>

በስዊድን የባልደራስ ምክር ቤት ቻፕተር ቦርድ አባል ተወካዮች ለኢትዮጵያ ኤምባሲ ያስገቡት ደብዳቤ

ለኢትዬጵያ ኢምባሲ 

ለ- በስዊድን የኢትዬጵያ ኢምባሲ

ጉዳዩ​- ​የባለአደራው ምክር-ቤት አባላት የሆኑት የሕሊና እስረኞች በአስቸኳይና ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ እንዲፈቱ ስለመጠየና በቅርቡ የአዲስ አበባ መስተዳድር በ”Reform” ሰበብ በመስተዳድሩ ሠራተኞች ላይ የወሰደው ሕገ-ወጥና ኢ-ፍትሐዊ ከሥራ የማፈናቀል እርምጃ በአስቸኳይ እንዲስተካከል ስለመጠየቅ።

በሐገራችን ኢትዬጵያ ከረዥሙ የህወሐት መራሹ የ27 አመት ጨቋኝ አገዛዝ በኃላ- ከአንድ አመት በፊት በኢትዬጵያኖች ትግልና መስዋትነት የህወሐት መራሹ መንግሥት ከአራት ኪሎ ሊሰናበት ችሏል። ይህ ለውጥ ጅማሮው ላይ አበረታች የሆኑ እርምጃዎችን መውሰዱና ሁሉኑም ኢትዬጵያውያን በሐገራቸው የዲሞክራሲ ግንባታ ላይ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መጋበዙ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ነገር ግን ለውጡ ሊያመጣ የታሰበውን የዲሞክራሲያዊ ሥረአት ግንባታ ሂደት በአጭር ጊዜ ውስጥ አደጋ ላይ መውደቁ፣ ብሎም ፅንፍ የረገጡ የብሔር ፖለቲከኞች- የለውጡን አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በመለወጥ ወደ ተራ የሆነ የብሔር ተረኝነትና ተስፋፊነት ለውጠውታል። ይኸን አሳዛኝ ኩነት የሚያሳዩ ብዙ ክስተቶች እንዳሉ ይታወቃል። በተለይ የሐገሪቱ ርእሰ ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ ላይ የህልውና አደጋ የጣሉ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ሴራዎች የለውጥ ሐይል በሚባለው አካል በግልፅ መጐንጐናቸው አንዱ አብይ ክስተት ነው።

የባለአደራው ምክር-ቤትም በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ላይ የተጋረጠው የሕልውና አደጋ ለመመከት- በጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች እስክንድር ነጋና ሌሎች ተቆርቋሪ ኢትዬጵያውያን ተመስርቷል። የምክር-ቤቱ አመሠራረት ፍፁም ሰላማዊ እንደነበረ ከአመሠራረቱ ሂደት በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል። ምክር-ቤቱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ሕልውና አደጋ ላይ የጣሉትን አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ሂደቶች ለመታገል ይረዳው ዘንድ አራት ግልፅ የሆኑ አላማዎችን አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ይሁን እንጂ ከምሠረታው ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በመንግሥት በኩል በባለአደራው ምክር-ቤት ላይ የሚደረገው አፈና፣ እንግልትና እስራት ከአሳሳቢነት አልፎ በእጅጉ አሳፋሪ እየሆነ መምጣቱ የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ቆይቷል። በምክር-ቤቱ ላይ የሚደረገው ወከባ ፍጥነትና ቀጣይነት- ለውጥ የሚባለው ነገር እንደሌለና ይልቁንም ከሕወሐት ጊዜ ወደባሰ ጭቆና እየገባን እንደሆነ ማሳያ ነው። በተጨማሪም ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ በአጠቃላይ የሐገሪቱ እጣፋንታ በትርምስና ሁከት የተሞላ ለመሆኑ ለመገንዘብ ነብይ መሆን አያሻም።

