>

የጉድ ሀገር ጉድ ሲጋለጥ! "በግሉ እስር ቤት አለው" ተብሎ በ43 ክሶች የታሰረው ባለሃብት!  (ስዩም ተሾመ)

የጉድ ሀገር ጉድ ሲጋለጥ! “በግሉ እስር ቤት አለው” ተብሎ በ43 ክሶች የታሰረው ባለሃብት! 
ስዩም ተሾመ
” ይሄን ሁሉ መከራና ፍዳ አይቼ በዋስ ከተፈታሁ በኋላ እንኳን በሀገሬ በሰላም መኖር አልቻልኩም!!!”
በግል መኖሪያ ቤቱ ውስጥ “የማሰቃያ እስር ቤት አለው” ተብሎ የተከሰሰውን ባለሃብት አስታወሳችሁት? ያ….እንኳን ሐምሌ 13/2009 ዓ.ም ጠዋት ላይ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት (#FBC) “ለብዙ ወጣት ባለሃብቶች የአራጣ ብድር በመስጠት ለከፋ ድህነትና ችግር ዳርጓቸዋል” የተባለውና ከሰዓት በኋላ በቁጥጥር ስር የዋለው ሰውዬ ትዝ አይላችሁም። ከአምስት ቀናት በኋላ ሐምሌ 18/2009 ዓ.ም ፋና በድጋሜ በመኖሪያ ቤቱ እስር ቤት አለው፣ #አዲስ_ቪው በተባለው ሆቴል ምድር ቤት ላይ የማሰቃያ እስር ቤት አለው፣ በመሬት ወረራ ተወዳዳሪ የለውም፣ በጋዜጠኞችና ምስክሮች ላይ እያደረሰ ያለው ማስፈራራት ታይቶ አይታወቅም፣… ወዘተ የተባለው ባለሃብት፤ የአዲስ አበባ ነዋሪ “አቤት ጉድ” ብሎ ዝም ያለው ግለሰብ። ይሄ ሁሉ የወንጀል ፍረጃ በዋናነት በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ሌሎች ደግሞ ይሄንኑ ዘገባ በመቀባበል የዘገቡት ገና ግለሰቡ ፍርድ ቤት ቀርቦ ክስ ሳይከሰስ ነበር። አሁን እነዚህን ዘገባዎች በየትኛውም የፋና ድረገፆች ላይ አታገኙትም። ምክንያቱም ተበዳይ ነን ያሉ በዳዮች፣ ዘጋቢ ሚዲያዎች፣ መርማሪ ፖሊሶች እና ከሳሽ አቃቢ ህግ በአንድ ግለሰብ ላይ ተባብረው የፈፀሙት ግፍና በደል እንደሆነ ስለሚያውቁ ሁሉንም ዘገባዎች አጥፍተዋቸዋል።
ግለሰቡ አቶ አብይ አበራ ይባላሉ። ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ከፍተኛ የስም ማጥፋት ከተፈፀመባቸው በኋላ መጀመሪያ ላይ በ3 ክሶች፣ ከዚያ በመቀጠል በ38 ክሶች፣ በመጨረሻ እስር ቤት እያሉ በ3 ክሶች፣ በጠቅላላ በ43 ክሶች ተከስሰው ለአንድ አመት ያህል በቂሊንጦ እስር ቤት ቆይተዋል። በወቅቱ የፍርድ ሂደቱን በአግባቡ የዘገበው ሪፖርተር ጋዜጣ የየፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሐሙስ ጳጉሜን 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ተረኛ ችሎት በአቶ አብይ አበራ ላይ ያቀረበው 38 ክሶች፤ 3 አራጣ ማበደር፣ 2 የባንክን ሥራ ተክቶ መሥራት፣ 4 በሕገወጥ የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስስሎ ማቅረብ፣ 4 ከፍተኛ የማታለል፣ 6 በሕገወጥ መንገድ ኢትዮጵያውያንን ወደ ውጭ መላክ፣ 5 ግብር አለመክፈል፣ 7 የተሳሳቱና ሐሰተኛ ሰነዶችን ማቅረብ፣ 4 ተጨማሪ እሴት ታክስ አለመክፈል እና 3 ከባድ የማታለል ወንጀሎችን መፈጸማቸውን አብራርቷል፡፡ ከ43ቱ ክሶች ውስጥ በግለሰብ ደረጃ በአቶ አብይ የቀረቡት 29 ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ከሌሎች ሰዎችና ድርጅቶች ጋር በተያያዘ ነበር።
አቶ አብይ አበራን ለዚሁ ግፍ የተዳረጉበት ምክንያት ዝርዝሩ ብዙ ነው። ዋናው ምክንያት ግን በወቅቱ የፌደራል ዋና አቃቤ ህግ የነበሩን አቶ ጌታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ጭምር ደብዳቤ በመፃፍ ስለ ከሰሷቸው ነው። አቶ ጌታቸው አምባዬ ከኃላፊነታቸው ከተነሱ በኋላ ግን ፍርድ ቤቱ በግለሰብ ደረጃ በአቶ አብይ ላይ ከተመሰረቱት 29 ክሶች ውስጥ 22ቱን ውድቅ በማድረግ በ5 ሚሊዮን ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ብይን ይሰጣል። ይሄን ሁሉ መከራና ፍዳ አይቼ በዋስ ከተፈታሁ በኋላ እንኳን በሀገሬ በሰላም መኖር አልቻልኩም” እያሉ ነው። እኔም የነፃ ወይይት ፕሮግራም ላይ እንግዳ አድርጌ በመጋበዝ ትላንት ያለፉበትን፣ ዛሬ ላይ ያሉበትንና የወደፊት ስጋታቸውን የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሰምቶ ይፈርዳቸው ዘንድ እንሆ ብያለሁ። ሙሉ ውይይቱን ለመመልከት ይሄን ሊንክ ይጫኑ:-
Filed in: Amharic