>
9:31 am - Tuesday July 5, 2022

የገሃነም ደጆች አይችሏትም! (ቅዱስ ማህሉ)

የገሃነም ደጆች አይችሏትም!
ቅዱስ ማህሉ

“ቀሲስ በላይ ፕሮቴስታንት ወይም ሙስሊም መሆን ይችላሉ። የጅማ ማርያምን ግን መውሰድ አይችሉም!!!” ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አህመድ ለሲኖዶስ አባላት በጽሕፈት ቤታቸው የተናገሩት ነው። ይህን ከተናገሩ ከሦስት ቀናት በኋላ የጅማ ማርያም ላይ ጥቃት ለማድረስ ሙከራ ተደረገ!!!

 
*በኢሊባቡር ዞን ዲዱ ወረዳ ከሰባ አመት በላይ እድሜ ያለው የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ዮሀንስ ጋዝ እና ክብሪት በያዙ ቄሮዎች ተከቧል!!!

በጅማ የመስከረም 4ቱን ሰልፍ  ለማደናቀፍ ትናንት ዋና አስተባባሪው በፖሊስ ታፍኖ ቢወሰድም በምዕመናኑ ጥረት ፖሊስ ከእስር እንደፈታው ይታወሳል። በዚህ የተበሳጩ የሌላ ዕምነት ተከታዮች ዛሬ የቤተክርስቲያኒቷን መገልገያዎች የሆኑትን መስቀል፣ ፀናፅል፣ ዣንጥላ እና አንዳንድ የቤተክርስቲያን ቁሳቁሶችን በከተማው መሐል ሊያቃጥሉ ሲሉ በጅማ የተዋህዶ ልጆች ከየአቅጣጫው ባደረጉት ርብርብ ድርጊቱን ማክሸፍ ችለዋል። በዚያው በጅማ ቤተክርስቲያንኑም ሊያቃጥሉ ሲሉ በተመሳሳይ ሁኔታ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል። ወጀለኞቹን ፖሊስ ወስዷቸዋል ተብሏል።
ቤተክርስቲያንን የማውደሙም ሆነ የማቃጠሉ ሰይጣናዊ ተግባር ስልጣን ላይ ባሉ ሰዎች ጭምር በቅንጅት እየተካሄደ ለመሆኑ ሌላው ማሳያ፦
በኢሊባቡር ዞን ዲዱ ወረዳ ከሰባ አመት በላይ እድሜ ያለው የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ዮሀንስ ጋዝ እና ክብሪት በያዙ ቄሮዎች ተከቧል። የአካባቢው ህብረተሰብ ብሄርና ሀይማኖት ሳይለይ የድረሱልኝ ጩኸቱን ቢያሰማም አውቆ የተኛው የመንግስት አካል የህብረተሰቡ ዋይታ ችላ ማለቱም ታውቋል። ይህም ማለት ከእንግዲህ ህብረተሰቡ ከመንግስታዊ አካል ጥበቃና ከለላ የማግኘቱ ጉዳይ የማይታሰብ በመሆኑ ሁላችንም በየአካባቢያችን ሁኔታዎችን በንቃት መከታተልና ጥበቃ ማድረግ ይኖርብናል።
 አሁንም መንግስት የሰልፉን ይዘትና አቅጣጫ ለመቀየር የሚያደርገው ሙከራ የማይመዘዝ መዘዝ ይዞበት ይመጣልና ቢያስብበት እና  ከቤተ ክርስቲያናችን ላይ ሳይረፍድ ዛሬውኑ እጁን ቢያነሳ የተሻለ ነው።
 በሃይማኖታችን ጉዳይ እኛ የምንሰማው ብጹአን አባቶቻችንን ብቻ ነው። በሃይማኖታችን እና በቅዱስ ሲኖዶስ አሰራር ላይ እንዳሻኝ ካልፈነጨሁበት በነጻነት አታመልኩም የሚለውን መንግስት ጆሮ አንሰጠውም። ፈጽሞ ልንሰማው አንወድም፤አንፈልግምም! እዚህ ላይ ዶ/ር አክሊሉ ደበላ ያለውን መጥቀስ ያስፈልጋል። “ቤተክርስቲያን የደገፈችውን የመደገፍ ፤ የተቃወመችውን የመቃወም ሃይማኖታዊ ግዴታችን ነው። ይህን አለማድረግ ደግሞ ውርደትም፣ ክህደትም ነው። በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስን አቃሎ የሚመጣን አሠራር መልካም ቢሆንም እንኳ ላለመቀበል ግዴታ አለብን። የቤተክርስቲያን አሰራር ውስጥ እንደፈለኩ ካልገባሁ የሚለውን መንግስት አንሰማውም። እንቃወመዋለን። ቤተ ክርስቲያን በዚህ ምድር የምንታዘዛት የመጨረሻዋ አካል ናት። መሞት ካለብን ስለቤተክርስቲያን መሞትን በደስታ እንቀበላለን። ኖረን ከምናዋርዳት፤ ሞተን ብናስከብራት ይሻላል።” በማለት ዶ/ር አክሊሉ ደበላ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ብጹዕ አቡነ ፋኑኤል “ሕዝባችንን ተነሳ ማለት ከባድ አይደለም። ክርስትያኑን በሜንጫ ነው የምንፈጀው ብለው ሲያውጁ ዝም ያልነው ለፍቅር እና ለሀገር ሰላም ብለን ነው። የክልል ቤተ ክህነት የሚባለው የቤተ ክርስቲያንን ማዕከላዊነት የማፍረስ ሥራ ነው። የቀረችን ይህች ቤተ ክርስትያን ናት። ዝም አንልም!” በማለት  “እኛ ካልገዛናችሁ ትፈርሳላችሁ የምትሉ ሁሉ ተጠንቀቁ!” ብለዋል። ዛሬ ከተሰማው መልካም ዜና ውስጥ ደግሞ “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ” በሚል የኦሮሞ አክራሪ ብሄርተኞችን አጀንዳ ሲያራገብ የነበረው ቡድን አባል የሆነው መምህር ቀለመወርቅ ሚዴቅሳ “የአባቶቼን ምክር እከተለላሁ። የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ አከብራለሁ!” በማለት ራሱን ከኮሚቴው ማግለሉን ይፋ አድርጓል። የመስከረም 4ቱ ሰልፍ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች ስለ ቤተክርስቲያናቸው ድምጻቸውን የሚያሰሙበት ብቻ ነው። ሌላ ምንም ዓይነት እቅድ እና ዓላማ የለውም። ሆኖም ግን በሰልፉ ላይ የሌላን እምነት የሚያንኳስሱ፣ ብሔር ለይተው የሚሳደቡ መፈክሮች ሰልፉን በማይደግፉ የመንግስት ባለስልጣናት ድጋፍ አማካይነት በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራ ይገኛል። በዚህ ረገድ የሰልፉ አስተባባሪዎች የራሳቸውን ጥንቃቄ እየወሰዱ ከመሆኑ ባሻገር ለሕዝበ ክርስትያኑ ጳጉሜ 5 ቀን በሚሰጡት መግለጫ ላይ የጥንቃቄ መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪ በሰልፉ ላይ ብዙ ሰዎች እንዳይገኙ መስከረም 4 ቀን ነዋሪውን በየቀበሌው ለመያዝ የስብሰባው አጀንዳ የማይታወቅ ግን “አበል አለው ዝም ብላችሁ ተገኙ” በሚል ብቻ የቤት ለቤት ቅስቀሳ እየተደረገ ነው። ጥሁፌን ከሰሞኑ ብጹዕ አቡነ ቀውስጦስ ባስተላለፉት መልዕክት ልቋጭ። “በማይለወጥ እምነት እና ተስፋ ከጸናችሁ ዋጋችሁን እከፍላችኋለሁ ያለው እግዚአብሄር ቃሉ አይታበልምና ሃይማኖታችንን እንጠብቅ። ልጆቼ እራሳችሁን እንዳታሰርቁ! ሃይማኖታችሁን ጠብቁ! አደራ! አደራ!
Filed in: Amharic