>

ለመሆኑ በቀለ ገርባ ጻፍኩት የሚለው  ሕገ መንግሥት ምን እንደሚል ያውቃል?  (አቻምየለህ ታምሩ)

ለመሆኑ በቀለ ገርባ ጻፍኩት የሚለው  ሕገ መንግሥት ምን እንደሚል ያውቃል? 
አቻምየለህ ታምሩ
በቀለ ገርባ «የአዲስ አበባ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ  የመወሰን መብት የለውም» ብሎ የሰዎችን መብት ሲደመስስ የጣሰው ጻፍሑት የሚለውን ሕገ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የተፈራረመቻቸውን የዓለም አቀፍ ሕጎችን ሁሉ ነው!
በቀለ ገርባ ገራሚ ፍጡር ነው። ወጥቶ በተናገረ ቁጥር  ሲዘባርቅ ሌላው ቢቀር  ጻፍሑት የሚለው ሕገ መንግሥት ተብዮ ደንብ  እንኳ  ምን እንደሚል   አለማወቁ አያሳፍረውም። ጻፍሑት የሚለው ሕገ መንግሥት ምን እንደሚል አለማወቁን ለማሳየት  በትናንትናው ክርክር የአዲስ አበባን ሕዝብ መብት  ለመግፈፍ  ካቀረባቸው የሀፍረት መከራከሪያዎች አንዱን በአስረጅነት ወስደን እንመልከት።
በቀለ ትናንትና ከእስክንድር ጋር በናሑ ቴሌቭዥን  ባደረገው ክርክር «የአዲስ አበባ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ  የመወሰን መብት የለውም» ብሎ በድፍረትተከራከረ። ለዲሞክራሲ እታገላለሁ እያለ ለሱ የሚገባውን መብት ለሌላው ሲሆን ግን  የሚገፍ  የማውቀው ፍጡር ቢኖር  በቀለ ገርባ ብቻ ነው።
በቀለ የአዲስ አበባን  ሕዝብ የራስን  እድል በራሱ የመወሰን መብት ሲገፍ ያቀረበው  የድፍረት መከራከሪያ «የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት  ለብሔሮች ብቻ የተሰጠው መብት ነው» የሚል ሰበብ ነበር። በቀለ «የራስን እድል በራስ የመወሰን ለብሔሮች ብቻ የተሰጠ መብት ነው» ብሎ ሽንጡን ገትሮ  ሲከራከር  «የኦሮሞን መብትና ጥቅም የምናስከብረው  የሌላውን መብትና ጥቅም በመንጠቅ ነው የሚለውን» የሚለውን የኦሮሞ ብሔርተኞች የጋራ እምነት መከተሉን እንጂ  ጻፍሑት የሚለው ሕገ መንግሥት ተብዮ ደንብ በአንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ  ያሰፈረውን «መብት» እየሻረ መሆኑ  አልታየውም። ለነገሩ እነ በቀለ ጻፍነው የሚሉንን ሕገ መንግሥት  እንድናከበር የተፈረደብን እኛ ብቻ  እንጂ  ደንቡን የማክበር ያለማክበር ጉዳይ እነ በቀለን አይመለከትም።
«የመብት ተሟጋቹ»  በቀለ ገርባ ለአዲስ አበባ ሕዝብ የነፈገው መብት አንዱን የሕገ መንግሥት ተብዮ አንቀጽ ብቻ ሳይሆን ሙሉውን ጻፍሑት ያለውን ሕገ መንግሥት ጭምር ነው። በበቀለ እሳቤ  በአዲስ አበባ ውስጥ  እንዲተረጎም የሚፈቅደው «የሕገ  መንግሥቱ»  አንቀጽ  ለአዲስ አበባ ሕዝብ የታወቁት መብቶች ሳይሆኑ «ኦሮምያ» በአዲስ አበባ ላይ ያላትን  ልዩ ጥቅም የሚደነግገውን አንቀጽ ብቻ ነው።
በቀለ ገርባ ጻፍሑት ያለው ሕገ መንግሥት «የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት»  በቀለ እንደሚለው «ብሔር» ብቻ  ብሎ አያቆምም። በቀለ ጻፍሑት የሚለው ሕገ መንግሥት «የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት የብሔር፣ ብሔረሰብና፣ ሕዝብ ነው» ይላል። ይህ  ማለት «የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት» የቁጥር ገደብ ስለሌለው አምስት ጎረቤቶችም ቢሆኑ  ተሰብስበው ከሶስቱ አሀዶች  አንዱን መርጠው  «የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት» ጥያቄ ሊነሱ ይችላል።
በቀለ ጻፍሑት ወደሚለው ሕገ መንግሥጥ ስንመጣ «የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት» የነማን  መብት እንደሆነ  በቀለ የጻፈው ሕገ መንግሥት  በአንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 የሚከተለውን ይለናል፤
«አንቀጽ 39 – የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች መብት፡ 
 
ንዑስ አንቀጽ 1፡ ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ፣ ብሔረሰብ ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው።»
 
ምንጭ: የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት፥ ፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ፥  አንደኛ አመት፥ ቁጥር ፩፤ ነሐሴ ፲፭ ቀን ፲፱፻፹፯።  
በቀለ የጻፈው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 «የራስን እድል በራስ መወሰን  መብት በማናቸውም መልኩ  የኢትዮጵያ ብሔር ፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ  ሁሉ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው» እያለ ነው እንግዲህ ሕገ መንግሥቱን  ጻፍሑት የሚለው በቀለ ገርባ  የብሔረሰብና የሕዝብን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ገፍፎ «የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ለብሔር ብቻ የተሰጠ መብት ነው»  የሚለን!
በቀለ ገርባ «የአዲስ አበባ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ  የመወሰን መብት የለውም» ብሎ የሰዎችን መብት ሲደመስስ የጣሰው ጻፍሑት የሚለውን ሕገ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የተፈራረመቻቸውን የዓለም አቀፍ ሕጎችን ሁሉ ነው። ከዚህ በተጨማሪ  የራስን እድል በራ የመወሰን መብትን ጨምሮ ማናቸውንም መብት ሕገ መንግሥትም ሆነ ዓለም አቀፍ ሕግ እውቅና ሊሰጡ ይችላሉ  እንጂ በቀለ ሊነግረን እንደፈለው መብትን ሊሰጡ አይሰጥም።
ባጭሩ በቀለ ገርባ ጻፍሑት የሚለው ሕገ መንግሥት ግን ራስን እድል በራስ የመወሰን  መብት ለብሔር ብቻ ሳይሆን ለብሔረሰብና ለሕዝብም ሰጥቷል። የአዲስ አበባ ሕዝብ  በቀለ ጻፍሑት ያለውን  ሕገ መንግሥት የራስን እድል በራስ የመወሰን  መብት» ተጠቅሞ የራሱን እድል በራሱ መወሰን ይችላል። ለመብት እታገላለሁ የሚለው በቀለ ግን ከኦሮሞ ውጭ ነው ያለውን የአዲስ አበባ ሕዝብ መብት ሊገፍ የሄደው ጻፍሑት የሚለው ሕገ መንግሥት የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት  ከሰጣቸው «የኢትዮጵያ ብሔር ፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ» መካከል በሕዝብ ስር  የሚጠቃለለውን  የአዲስ አበባን ሕዝብ የራስን እድል በራስ የመወሰን  መብት ነው። https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=2566042816750985&id=100000358765743
Filed in: Amharic