>

የአንዳርጋቸው ጽጌ ነገር...   (አቻምየለህ ታምሩ)

የአንዳርጋቸው ጽጌ ነገር…
  አቻምየለህ ታምሩ
አንዳርጋቸው ጽጌ ኖርዎይ ኦስሎ ተገኝቶ ባሰማው ዲስኩር የመጽሐፉን መውጣት  ተከትሎ ከተዥጎደጎደበት  ከዚያ ሁሉ ትችት በኋላም ሲባል የሰማውን ዝባዝንኬ ከመድገም ባሻገር በምሁር ዓይን ለመመርመርና ከፍ ለማድረግ አእምሮውን ዝግጁ ያልሆነ ሰው መሆኑን በድጋሜ አስመስክሯል።
በድንጋይ ላይ ተጽፏል ያለውን «ማስረጃ» በማውሳት የበጌምድርን ታሪክ ሲያቀርብ «[አክሱማውያን ነገሥታት ከአክሱም] ወደታች ወርደው ዛሬ በጌምድር የምንለውን ያን ጊዜ የቤጃ ምድር የሚባለውንና የቤጃ ቋንቋ የሚናገረውን [ነገድ] አስገብረነዋል ብለዋል» በማለት በድፍረት ተናግሯል።
ይህንን የአንዳርጋቸውን ንግግር ይዛችሁ በአክሱም ዘመን የተጻፉትን የድንጋይ ላይ ጽሑፎች ብታገላብጡ አንድም የአክሱም ንጉሥ «የቤጃ ምድርን አስገበርሁ» ብሎ ያስቀረው የድንጋይ ላይ ጽሑፍ አታገኙም። በአክሱሞቹ  ነገሥታት በዐፄ ኢዛናም ሆነ በዐፄ ካሌብ የድንጋይ ላይ ጽሑፍ የምታገኙት «ቤጃ» የሚባል  ነገድን እንዲ የቤጃ ምድር የሚል ቦታ ተጠቅሶ አታገኙም።   በዐፄ ኢዛና የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ንጉሡ «ቤጃ» የተባለን ነገድ ወግተው እንዳስገበሩ እንጂ «ቤጃ ምድር» የተባለን ቦታ እንዳስገበሩ አልተጻፈም። [ምንጭ፡ Munro-Hay, S. C., & Munro-Hay, S. C. (1991). Aksum: an African civilisation of late antiquity. Edinburgh: Edinburgh University Press; Page 189]
በዐፄ ካሌብ የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ደግሞ «ቤጃ» ተጠቅሶ የምናገኘው ንጉሡ ከወጓቸው ወይም ካስገበሯቸው ነገዶች መካከል ሳይሆን የንጉሡ ማዕረግ ሙሉው ሲጻፍ ከተዘረዘሩት የነገድ ስሞች ተርታ ነው። ከዐፄ ካሌብ የድንጋይ ላይ ጽሑፍ የተገለበጠውና ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመው  የንጉሡ ሙሉ መጠሪያ የሚከተለውን ይመስላል፤
“Aeizanas, king of the Aksumites, the Himyarites,
Raeidan, the Ethiopians, the Sabaeans, Silei (Salhen), Tiyamo, the Beja, and Kasou, king of kings, son of the unconquered Ares”  [ ምንጭ፡ Ibid; Page 132]
ከነዚህ ከሁለቱ የድንጋ ላይ ጽሑፎች ውጭ ስለ ቤጃ የተጻፈበት የአክሱም ዘመን የድንጋይ ላይ ጽሑፍ የለም። አንዳርጋቸው በድፍረት የአክሱም ነገሥታ «የቤጃ ምድርን አስገበርን» ብለው በድንጋይ ላይ ጽፈዋል ያለውን በበሬ ወለደ ነው። በአክሱም ዘመን የተካሄደን ዘመቻ ተከትሎ ከተጻፈ የድንጋይ ላይ ማስረጃ የምናገኘው ጽሑፍ «የቤጃን ነገድ ወጋሁ» የሚለው የኢዛናን የድንጋይ ላይ ጽሑፍ እንጂ አንዳርጋቸው የነገረንን «የቤጃ ምድር አስገበርሁ» የሚል የድንጋይ ላይ ጽሑፍ አናገኝም።
