>
11:10 am - Wednesday December 7, 2022

የአንድ ጎሣና የአንድ ሃይማኖት እሳቤ በሀገር አስተዳደር ላይ ያለው ተፅዕኖ (ነፃነት ዘለቀ)

የአንድ ጎሣና የአንድ ሃይማኖት እሳቤ በሀገር አስተዳደር ላይ ያለው ተፅዕኖ

ነፃነት ዘለቀ

ከምንታዘበው ሀገራዊ ምስቅልቅል ሁኔታ አኳያ ጊዜው የአርምሞና የጸሎት ቢሆን ብዙዎቻችን የምንስማማበት ይመስለኛል፡፡ ላለፉት ሁለትና ሦስት አሠርት ዓመታት ብዙ ተጯጩኽን ያመጣነው የረባ ነገር ባለመኖሩ መጻፍም ሆነ መናገር ከላይ ካልታገዘ በስተቀር በእስካሁኑ አካሄድ ከሆነ ትርፉ ከድካም እምብዝም አላለፈም፡፡ ለውጥ ሲባል ሁሉንም የሚጠቅም ሲሆን እንጂ ትሻልን እየሰደድክ ትብስን ማምጣት ከለውጥ ሊቆጠር አይገባውም፡፡ ለዚህም ሣይሆን አይቀርም በርካታ ጸሐፍትም ይህን በመገንዘብ አደብ ገዝተው ዐርፈው የተቀመጡት፡፡ አንዳንዶች ደግሞ አያርማቸውምና ግመሎቹን መከተል አይሰለቻቸውም – እንደውሻዋ እየጮኹ፡፡

የሦርያን 10 መቶኛ አካባቢ የሕዝብ ቁጥር የሚይዙት አላዊቶች የሀገሪቱን ሁለመና ለብዙ ዓመታት ተቆጣጠሩ፡፡ ለአብነት ከ1200 ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖችና የጦር አዛዦች ውስጥ ከ1000 በላይ እነሱው እንደነበሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው የሀገሪቱ ጥቅማጥቅሞችና የሥልጣንና ኃላፊነት ቦታዎች በአንድ አነስተኛ ነገድ ቁጥጥር ሥር መግባታቸውንና ሌሎቹ በገዛ የጋራ ሀገራቸው የበይ ተመልካች ሆነው ለድህነትና ለባይተዋርነት መጋለጣቸውን ነው፡፡ ያ ወልጋዳ አካሄድ ለአራት አሠርት ዓመታት እንደቆዬ በሀገሪቱ የማያባራ ቀውስ በማስከተሉ በውጪ ጣልቃ ገቦች ምክንያት ሀገሪቱ መረጋጋት አቅቷት ይሄውና ከሀገራት ተርታ ወጥታ በነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህን ያነሳሁት ለምን እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ከዚያ ብዙ መማር ሲቻል የኞች የምንላቸው የገዛ ወገኖቻችን የሦርያን መሰል የአንድ ወገን አክራሪነት በዚህች ሀገራችን በማምጣት የማይበርድ እሳት ሊለኩሱ ቀን ከሌት ሲራወጡ እያየን ስለሆነ ወደኅሊናቸው በጊዜ እንዲመለሱ ለመምከር ነው – ጆሮ ቢኖራቸው ለዚሁም፡፡

የአንድ ጎሣና የአንድ ሃይማኖት የበላይነትን ለማስፈን መከጀል መዘዙ ምን እንደሆነ እጅግ ብዙ ምሣሌዎችን ማየት ይቻላል፡፡ ከዚህ በላይ የተጠቀሰው ምሣሌ ይብቃንና ወደሀገራችን ስንመጣ በተለይ በአሁኑ ወቅት እየተስተዋለ የሚገኘው የአንድ ጎሣና የአንድ ሃይማኖት እንደኤች አይቪ በየሴኮንዶችና ደቂቃዎች እየተስፋፋ መምጣት ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል መታወቅ አለበት፡፡