እኛም በስዊድን ሐገር የምንኖር ኢትዬጵያውያን በአንድ በኩል-የሐገራችን ጉዳይ ስለሚያሳስበንና ስለሚያገባን በሌላ በኩል ደግሞ የባለአደራው ምክር-ቤት አንግቦ የተነሳው ግብ እንዲሁም እንቅስቃሴው ሙሉ በሙሉ በባለቤትነት ስሜት እንደምንደግፍ ብሎም ከምክር-ቤቱ ጐን በመቆም አብረን እንደምንታገልና እየታገልን እንደሆነ በስዊድን የሚገኘው የኢትዬጵያ ኢምባሲና የኢትዬጵያ መንግሥት እንዲገነዘቡልን እንወዳለን። በዚህም መሠረት ከታች የተዘረዘሩትን ጥያቄዎችና ማሳሰቢያዎች ኢምባሲው ለሚመለከተው የመንግሥት ክፍል አሳውቆ በአስቸኳይ መልስ እንዲሰጠን በአፅኖት እንጠይቃለን፥

​1- የባለአደራው ምክር-ቤት አባል በመሆናቸው ብቻ የታሰሩት

– ጋዜጠኛ ኤልያስ ብሩ
– ስንታየሁ ቸኰል
——-
በአስቸኳይና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ አጥብቀን እንጠይቃለን።

2- እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የሕሊና እስረኞች- የታሰሩት በምክር-ቤት አባልነታቸው ሆኖ ሳለ- ክስ የተመሰረተባቸው በባሕር ዳር ከተማ ሰኔ 15 በተከሰተው የመንግሥት ባለስልጣኖች ግድያ ነው። ክሱም የተመሰረተባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይለወጣል ባሉት አፋኙና አሮጌው የፀረ-ሽብር ሕግ ነው። ስለዚህም አቃቤ-ሕጉ፥ በአዲስ አበባ ላይ የሚንቀሳቀስ መሐበራዊ (ስቪክ) ድርጅትን እንዴት ባሕርዳር ከተማ ከተከሰተ ድርጊት ጋር አያይዞ በአሮጌው የፀረ-ሽብር ክስ ሊመሠርት እንደቻለ ግልፅ የሆነ ሙብራሪያ እንዲሰጠን እንጠይቃለን? (ይህ ድርጊት ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት መሆኑና መንግሥታዊ ተቋማትም እንደ ብሔራዊ ተቋም በመርህ ሳይሆን በአሳፋሪ ማንአለብኝነት እንደሚንቀሳቀሱ የተገነዘብን እንደሆነ መንግሥት እንዲረዳው እንፈልጋለን)

3- በባለአደራው ምክር-ቤት ላይ የሚደረጉ ወከባና አፈናዎችና እጅግ የተቀናጁ መሆናቸውን ተገንዝበናል። ከዚህ ድርጊት ጀርባ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትና የአዲስ አበባ መስተዳድር እጅ እንዳለበት የሚያሳዩ አስተማማኝ መረጃዎች አሉ። ከዚህም በላይ እነዚህ የመንግሥት ተቋማት ከፅንፈኛ የብሔር ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ጋር በትብብር እንደሚሠሩ ደርሰንበታል። በአንድ ሐገር እየኖርን ተረኞች ሕግ ተላልፈው ብዙ ወንጀሎች ሲሰሩ ዝም የሚባሉበት- በሰላማዊ መንገድ ሕግ አክብሮ የሚንቀሳቀሰው የባለአደራው ምክር-ቤታችን ደግሞ እንደ ወንጀለኛ የተቆጠረበት ምክንያት ስላልገባንና እንደ ሐገርም በድርጊቱ ስላፈርንበት መንግሥት ለዚህም በቂ ማብራሪያና መልስ እንዲሰጠን በአፅኖት እንጠይቃለን።