ኢዛና ወጋሁት ያለው የቤጃ ነገድም መገኛው የት እንደሆነ በድንጋይ ላይ ጽሑጹ ተቀምጧል። ኢዛና ወጋሁት ያለው የቤጃ ነገድ መኖሪያው አንዳርጋቸው ፈጥሮ ሊነግረን እንደፈለገው በጌምድር ውስጥ ሳይሆን በቀይ ባሕር ደሴቶች ውስጥ ነው። የኢዛና የድንጋይ ላይ ጽሑፉ የቤጃችን መገኛ «…The Beja are the tribes of the Red Sea hills,..» በማለት ይገልጸዋል። [ ምንጭ፡ Ibid; Page 134]
የዘመኑ የአረብ ተጓዦችም ቤጃ ሓጀር  [Beja Land]  ብለው የሚጠሩት አንዳርጋቸው እንደሳተው በጌምድርን ሳይሆ የRed Sea hillsን እንደሆነ ይህ ተመሳሳይ ምንጭ  መዝግቦት እናገኘዋለን። [ ምንጭ፡ Ibid; Page 12]
በድንጋይ ላይ ተመዝግቦ የምናገኘው የአክሱም ዘመን ታሪክ ይህ ብቻ ሆኖ ነው እንግዲህ አንዳርጋቸው ጽጌ  በጌምድርን ቤጃ ምድር አድርጎ  በበሬ ወለደ ተረት ታሪኩን እንዳሻው ሊቀይረው የፈለገው። አንዳርጋቸው በኦስሎው ዲስኩሩ «በጌምድር የቤጃ ምድር ማለት ነው፤ የቤጃ ቋንቋ የሚናገሩ የቤጃዎች ምድር ማለት ነው» ሲል ከተናገረው «ቤጃ ምድር» የሚለው የቦታ ስም ቤጃኛ ሳይሆን አማርኛ እንደሆነ እንኳ ማስተዋል አልቻለም። በጌምድር ቤጃ ምድር ማለት ከሆነና ግዛቱ የቤጃ ቋንቋ የሚነገርበት ምድር ከነበር የቦታው ስያሜ  በቤጃ ቋንቋ  እንጂ «ቤጃ ምድር» የሚል አማርኛ አጠራር ሊኖረው አይችልም።
በጌምድር የሚለው የቦታ ስሜን እውነት አንዳርጋቸው ጽጌ ሊነግረን እንደፈለገው የቤጃ ምድር ማለት ነውን? ይህን ጥያቄ ለመመለስ እንደ አንዳርጋቸው ጽጌ የኢሕአፓንና የሕወሓትን ፕሮፓጋንዳ መድገም ሳይሆን የታሪክ ማስረጃዎችን ማገላበጥ ይጠይቃል። በጌምድርን ምን ማለት እንደሆነ ማብራሪያ ከሰጡና ቆየት ካሉ የተመዘገቡ የታሪክ ማስረዎች መካከል በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የጎንደር ከተማ ከመቆርቆሯ በፊት ኢትዮጵያን የጎበኘው ፖርቲጋላዊው ሚሲዮን Jerónimo Lobo የጻፈውን ታሪክ እናገኛለን።
ሚሲዮኑ Jerónimo Lobo የኢትዮጵያ ጉብኝቱን አስመልክቶ እ.ኤ.አ. በ1622 ያሳተመው መጽሐፍ “Voyage historique d’Abissinie” የሚል ሲሆን ይህንን በፈረንሳይኛ ቋንቋ የተጻፈ የJerónimo Lobo ማስታወሻ ሳሙኤል ጆንሰን እ.ኤ.አ. በ1803 ዓ.ም. «A Voyage to Abyssinia» በሚል ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተርጉሞታል። Jerónimo Lobo በኢትዮጵያ ቆይታ ማስታወሻው ስለጎበኛቸው የአባይ ተፋፈስ አካባቢዎች ሲገልጽ ስለ በጌምድርና ትርጉሙ እንዲህ ይለናል . . .
«Here the river alters its course, and passes through many various kingdoms; on the east it leaves Begmeder, or the Land of Sheep, so called from great numbers that are bred there, beg, in that language, signifying sheep, and meder, a country»
[ ምንጭ፡ Lobo, J. (1622). A voyage to Abyssinia. A. Bettesworth, and C. Hitch. Pages: 140-41]
ይህ የጎንደር ከተማ ከመቆርቆሯ በፊት የተጻፈው የJerónimo Lobo የ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማስታወሻ እንደሚያሳየን አካባቢው  «በጌምድር» የተባለው የበግ ሀብት በብዛት ይረባበት ስለነበር እንጂ አንዳርጋቸው ጽጌ ሊነግረን እንደፈለገው የቤጃ ምድር ስለሆነ አይደለም። Jerónimo Lobo ጨምሮ እንደነረን በጌምድር የሚለው የቦታ ስም በግና ምድር ከሚሉ ሁለት «የቦታው ቋንቋ» ቃላት እንደተዋቀረና ትርጉሙም የበግ ምድር ማለት ነው ሲል ከነገረን በጌምድር የሚለው ስም በግና ምድር ከሚሉት ቃላት ሊፈጠር የሚችለው የቦታው ቋንቋ አማርኛ ብቻ ነው። በሌላ አነጋገ በጌምድር አማርኛ የሚነገርበት እንጂ አንዳርጋቸው ሊነግረን እንደፈለገው ያገሩ ቋንቋ የቤጃ ቋንቋ እንዳልነበረ ነው።
በጨረሻም አንዳርጋቸው ጽጌ አማራ  በአክሱም ዘመን እንደ ማኅበረሰብ አይኖርም ነገር ስላለው ተደጋጋሚ አላዋቂነት ኢኔርኮ ቸሪሊ በአክሱም ዘመን ኢትዮጵያን የጎበኙ የአረብ ተጓዦችን ማስታወሻ ተርጉሞ እ.ኤ.አ. በ1931 ዓ.ም. “Documenti arabi per la storia dell’ Etiopia” በሚል ባሳተመው መጽሐፍ ውስጥ ገጽ 209 ላይ «በየካቲት ወር 522 ዓ.ም. አማራዎች በወርጂዎች አገር ላይ ጥቃፈጽመው ተመለሱ» በሚል ያቀረበውን  ታሪክ ያንብበው እላለሁ። አማራ በአክሱም ዘመን እንደ ማኅበረስብ ካልነበረ  የአረቡ ጎብኚ በአክሱም ዘመን አ እ.ኤ.አ. በ522 ዓ.ም. በጻፈው  የጉዞ ማስታወሻ «በየካቲት ወር 522 ዓ.ም. አማራዎች በወርጂዎች አገር ላይ ጥቃፈጽመው ተመለሱ» ብሎ  የዓይን ምስክርነት ሊሰጥ አይችልም።
