>
3:03 am - Monday July 4, 2022

ግልፅ እና አጭር ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ! (አናንያ ሶሪ ጉታ)

ግልፅ እና አጭር ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ!
አናንያ ሶሪ ጉታ
በሰላምታ እና በመግቢያ ሀተታ ራሴንም፣ አድማጭንም፣ እርስዎንም ማድከም አልሻ! ሰላምን እና መልካም ነገርን ሁሉ ግን፤ ለሰው ልጆች በመላ ለእርስዎም ጭምር እመኛለሁ! የለውጥ ማሻሻያ ጅምርዎን በተስፋ እና በጉጉት ስንመለከት ለነበርን ብዙዎች፤ በአሁኑ ወቅት እየተካሄዱ ያሉ አፍራሽና አፋኝ አዝማሚያዎች በእጅጉ ያሳዝኑናል!
እንደ ንቁ ዜጋ እና የጋዜጠኝነት መስክ ተዋናይ፦ ውስብስቦቹን እና የተለያዩ የፖለቲካ ልሂቃንን እውነተኛ ንግግርና ድርድር የሚጠይቁ ወሳኝ ጉዳዮችን ወደጎን ብንተው እንኳ፤ ቢያንስ “ሃሳብን ያለ እግድ በነፃነት በመግለጥ” መብትና ልምምድ ዙርያ እንደአገር ከፍተኛ እርምጃ እናሳያለን ብለን በእርግጠኝነት መንፈስ ጠብቀናል! ሆኖም ግን፦ ዛሬም ከውዳሴ እና የገደል ማሚቶነት ሚና ያልራቁ የሚድያ አካሄዶች፤ የመሪዎችን ግለ-ምልከታ (Self image) ብሎም ተክለ-ስብዕና አለቅጥ በማግነን እያገዘፉ፤ አንድን የህዝብ ስልጣን የተቆናጠጠ መሪ “ልዕለ-ሰብ” (Super Human) የሆነ እንዲመስለውና፤ ትችትን ባግባቡ እንዳይቀበል የሚያደርጉ አሉታዊ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛሉ!
በዚህም የተነሳ፦ ከአድናቆት ቃል በቀር የተለዩ ድምፆችን መስማት የማይፈልጉ “የለውጥ አመራር” ባለሟሎች፤ እንዲህ ያሉ ትችት-አዘል አስተያየቶችን የሚሰጡ ዜጎችን ወደእስር ግዞት በመስደድ ላይ ይገኛሉ!ከእነዚህም ሰለባዎች ውስጥ አንዱ እና ግንባር ቀደሙ፤ ጋዜጠኛና የመብት ተሟጋች ኤልያስ ገብሩ ጎዳና ነው!
በእርስዎ ጊዜያዊ አስተዳደር እና የለውጥ ሽግግር አካሄድ ዙርያ በሰነዘረው አስተያየት ምክንያት ብቻ፤ እንደወንጀለኛ ተቆጥሮ ያላንዳች ጥፋት በእስር በመማቀቅ ላይ ይገኛል! በድህረ-ወያኔ/ኢህአዴግ ዘመን፣ ስለ”ለውጥ” ብዙ በተነገረበት እና ህዝቡም በተስፋ በተሞላበት በዚህ ወቅት ይህ መደገሙም የክፍለ-ዘመኑ ታላቅ ምፀት ያደርገዋል! ምናልባት እርስዎ ይህን ጉዳይ አልሰሙ እንደሆነ፤ ክቡርነትዎ ይህንኑ ተመልክተው ፍትሃዊ የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ ስል በአክብሮት እና በወንድማዊ ተግሳፅ እጠይቃለሁ!
ለአገራችን ፖለቲካዊ ባህል ፍፁም አዲስ እና ገንቢ የሆነ “በጋራ ሁላችንም እናሸንፍ” ፣ “ማሰር መግደል ኋላቀር የሽንፈት መንገድ ነው” የሚል ብሩህ ፅንሰ-ሃሳብን ይዘው ተነስተው ሲያበቁ፤ ዛሬ ላይ የድሮው ዘመን ግርሻ የሆኑ የሰቆቃ እና ንፁሃንን ከህግ ውጪ የማጋዝ እኩይ ተግባራት፤ ከትናንቱ ማዕከላዊ እስር ቤት ጎን ባለ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቅፅር ግቢ ውስጥ መከናወኑ እጅግ አሳዛኝም አስገራሚም ነው! ጉብኝቱም ጨዋታ ይመስላል ።
የሆነ ሆኖ፦ የቆየ ልማድ ወዲያዉኑ ለቆ እንደማይሄድ የታወቀ እና የታመነ ሆኖ እንዳለ፤ ከድጋሚ ጥፋቱ ይልቅ የድጋሚ እርምቱ ዋጋ በእጅጉ አገራዊ ፋይዳ አለውና፤ በዚሁ መሰረት ያለጥፋቱ በከንቱ የሚጉላላውን የስራ ባልደረባዬ ኤልያስ ገብሩን ይፍቱ ስል በአፅንዖት አሳስባለሁ!
 
* የምጠራው መንጋ የሌለኝ ግለሰብ እና ነፃ ዜጋ!
ከአክብሮት ጋር!
Filed in: Amharic