4- ከለውጡ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባን መስተዳድር ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለመፍታት በሚል ታሳቢነት ከተለያዩ ባለሙያዎች የተወጣጣ አጥኚ ቡድን እንደ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ተቋቁሞ ጥናት ሲያደርግ እንደነበር እናውቃለን። የዚህ ፕሮጀክት ጽ/ቤት የጥናት ቡድን ሆን ተብሎ በከንቲባ ታከለ ኡማ እንዲበተንና የጥናቱም መጨረሻ የከንቲባውን ቢሮ መጽሐፍ መደርደሪያ ማጣበብ ሆኗል። ስለዚህም የፕሮጀክት ጽ/ቤቱን የጥናት ውጤት የከንቲባው ቢሮ ለምን ለሕዝብ ይፋ እንዳላደረገና የጥናት ቡድኑኑም ለምን እንደበተነው ዝርዝር ማብራሪያ መስተዳድሩ እንዲሰጠን አጥብቀን እንጠይቃለን።

5- በቅርቡ በታከለ ኡማ የሚመራው የአዲስ አበባ መስተዳድር “reform” በሚል ሰበብ አዲስ የሠራተኞች ድልድል ለማድረግ-በከንቲባ ታከለ ኡማ የተቋቋመ ኮሚቴ እንዳለ ይታወቃል። ይህ ኮሚቴ የሚመራው የአራዳ ክፍለ ከተማ የፖለቲካ ቹመኛ ካድሬ ወ/ሮ ሕይወት ጉግሳ ሲሆን-ሁሉም የኮሚቴው አባላት የኦዴፖ ካድሬዎች ናቸው። ይህ ኮሚቴ ባደረገው የሥራ ድልድል ከ90 ሺህ ሠራተኞች ወደ 17ሺህ የሚጠጉ ሠራተኞች ከሥራ ምደባ ውጪ ሆነዋል። ከ2 ሺህ እስከ 3 ሺህ የሚጠጉ ሠራተኞች ደግሞ ጭራሽኑ ከሥራ ተባረዋል። ባልተመደቡና ከሥራ በተሰናበቱ ሠራተኞች ፋንታ-ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የኦዴፖ ካድሬዎች እየተመደቡበት እንደሆነ አስተማማኝና በቂ መረጃ አለን። ስለሆነም የአዲስ አበባ መስተዳድር ከታች ለዘረዘርናቸው መሠረታዊ ነጥቦችና ጥያቄዎች በፍጥነት ማብራሪያ እንዲሰጠን በብርቱ እናሳስባለን፥

– የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ቅጥር፣ ምደባና ሌሎች የተያያዙ ጉዳዬች-በሜሪትና በትምሕርት ዝግጅት መሆን ሲገባቸው- እንዴት ከዘመነ ሕወሐት ጊዜ በከፋ መልኩ በካድሬዎች ስብስብ በተሞላ ኮሚቴና በር ተዘግቶ ግልፅና ይፋ ባልሆነ መስፈርት ሊከናወን ቻለ? ለምን?

-እንደዚህ አይነት ኢ-ፍትሐዊና አድሏዊ አሠራሮች እንዲከናወኑ የሚወስነውና የሚያስፈፅመው የትኛው አካል ነው? ተጠያቂነቱስ?
-ይህ በአዲስ አበባ ሕዝብ ያልተመረጠ አስተዳደር- እንደዚህ ያሉ ትልቅ የመዋቅራዊ ለውጥ ሥራዎች እንዲሰራ የፖለቲካ ስልጣን ማን ሰጠው?

በመጨረሻም መንግሥት ለነዚህ ከላይ ላነሳናቸው ጥያቄዎችና ማሳሰቢያዎች ቁርጥ ያለ መልስና ማብራሪያ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚሰጠን ተስፋ እያደረግን- እኛ በስዊድን ሐገር የምንኖር የባለአደራው ምክር-ቤት ቻርተር አባላት- የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሕልውና አደጋ ጥያቄ እስኪመለስ ድረስ- አዲስ አበባና በመላው አለም ከሚገኙ የባለአደራው ምክር-ቤት አባላቶች ጋር በመተባበርና በመቀናጀት ትግላችንን የምንቀጥል መሆኑን ለማሳሰብ እንወዳለን።

-አዲስ አበቤነት ይለምልም!

-ኢትዬጵያ ለዘላለም ትኑር!

-ድል ለዲሞክራሲ!

Filed in: Amharic