አንዳርጋቸው እንደ ነገድ ሊቆጥራቸው ከፈለጋቸው መካከል ለምሳሌ ኦሮሞዎች ብንወስድ ግን አይደልም በአክሱም ዘመን እ.ኤ.አ. በ522 ዓ.ም.  አማራ በአክሱም አመን መመኖሩ ከተመዘገበ ከአንድ ሺህ ዓመታት በኋላም  ዛሬ ኦሮሞ የተባሉት በገዳ ስርዓት እየተመሩ እ.ኤ.አ. በ1522 ዓ.ም. ወረራ ሲጀምሩ በረይቱም እና ቦረን የሚባሉ ሁለት ነገዶች ነበሩ እንጂ እንደዛሬው ኦሮሞ የሚባል የአንድ ነገድ አካእ አልነበሩም። [ምንጭ፡ ጌታቸው ኃይሌ (1995)፥ የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፤ ኦሮሞዎችን ከሚመለከቱ ሌሎች ሰነዶች ጋር፥ ገጽ 76]
እንግዲህ! አንዳርጋቸው ጽጌ ሲባል የሰማውን ዝባዝንኬ ከመድገም ባሻገር በምሁር ዓይን ለመመርመርና ከፍ ለማድረግ ያልሞከረው የግራ ፖለቲካ ትርክት ሲመረመር እውነቱ ከፍ ብሎ የቀረበውን ይመስላል። አንዳርጋቸው Challenge የማይደረግበትን መድረክ እየመረጠ የቀድሞ አለቆቹ ኢሕአፓና ሕወሓት ያራገፉበትን ዝባዝንኬ እየደገመ የኛንም ጊዜ እያባከነ ይገኛል 🙂
ወዳጄ ቴዎድሮስ ጸጋዬ አንዳርጋቸውን  በመጽሐፉ ዙሪያ ለቃለ መጠይቅ ጋብዞት ነበር። ሆኖም ግን የርዕዮት መድረክ እንደ ኢሳት «በዚህ ሳምንት» ፕሮግራም ሳይሞገት አፉ ያመጣለትን እየደገመ የሚፏልልበት መድረክ እንዳልሆነ ስለሚያውቅ አራዳው  አንዲ ከቴዲ ጋር ቃለ ምልልስ ለማድረግ ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። እንደሚለው ከካድሬያዊ አፍነጠቅነት የዘለለ በንባብ የተገነባ የታሪክ እውቀት ካለ ከማንኛውም ሰው ጋር ለመከራከርና ለቃለ ምልልስ ዝግጅት ይሆን ነበር እንጅ የማይሞገትበትን መድረግ እየመረጠ ያሻውን ለመናገር አይገኝም ነበር። አንዳርጋቸው በማይተችበት መድረክ ቀርቦ የጻፈውን ዝባዝንኬና የፈጠራ ታሪክ የተቹትን ሰዎች ለመዝለፍ ሞክሯል። ሆኖምን ግን  ለቃለ ምልልስ ብቻ ሳይሆን መጽሐፉን ከተቹት ሰዎች ጋርም ፊት ለፊት ቀርቦ በደረተው መጽሐፍ ዙሪያ ለመከራከር ዝግጁ አይደለም።
በአንዳርጋቸው መጽሐፍ ላይ ትችት ካቀረቡ ሰዎች መካከል አንዱ እኔ ነኝ። በተናገራቸው የተሳሳቱ ታሪኮች ዙሪያ ካቀረብሁበት ትችቶች አንጻር መከላከል የሚችል ቢሆን በማንኛውም ጊዜ፣ እሱ በመረጠው መድረክ፣ ቢፈልግ በኢሳት ጭምር ከሱ ጋር ለመከራከር ዝግጁ መሆኔን ለመግለጽ እወዳለሁ። አንዳርጋቸው ደፍሮ ለሙግት ዝግጁ ቢሆን እኔም በአርቲክል መልክና  በርዕዮት ሬዲዮ ከጊዜ አኳያ ያላቀረብኋቸውን ተጨማሪ ትችቶ እንዲሁም መጽሐፉ ውስጥ  እንደታሪክ ያጨቃቸውን ያላጋለጥኋቸው ፈጠራዎችና የያ ትውልድ የውሸት ታሪኮች ከተመዘገቡ የታሪክ ማስረጃዎች አኳያ  በመመርመር እውነታው ምን እንደሚመስል የሚያሳዩ ዶሴዎች ይዤ የምቀርብበትን እድል አገኛለሁ 🙂
Filed in: Amharic