>

ድመቱ አዴፓ!!! (ቅዱስ ማህሉ)

ድመቱ አዴፓ!!!
ቅዱስ ማህሉ
የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ሚዲያ ልማት ዋና መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ረዳት ኮሚሽነር ሰይድ አህመድ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ። ትናንት እና ዛሬ ድረስ በዘለቀው የምዕራብ ጎንደር ውጊያ ላይ በቅጡ ያልተዘጋጁ የልዩ ሃይል አባላት እንደ ቅጠል መርገፍ የተቃወሙት ኮሚሽነር ሰይድ አህመድ ለእስር የተዳረጉት “ብዙ ጠላት ያለው ግን አንድም የጦር መሪ የለለው ህዝብ ይዘን እነ ጄነራል ተፈራ ማሞን እና ኮለኔል አለበል በእስር ማቆየት ሞኝነት ነው። ፍቷቸውና ህዝቡን ይታደጉት። ከዚያ በተጨማሪ ልምድ ያላቸው የአማራ ልዩ ሃይል አባላት እያሉ ልምድ የሌላቸውን ወታደሮች በመላክ የምታስጨርሷቸው ጀነራል አሳምነው ጽጌ ያሰለጠነው አንድም ወታደር በህይወት እንዳይተርፍ ሴራ ሸርባችሁ ነው።” በማለታቸው እንደሆን ተነግሯል።  አዴፓ ክልሉን ባዶ አድርጎ ትንሽ የቀሩትን ነፍስ ያላቸውን የራሱን ልጆች  እንደ ድመት ራሱ በልቶ እየጨረሳቸው ነው።
ይሄው ቡድን የአማራ ህዝብ ራሱንም እንዳይከላከል በተለያየ ማነቆ ይዞ ከሰኔ 15 ግድያ የተረፉትን  የጦር እና የመከላከያ ልምድ ያላቸውን ሰዎችም እስር ቤት ቆልፎ የክልሉን ህዝብ አደጋ ላይ እየጣለ ነው። ግን ይህ ድርጊቱ ትናንት ያልኩትን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው። አሁን የምዕራብ ጎንደር ገበሬዎች እየተገደሉ እንኳ በመከላከል ፋንታ ወይም ህዝቡ ራሱን እንዲከላከል መግለጫ በማውጣት ፋንታ አዴፓ “የፌደራል መንግስት ያግዘናል” የሚል መግለጫ ነው ያወጣው።  አብይ አህመድ እና መንጋው ሰሞኑን በናይሮቢ በር ዘግተው አዴፓን ለመቅበር ሲመክሩ ቆይተዋል። የአዴፓ ግብዓተ መሬት ሊፈጸም ተቃርቧል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በአፋር ልዩ ሃይል እና በሱማሌ ልዩ ሃይል መካከልም ግጭት መቀስቀሱ ታውቋል።
የአማራ ክልልን የሚሊሻ፣ የደህንነት እና የልዩ ሃይል ወታደራዊ ልምድ ያካበቱ እና ልምድ ያላቸውን ሰዎች በሙሉ ከክልሉ አራቁቶ እስር ቤት የዘጋው አዴፓ ዛሬ ጥቃት ሲደርስ ቅማንት፣ህወሃት፣ ኦነግ ወዘተ ማለት ምን ለማምጣት ፈልጎ ነው? አዎ! ነን ቢሉትም ከመግለጫ ውጭ ምንም አያመጣም።
 በስማቸው ለመጥራት የፈራውም ለዚያ ነው። ምክንያቱም ነፍስ ያላቸውን ሰዎች በሙሉ በር ቆልፎባቸው ፊትለፊት እያወሩ ከጀርባ አጠቀኑን ከሚሏቸው ሰዎች ጋር አንሶላ በሚጋፈፉ ጎጠኞች ተሞልቷል። ትናንት አስራት ያነጋገራቸው የባህርዳር ነዋሪዎች አሁን ድረስ እየከነከነኝ ነው። ነዋሪዎቹ ያሉት “የሚያስጠቃን እና የሚያጠቃን ሌላ ሳይሆን አዴፓ ነው። አሁን እየተገደልን እንኳ ለአማራ የሚቆረቆሩ ወጣቶችን እያሳደደ እያሰረ እና እየገደለ ነው። ምንም የማይሻሻል ድርጅት ነው።” ነው ያሉት። ይህ ማለት አዴፓ በዙሪያው አይደለም በጀርባው እሳት ቢነድበት ምንም ጉዳየ ብሎ የሚጥፈው አንድም ሰው እንደሌለ ነው።
ይህን ለመረዳት ምናልባትም እኔ የመጨረሻው ሰው ሳልሆን አልቀርም። እነዚህን ሁሉ የጦር መኮንኖች ያለ አንዳች ክስ ለወራት ቆልፈህ ተጠቃሁ ብትል ጆሮ የሚሰጥህ አታገኝም። ምንም! ይሄ ሁሉ ሰው ታስሮ እንኳ  የሰኔ 15ቱ የክልሉ አመራሮች ግድያ ሰለባ የሆኑት ቤተሰቦቻቸው “በገዳዮች የሚደረግ የወንጀል ማጣራትን  አንፈልግም።” ብለው መግለጫ አውጥተዋል።ስለዚህ ይህ ማለት አዴፓ በእስር ቤት ያጎረው ገዳዮቹን እንዳልሆነ የሟች ቤተሰቦች ሳይቀር ያውቃሉ ማለት ነው።
ገዳዮቹ መርማሪ ተደርገው መቀመጣቸውን የሟች ቤተስቦች አውግዘዋል። ያ ባይሆንማ ተወንጅለው ከታሰሩት እስረኞች ውስጥ ቢያንስ አንዱ ላይ ማስረጃ አቅርባችሁ ክስ ትመሰርቱ ነበር። ግን እስካሁን ምንም የለም። እዚህ ላይ ሁለት ችግር ነው ያለው። አንዱ ንጹሃንን ማሰሩ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የንጹሃን ደም በከንቱ ፈሶ እንዲቀር እየተደረገ ነው።ከዚያ ውጭ ግን እነዚህን ያለወንጀላቸው በእስር የምታማቅቋቸውን አንዳንዶቹም ፍርድ ቤት ለቋቸው በጉልበት ያፈናችኋቸው ንጹሃን ለቤተሰባቸው ብቻ ሳይሆን ለአደጋ እያጋለጣችሁት ያለውን ህዝብ ለመታደግ ይጠቅማሉና በአስቸኳይ ፈታችሁ ካሳ ከፍላችሁ ወደ ስራቸው መልሷቸው።
Filed in: Amharic