አንድ የሀገር መሪ የራሱን የጎሣ አባላትና የራሱን እምነት ተከታዮች በመብራት እየፈለገ ወደ ራሱና ወደሥልጣን ማስጠጋቱ በራሱ ችግር አይደለም፡፡ ችግሩ ያን ተግባሩን በመታከክ ሌላ ሸርና ተንኮል ወይም ሤራና ደባ ካለው ነው፡፡ የሀገራችንን ወቅታዊ ፖለቲካ የምናየው በዚህ መነጥር ነው፡፡ እንጂ መከላከያው በጴንጤ፣ ፖሊስ ሠራዊት በጴንጤ፣ ገቢዎች ሚኒስቴር በጴንጤ፣ ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጴንጤ፣ አዲስ አበባ አስተዳደር በጴንጤ፣ ምን አለፋችሁ ከሞላ ጎደል ሁሉም የሀገራችን ከፍተኛ የሥልጣን እርከኖች በጴንጤና ከነዚሁም አብዛኞቹ በኦሮሞ ጎሣ መያዛቸው በራሱ እንደችግር ባልታዬ፡፡ ችግሩ ሌላ ሆኖ በመገኘቱ ግን አሳሳቢነቱን ሳንሰለች መግለጽ ቢያንስ ለታሪክ ፎጆታ ሲባል እንገደዳለን፡፡ ዝም አይነቅዝም አይባልም – ይነቅዛል፡፡

ኦርቶዶክስና አማራዊነት ከፋም ለማም ከነህፀፆቻቸውና ከነችግሮቻቸው ኢትዮጵያን አንድ አድርገው አቆይተዋል፡፡ አማራ በተለይ ካለው ብሔራዊ የዜግነት ስሜት አኳያ ማንም ሊቀጣጠበው(ሊያሽሟጥጠው) በማይችል ሁኔታ ለዚህች ምድር ብዙ መስዋዕትነትን ከፍሏል፡፡ ጎሠኝነትን የሚጠየፈው ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንዱ ፈርጥ ከመሰል ጎሣዎችና ነገዶች ጋር በመሆን የሀገራችንን አንድነት ጠብቆና አስጠብቆ ጠላት የሚመኝላት የመበታተንና የመፈራረስ አደጋ ሳይደርስባት እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ጸንታ እንድትቆይ ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል – እናንተ ከፈለጋችሁ “የአንበሣውን ድርሻ” በሉት – በኔ ግን አያምርምና ሆን ብዬ ተውኩት፡፡

አሁን ግን ነገሮች ወዴትና በየትኛው አቅጣጫ እየተጓዙ እንደሆነ ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ሀገራዊ ምስቅልቅሉ ጦዟል፡፡ ገመድ ጉተታው በየቀኑ እየተጋጋለ መጥቶ ሀገራችን ባለቤት የሌላት እስክትመስል ድረስ የኳስ አበደች ዓይነት ድራማ ግዘፍ ነስቷል፡፡

በልማድ ጴንጤ የምንላቸው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ከላይ እስከታች በወረራ በሚመስል መልክ ሥልጣን እየተቆጣጠሩ ነው – ለዘመናት የተጠሙበት በሚመስል ሁኔታ እንደተራበ ጅብ ሥልጣኑን እየተቀራመቱ ይገኛሉ፤ በዚህም ያሣዝኑኛል፡፡ ብርቅ ሆኖባቸው ወድቆ ያገኙት የመሰላቸውን ሀገርን የመግዛት ዕድል ክፉኛ እየተቦጫጨቁት ነው፡፡ ይህ ነገር ምናልባት የሀገሪቱን አንድነት ከማስጠበቅ አኳያ የቀዳሚነት ሥፍራ የሚይዘውን የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ለመምታትና ሀገሪቱን ለመበታተን ዓላማ ያደረጉ የውጭ ኃይሎች እጅ ያለበት እንደሆነ ያስጠረጥራል፡፡ ለምሣሌ በኢትዮጵያ ታሪክ የፕሮቴስታንት የመከላከያ ሚኒስትር ታይቶ አይታወቅም፡፡ እንዲህ ማለት ያስቻለኝ በልማድ እንደምናውቀው ጴንጤዎች በኢየሱስ ተዓምራት እንጂ በአካላዊ ጦርነት እንደማያምኑና ለሀገራዊ ወታደራዊ ግዳጅ እንኳን መመልመል እንደማይፈልጉ በደምብ ስለማውቅ ነው፡፡ የጴንጤ የጦር መሪ ይቅርና ተራ ወታደርም በኔ ዘመን አይታወቅም፡፡ ከመነሻው ይህን ነገር እነሱም ይቃወሙታል፡፡ አሁን ምን ተገኘና ነው ታዲያ ምድረ ወታደርና የጦር አዛዥ ከነሀገሪቱ አጠቃላይ የአመራር ስኳድ ጭምር ጴንጤ ሊሆን ያስፈለገው? ኦርቶዶክስንስ እንደዶሮ ብልት መገነጣጠል ለምን አስፈለገ? ሌላው ቀርቶ ሙስሊሙ ጃዋርና “ኦርቶዶክሱ ቀሲስ” በላይ በፍቅር ብን ብለው በአንድ ላይ ፎቶ እስኪነሱ ድረስ አንድ ባልሆኑበት ሃይማኖት እንዲያ መተባበራቸው ለምን ይሆን? መነሻው እንደሚባለው የናይል ዴልታ ይሆን? አማራንስ ቤተስኪያን እንደገባች ውሻ እንዲህ ጥምድ አድርገው የያዙት ምናልባት የሀገሪቱን አንድ ምሠሦ በማውለቅ ቶሎ እንድትፈራርስላቸው ይሆን? አማራን ማሳደድና ቤቱ ድረስ በመሄድ የፈለጉትን መግደል፣ የፈለጉትን ማሰር፣ የፈለጉትን መሾም… ከምን የመነጨ ድፍረት ይሆን? ይህንን ተንኮልና ሸራቸውንስ ሁሉ እንዴት አወራርደው ይጨርሱታል? ያልገባንን ነገር መጠየቅ አግባብ ነው – ነውርም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሀገራችን የሁላችን እንጂ የዚህ ሃይማኖት ወይም የዚያ ጎሣ ተከታዮች የግል ንብረት አይደለችምና፡፡ በነገራችን ላይ እሥራኤል ዳንሳ የሚባለው የአጋንንት ውላጅ በሚፈነጭባት አንዲት “ቸርች” ውስጥ የሚከናወንን ፊንታና ከምዕራብ አፍሪቃ ተገዛ በሚባል የጥንቆላ ፓኬጅ በንጹሓን ዜጎች ላይ የሚተበተበውን ሰይጣናዊ አፍዝ አደንግዝ የምንታዘብና ተልእኮውን የምንረዳ ወገኖች የዚህ እምነት ተከታዮች ከ”ቸርች” ባለፈ ሀገርን ሲገዙ ምን ዓይነት ትንግርታዊ ሁከት ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አይከብደንምና ፈጣሪ ኢትዮጵያን ከተደገሰላት ዓለም አቀፍ የሉሲፈሪያን ካባሊስቶች የመከራ ዶፍ እንዲታደጋት በርትተን መጸለይ ይኖርብናል፡፡ ይህ ነገር ቀልድ አይደለም፡፡ ውኃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው፡፡ እንዶድንም በሞኝነቷ ነው ውኃ ጠራርጎ የሚወስዳት፡፡ የጠፋችን ሀገር ለመመለስ ከመሞከር ይልቅ እንዳትጠፋ ሁላችንም ከወዲሁ ጥረት ማድረግ ይገባናል፡፡ እዚህ ላይ ጤነኞች የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችን ማስቀየም እንደማልፈልግ በትኅትና መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ አንድ የሃይማኖት ተቋም በራሱ መጥፎ ሊሆንበት የሚችልበት አጋጣሚ በጣም ጥቂት ነው – ዝርዝሩ ይደርልኝ፡፡ በመጥፎነት የሚፈረጁት ግለሰቦችና ተከታዮቻቸው እንጂ ተቋማዊ መጥፎነት ብዙም የለምና ጥሩ ስብዕና ያላችሁ የዚህ ቤተ እምነት ተከታዮች ሥጋቴን ከልብ ተረድታችሁ የነገሬ ዒላማ እናንተ ሳትሆኑ አጭበርባሪዎቹ መሆናቸውን እንድትገነዘቡልኝ ከይቅርታ ጋር እማጠናችኋለሁ፡፡ የሁላችን የሆነው ክርስቶስ “ሁሉን መርምሩ፣ የሚበጀውን ግን ያዙ” እንዳለ በበኩሌ ለሃይማኖት ክፍፍል ትልቅ ትኩረት ሰጥቼ በከንቱ ጭቅጭቅና አታካሮ ጊዜ የማባክን አይደለሁምና እምነታችሁ በአንድ ወይ በሌላ መንገድ የኔም መሆኑን እንደምረዳ ተረዱልኝ፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝና ፈራጁ ልዑል እግዚአብሔር በመንበሩ ተቀምጦ ሁሉን ማድረግ እየቻለ እርሱን በመተካት የኔ ሰዎችን በእምነታቸው ምክንያት መፈረጅና አንዱን ለገነት ሌላውን ለሲዖል የማጨት እገዛየ እንደማያሻውም አምናለሁ፡፡ (ዋና የዛሬ መልእክቴ ነው)፡፡… ለማንኛውም በዚህ ሁሉ ትያትር አንዳች አደጋ ቢከሰት ተጎጂዎቹ ሁላችን እንጂ አንድ ወገን ብቻ አይሆንም፡፡ እርግጥ ነው – የአደጋው ቀስቃሽ ሞተሮች ከጦርነቱ ዞን ውጪ ልዩ ጥበቃ በሚኖርበት ምቹ ሥፍራ ሊሆኑ ስለሚችሉ ጉዳቱ ለጊዜው እነሱን አይነካቸው ይሆናል፡፡ ቢሆንም በአንድ ወይ በሌላ መንገድ ከጉዳቱ ነፃ የሚሆን አካል ሊኖር እንደማይችል ከታሪክ መማር ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ የሙስሊሙም፣ የኦርቶዶክስ ክርስቲያኑም፣ የጴንጤውም (በወታደራዊ ጉዳዮች ላለመሣተፍ ያለው የቀደመ አቋሙ ተከብሮለት)፣ የዋቄ ፈታውም፣ የካቶሊኩም፣ እንደሬቻና ቦረንቲቻ ዓይነት የባዕድ አምልኮት ተከታዩም፣ ሃይማኖት ከናካቴው የሌለውም፣ የሴቴኒስቱም፣ ወዘተ፣ የወል ሀብት ናት፡፡ ለምሣሌ በምርጫም ይሁን በጡጫ – በሆነ አጋጣሚ – ሴቴኒስቱ ሥልጣን ቢይዝ የክርስቲያኑን መብት መቶ በመቶ ሊያከብር ይገባዋል – ይህ ግድ ነው – ካላከበረ ከመነሻው ሥልጣን መያዝ የለበትም፡፡ ሀገርንና ሌላ ሌላ ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ልዩነትን መለየት ተገቢና ግዴታም ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ኢትዮጵያ የኦሮሞውም፣ የትግሬውም፣ የጉራጌውም፣ የጉሙዙም፣ የአፋሩም፣ የሃዲያውም፣ የአማራውም…. የጋራ ንብረት ናት፡፡ አንድ ጎሣ “በቁጥር ብዙ ነኝ” ወይም “በምንትሴ ትልቅ ነኝ” ብሎ ትንሽ ቁጥር ያላቸውን ጎሣዎች ሊበድል ቢነሳ ስህተት ብቻ ሳይሆን ዕብደትና ወንጀል፣ ነውርና ኃጢኣትም ነው – ትዕቢትና ትምክህት ለተወሰነ ጊዜ ናላን ቢያዞሩም የዞረ ድምራቸው ግን እጅግ አደገኛ ነው፡፡ አምስት አባላት ያሉት ጎሣም 30 ሚሊዮን አባላት ያሉት ጎሣም በጋራ ሀገራቸው እኩል መብት አላቸው፡፡ የሁሉም መብት እኩል ካልተከበረ ደግሞ ሀገሪቱ በሽተኛ እንደሆነች ትኖራለች፡፡ ያም በሽታ አንድ ቀን ሊገድላት ይችላል – ብዙ ሀገሮች እንደሞቱት፡፡ መስሎህ እንጂ በዚህች ምድር የምትኮራበት አንድም የግል ነገር የለህም፡፡ ጃጅተህ አርጅተህም ሆነ ገና በውርዙትናህ በአንዲት ብጣሽ ጨርቅ ተጠቅልለህ፣ በአንዲት ጠባብ ጉድጓድ ተጥለህ አንድ ሣምንት ሳይሞላህ ለምትረሣው ብዙም ተንኮለኛና ከይሲ ባትሆን ላንተ ለራስህ ይበጅሃል፡፡

ትዕቢትም ሆነ ትምክህት ገደብ ካላበጁለት በግለሰብም ይሁን በቡድንና በማኅበረሰብ ደረጃ ሊጠገን ለማይችል ስብራትና ውድቀት ይዳርጋል፡፡ “ሃይማኖትና ጎሣ የግል፣ ሀገር ግን የጋራ” መሆናቸውን ዘንግተን ቀን ሰጠን ብለን ያሻንን ብናደርግ የክፋታችንን ልክ የሚመጥን እንዲያውም ከዚያም የሚያልፍ ውዝፍ ዕዳ የምንከፍልበት ጊዜ እንደሚመጣ መረዳት ብልኅነት ነው፡፡ በቃኝ እባክህን…. ፈጣሪያችን ይሄን አስለፍላፊ የእፉኝቶች ክፉ ዘመን ቶሎ ወደማኅደሩ በጠቀለለልኝና እኔም ትንሽ አረፍ ባልኩ….

Filed in: Amharic