አጠራቅመው ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በማሰብ ነው።
*
የከተማው ንፅህና፣ አረንጓዴው ልምላሜ፣ ወደ ውስጥ የሚማገው አየር ከብክለት ነፃ መሆን ያስደምማል። መንግሥት ለዜጎቹ አብዝቶ ይጨነቃል። የመኪና ጭስ ፈፅሞ ዐላየሁም። አየሩ እንዳይበከል ‘ባይስክል’ በነፃ ሊባል በሚችል ደረጃ በየስፍራው የሚያቀርበው የስዊድን መንግሥት – አሁን ደግሞ በምድር ልብ ውስጥ የሚጓዝ የመኪና መንገድ ለመሥራት ግንባታ ላይ ነው። መንገድ ሲሠራ ከዕይታ ተከልሎ ብቻ ሳይሆን በምሽት ጊዜ ነው።
*
ቅዳሜና እሁድ እረፍት ነው። ከኢትዮጵያ የሄደ አንድ ወገን በትርፍ ሰአት ቀንና ሌሊት፣ ቅዳሜና እሁድ ጭምር እየማሰነ መሆኑን ለአለቃው ሲነግረው –
“ባለማወቅ ያደረግኸው ስለሆነ አልቀጣህም! = ካላረፍህ ዛሬን በተቃወሰና በተጨናነቀ ሁኔታ መሥራትህ መጉዳቱ  ብቻ ሳይሆን፤ ነገ ያለጊዜህ በመጦር ጉዳት ታስከትላለህ” አለው። (ስዊድን ውስጥ ከፍተኛውን መዋዕለ ነዋይ የሚጠቀሙት ጡረተኞች ናቸው።)
ኢትዮጵያ ረጂም እድሜ ልትኖር ቀርቶ ሞትህም አያሳስብምና ከቻልክ 24/7 ሥራ። ይህኛው ተሞክሮ እስክንደርስበት ለዛሬዎቹ ለቁም ሙታን – ለእኛ አይጠቅምም።
*
የገረመኝ ነገር ስዊድን ውስጥ ከአምስት ዓመት በላይ የቆዩት ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንደ ስዊድኖቹ ሁሉ በጣሙን የተረጋጉ ናቸው። ለሀገር ያላቸውን ፍቅር በዕንባ ጭምር ይገልፃሉ። ስንትና ስንት የሚያስተምረኝ ምሁርና የከበረ አረጋዊ ባለበት ሀገር – ለእኔ ለትንሹ ሰው የሰጡኝ ክብር – ብቸኛ መነሻው ለኢትዮጵያዊነት ያላቸው ፍቅር ነው።
*
ስዊድን አጀብ ታሰኛለች። የእኔ መሻት ግን እኛስ ኢትዮጵያን አጀብ የምታሰኝ ሀገር የምናደርጋት መቼ ነው?!
*
ዳጊስ (መዋዕለ ውሻ) = ጃዋር ይሰማልን?!
*
ለኛ አስገራሚ – ለስካንዲናቪያ የዘወትር እውነታ፦
ስዊድን ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ውሾች – “ውሻዊ መብታቸው” ይከበራል።
*
የውሾች አሳዳሪዎች ውሾቻቸውን በዘፈቀደ እንዳሻቸው ማኖር አይፈቀድላቸውም።
*በመጀመሪያ ደረጃ የተሟላ መኝታ ክፍል ሊዘጋጅላቸው ይገባል።
*ምሽት ላይ ቤት እንደማደራቸው መጠን  ሲነጋ የመናፈስ መብታቸው ይጠበቅላቸዋል። አሳዳሪዎቻቸው ጧት ሲያናፍሷቸው ኩሳቸውን (አ*) ለማንሳት የእጅ ግሎቭና ላስቲክ መቋጠሪያ  ይዘው ይከተሏቸዋል።
*የሚደንቀው ሥራ የሚውሉ ሰዎች ውሾቻቸውን ለብቻ ቤት ውስጥ ማዋል በፍፁም አይችሉም። ስለሆነም ወረፋ ተይዞ በመከራ በወር 2,000 ክራውን (ክሮነር) እየተከፈለላቸው “መዋዕለ ውሻ” ውስጥ ይቆያሉ።
*ውሾቹ በምንም መልኩ ትራፊ ምግብ አይበሉም። የማይስማማቸው ‘አለርጂ’ የሆነ ምግብ በስህተት እንዳይሰጣቸው ይመዘገባል። (የየራሳቸው ምሳ ይቋጠርላቸዋል።)
በበረዶ ወቅት – የበረዶ ልብስ ይለብሳሉ።
*
እንዳንቃጠል ከብዙ በጥቂቱ ይህንን ካካፈልኳችሁ – የውሻ መብት ከሚከበርባቸው ሀገሮች መጥተው – የሰዎችን ሰብአዊ መብቶች የሚጋፉ ክፉዎች ስናይ – ሳንወድ በግድ እንድንጀግን የግድ ይለናል።
*
ጃዋር ይሰማል?! – እረፍ!
ጉልበትህ የተለየ ሆነህ የተገኘ ሳይሆን – ከምትረጨው ዶላርና ሳይገባው ከሚጃመለው መንጋ የመነጨ ነው።
– እንጂ – በተዋህዶ ሀይማኖት ውስጥ፦
ምን ኮነሰረህ?!
ምን ዶለህ?!
ምን አገባህ?!
እባካችሁ ወገኖቼ የክፋት አጀንዳን እንቅበረው። በየእምነታችን አስተምህሮ እንኑር። ጥላቻ አንዳች ትርፍ የለውም። ዘላለም ለማንኖርበት አጭር እድሜ ለወገን የስቃይ ምንጭ አንሁን።
*
መልካም አዲስ ዓመት
Filed in: Amharic