>

"የኢትዮጵያ ፈውስ ከመስቀሉ ሥር ነው!!!" (ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ) 

“የኢትዮጵያ ፈውስ ከመስቀሉ ሥር ነው!!!”
ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ 
* በመስቀል ደመራ አከባበር ላይ 55 ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል!!!
የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት
ኢትዮ 360
ብጹዕ አቡነ ማቲያስ በዛሬው የመስቀል በዓል ንግግራቸው በአደባባይ የተገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የእምነትን ተከታዮች ብቻ ሳይሆን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ንግግራቸውን የሰሙ የተለያዩ በጎ አስተያየቶችን እየሰጡ ነው። ከንግግራቸው መካከል …
“ኢትዮጵያውያን መሪዎችና ልኂቃን ከሐምሣ ዓመታት ላላነሱ ዘመናት ከእግዚአብሔር ርቀዋል፡፡ ከመስቀሉ ሥርም ጠፍተዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አመለካከት በኢትዮጵያ ውስጥ አያስኬድም፣ እንደማያስኬድም በግልጽ እያታየ ነው። ከእንግዲህ ወዲህ ተዉ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እንደ ቀደምት አባቶቻችን ከቤተ ክርስቲያን አፀድና ከመስቀል ሥር እንገኝ፡፡ የጎደለንን ፍቅርና ሰላም፣ አንድነትና እኩልነት፣ ፍትሕና ወንድማማችነት በመስቀሉ ውስጥ ተትረፍርፎ እናገኘዋለን፡፡ ይቅርታና መተባበር፣ መከባበርና መተማመን በመስቀሉ ውስጥ ሞልቷል፡፡ የኢትዮጵያ ፈውስ ከመስቀሉ ሥር እንደሆነ ሁላችንም እንወቅ፤ እንደ አባቶቹ በመስቀሉና በቃሉ ለመክበር የሚፈልግ ትውልድ ወደ መስቀሉና ወደቃሉ ሊመለስ ግድ ይለዋል፤ ያለዚያ ግን ምኞቱ ሁሉ ቅዠት ከሚሆን በቀር ሊሳካ አይችልም፡፡”
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ፓትርያርክ
 በመስቀል ደመራ አከባበር ላይ ጽሑፍ ያለው ቲሸርት ለብሳችኋል በሚልና በሌሎች ምክንያቶች 55 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት አስታወቀ።
 ሃገረ ስብከቱ እንዳስታወቀው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ምእመናን መካከል 33ቱ ቤተክርስቲያኗ ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት ይቁም የሚል መልእክት የያዘ ካኒቴራ በመልበሳቸው ነው።
ካኒቴራዎቹ ላይ የሰፈሩት ጽሑፎችም “የቤተክርስቲያን ጉዳይ ያገባኛል”፣ “የቤተክርስቲያን መቃጠልና ጥቃት ይቁም” የሚል የውግዘት መልእክቶችን የያዙ እንደ ነበሩ ሃገረ ስብከቱ አስታውቋል።
ከቀሪዎቹ 16 እስረኞች መካከል 12ቱ ስለት ይዘው ተገኘተዋል የሚል ክስ ሲቀርብባቸው 4ቱ ደግሞ የሌላ ሰው ባጅ አድርገዋል የሚል ምክንያት ቀርቦባቸዋል ሲል ሃገረ ስብከቱ አስታውቋል።
ምእመናኑ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ የተወሰዱት ካዛንችስ ወደሚገኘው ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ እንደነበረ የጠቆመው የሃገረ ስብከቱ መረጃ፣ ከብዙ ውጣ ውረድ እና ድርድር በኋላ ከእስረኞቹ መካከል 37 ምዕመናን በዋስ እንዲለቀቁ መደረጉንም አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል ደረጃ አደጋ ተደቅኖብኛል ስትል በይፋ የተናገረችበት የመስቀል ደመራ በአል የአለም መገናኛ ብዙሃንን ቀልብ መሳቡም እየተነገረ ነው።
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በገጹ ላይ 110 ሚሊዮን እንደሚሆን ከሚገመተው የአገሪቱ ህዝብ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆን ተከታይ ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከባድ ፈተና ከፊቷ መጋረጡን ዘግቧል።
አጃንስ ፍራንስ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከቤተክርስቲያኗ አበይት በዓላት አንዱ የሆነውና በየአመቱ የዓለምን ቀልብ በሳበ መልኩ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በከባድ ስጋት ውስጥ ሆኖ መከበሩን የሃይማኖት መሪዎችን ጠቅሶ በዘገባው አስፍሯል።
በደርዘን የሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናት በእሳት መጋየታቸውና የእምነቱ ተከታዮች አደጋ ውስጥ መሆናቸው እየተነገረ ባለበት በዚህ ወቅት የደመራ በአል መከበሩ ደግሞ በዓሉን ከፍተኛ የስጋት ድባብ እንዲያጠላበት አድርጓል ሲል ይገልጻል።
 የሐይማኖቱ መሪዎች ለሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቤተክርስቲያኗ እየደረሰባት ካለው ጥቃት እንዲታደጓትና የጥፋት ሃይሎች ከቤተክርስቲያኗ ላይ እጃቸውን እንዲያነሱ ጥያቄ ቢያቀርቡም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄውን በዝምታ አልፈውታል ይላል የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው።
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች አገሪቱን እያስተዳደረ ባለው አካል ደስተኛ አለመሆናቸውን ቃለ መጠይቅ ካደረገላቸው ሰዎች መረዳቱንም በገጹ አስፍሯል።
 በርካታ ኢትዮጵያውያን በዚህ ጉዳይ ላይ የአገሪቱ መንግስት አንድ ነገር ይላል ብለው ቢጠብቁም ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ አስተዳደራቸው በቸልታቸው ገፍተውበታል፤ ይህ ቸልታ እንደምን ሊቀጥል ቻለ ሲል ጥያቄውን ያቀርባል ኤ ኤፍ ፒ።
ምናልባትም ይላል ዘገባው በቤተክርስቲያኗ እና አገሪቱን አስተዳድራለሁ በሚለው አካል መካከል እያደገ የመጣው ቅራኔ አገሪቱን ወደሌላ አዲስ ቀውስ ሊከታት ይቻላል ሲል ስጋቱንም ጠቁሟል።
ቢቢሲ አፍሪካን እና ያሆ የዜና አውታርን ጨምሮ በርካታ የአለም መገናኛ ብዙሃን በስጋት ውስጥ ሆኖ የተከበረው የመስቀል ደመራ በአል በአስፈሪ ድባብ ውስጥ ማለፍ በዘገባቸው አፍረዋል።
በርካታ የሃገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃን በቤተክርስቲያኗ ላይም ሆነ በሐይማኖት አባቶችና በምእመናኑ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃትና ተፅእኖ እየጠነከረ መምጣት በአንፃሩ አገሪቱን አስተዳድራለሁ የሚለው አካል ዝምታ እና ቸልተኝነት በአገሪቱ የአዲስ ቀውስ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል በየዘገባዎቻቸው ጠቁመዋል።
Filed in: Amharic