>
5:13 pm - Wednesday April 19, 8406

የጠ/ሚንስትሩ ሰው ሰው የሚሸቱ አንዳንዴም የሚኮሰኩሱ ሀሳቦች!!! (መስከረም አበራ)

የጠ/ሚንስትሩ ሰው ሰው የሚሸቱ አንዳንዴም የሚኮሰኩሱ ሀሳቦች!!!
መስከረም አበራ
ጠ/ሚ አብይ ከጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ጋር ያደረጉትን ቃለ-ምልልስ አዳመጥኩት፡፡ግሩም ነበር!ጋዜጠኛዋ ወ/ሮ መዓዛ ብሩ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች እንደተለመደው በሳል እና ሰፋ አድርጎ ለመናገር የሚመቹ እና የሚጋብዙ ነበሩ፡፡ከጠ/ሚው ተፈጥሮ የምወድላቸው ለህዝብ ቀረብ የማለት ሰዋዊነት ለጠያቆ ጋዜጠኛም ምቾት መስጠቱ አይቀርም፡፡”መደብ ላይ እየተኛሁ፣ኩራዝ የሚበራበት ቤት ውስጥ ያደግኩ ነኝ” ሲሉ አድማጭ ከእኛ እንደ አንዱ እንጅ ከሰማይ ዱብ ብለው ዙፋን ላይ ያረፉ አለመሆናውን ይረዳል፤ይህ አይነቱ ሰው ሰው የሚል ነገር ከመሪ አንደበት ሲወጣ አንዳች ህዝብን እና መሪን የሚያቀራርብ መስህብ አለው፡፡የቀድሞው ጠ/ሚ ከሰው ይልቅ ለእግዜር የመቅረብ ሁኔታ ከእለታት አንድ ቀን ለጥያቄ ፊታቸው የሚኮለኮሉ ጋዜጠኞችን እጅ ሲያንቀጠቅጥ፣ቃላትን ሲሰባብር፣ትንፋሽ ሲቆራርጥ ተመልክቼ አውቃለሁና ጠ/ሚ አብይ ከጋዜጠኛ ጋር ሲገናኙ የሚያሳዩት ሰዋዊ ትህትና ከትልቅነት የምመዘግብላቸው ማንነታቸው ነው፡፡
ከሸገር ጋር በነበራቸው ረዘም ያለ ቆይታ ካነሷቸው ሃሳቦች የመደመር ፍልስፍናቸውን በተመለከተ ያቀረቡት ሃተታ በዚሁ ፍልስፍና ዙሪያ የነበረኝን ግርታ በመጠኑ ያቃለለ ነው፡፡ መደመር የሚለው አመት ሙሉ ሾላ በድፍን ሆኖ የኖረ ነገር መፍታታቱ ደግ ነው፡፡  በፍልስፍናው ዙሪያ ይታተማል ያሉትን መፅሃፍ ለማንበብም ጉጉ ነኝ፡፡ በመደመር ፍልስፍናቸው ውስጥ ትብብር እና ውድድርን እንዴት አብሮ ማስኬድ እንደሚቻል በአዞው እና በወፏ መስለው ያነሱትን ጭብጥ የበለጠ ወድጄዋለሁ፡፡የተጠናወተን በሁሉነገር በብሄረሰባችን አንፃር የመወዳደር አባዜ በቀላሉ ይለቀናል ብየ ለመገመት ቢቸግረኝም ይህ ፍልስፍና ሲብራራ፣መፅሃፍ ሆኖ ሲመጣ የሚያቀለው ችግር ቀላል አይሆንም፡፡ ከሁሉም በላይ ከባህር ማዶ ፍልስፍና “shop” ለማድረግ ዘምቢል ይዘን ከምንባዝን እንደ ሁኔታችን፣በችግራችን ልክ እና ተፈጥሮ በተሰፋ ሃገር በቀል ፍልስፍና ደግሞ ከፖለቲካችን ደዌ የምንፈወስ ከሆነ መሞከሩ አይከፋም፡፡
የሃገሪቱ ጠ/ሚ በመሆናቸው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚሰሩ፣ኦሮሞም ለብቻው በተለየ ሁኔታ እንዳይጎዳ እንደታገሉ፣በተለየ ሁኔታ እንዲጠቀምም እንደማይሰሩ የተናገሩት ንግግር ለጆሮ ቢጥምም በተግባር ከሚታየው ጋር ግን አይገጥምም፡፡ ሊቀመንበር ሆነው የሚመሩት ፓርቲ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም ይገባኛል፤ልዩ ጥቅሜ ደግሞ አዲስ አበባን ፊንፊኔ ብሎ የኦሮሞ ግዛት ማድረግ ነው ሲል ልዩ ጥቅም ከማለት አልፎ ጠቅልሎ የመውሰድ ትግል እንደሚያደርግ መግለጫ አውጥቶ በታከለ ዑማ በኩል ከሚያደርገው ርብርብ ጋር አይገጥምም፡፡እንደ እኔ ላለ ቃል ከተግባር ጋር ማመሳከር ለሚወድ ዜጋ ይህች ንግግር መኮስኮሷ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከአብይ አለፍ ብሎ ኦህዴድ ላይ ትኩረት ማድረጉ ደግ እንደሆነ አውቃለሁና ጠ/ሚውን በግል ልከሳቸው አልሻም፡፡ ለምን ቢባል ኦህዴድ ውስጥ ያለው የኦነግ መንፈስ፣በአጠቃላይ በኦሮሞ ብሄርተኛው ጎራ ያለው የማይጠረቃ የኬኛ ጥያቄ፣የኦህዴድም ከዚህ የማይጠረቃ ጥያቄ አለመዋጀት ጠ/ሚው የሚፈልጉትን ብቻ ሳይሆን የማይፈልጉትን የመናገር የመስራት ውድድር ውስጥ እንደሚከታቸው አላጣውም፡፡ ዋናው ለጥያቄ ግን አስከመቼ እንዲህ ሆነው ይዘልቁታል የሚለው ነው!
ጠ/ሚው ሃገራቸውን የሚወዱበትን ውድ የገለፁበት መንገድ ልቤን ነክቶታል፡፡ኢትዮጵያን በጣም ከሚወዱ ዜጎች አንዱ እንደሆኑ ገልፀው ስለ ኢትዮጵያ ሲሆን እንደሌላ ጊዜ ጠንከር ብሎ መቆም እስኪቸግራቸው ድረስ ስለኢትዮጵያ ሲሆን ስስ እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡ እንዲህ ሲሉ እኔን እኔን መስለውኝ ነው መሰለኝ ምን እያሉ እንደሆነ በደንብ ተረድቻለሁ! እንዲህ የሚል ጠ/ሚ በማኘታችንም ደስተኛ ነኝ፡፡ ይህን ያሉት አብይ ነገ ሌላ ጥፋት ሊያጠፉ ይችላሉ ግን ከዚህ ኢትዮጵያን ከመውደዳቸው ከፍታ እስካልወረዱ ድረስ ከነቃርሚያው ተስፋ እንዳደርግ ያደርጉኛል፡፡

ባለቤታቸውን ከእናታቸው ጋር እያናፀሩ የገለፁበት መንገድ፣በተለይ ቀዳማዊት እመቤቷ በመጠን መኖርን የሚውቁ ቀጥብ ግን ደግሞ ሃይለኛ ሴት መሆናቸውን የገለፁበት መንገድ ወ/ሮ ዝናሽ “Shopping” ከሚያበዙ የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች ወገን አለመሆናቸውን ያሳያል፤ይህም መልካም ነው! ሃይለኝነቱም አይጠላም፤ሴት ሃይለኛ ካልሆነች ይህን የወንድ አለም እንዴት ትዘልቀዋለች? በስተመጨረሻም ጠ/ሚው ለጥበብ ቀረብ ያለች ነፍስ እንዳለቻቸው የግጥም አብዝተው እንደሚወዱ የሚያደንቋቸውን ገጣሚያንን በመዘርዘር ተናግረዋል፡፡ ጥበብን መውደድ ሃገርን የመረዳት መንገድ ነው-በጥበብ በር ገብቶ የማይፈተሸ የህይወት ገፅ የለምና! 

!
Filed in: Amharic