>

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ፡-

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ፡-
 
* በማእከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳና አካባቢው የተፈጸመውን የሽብር ድርጊትና የጸጥታ መደፍረስ በተመለከተ ..
የአማራን ሕዝብ በጠላትነት የፈረጁ የፖለቲካ ኃይሎች በተለይ በአለፉት 28 ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ አይነተ ብዙ ጥቃት ሲፈጽሙ ቆይተዋል፣ በመፈጸምም ላይ ናቸው፡፡
እነዚህ አካላት የአማራ ሕዝብ ማህበራዊ እረፍት ማግኘት የለበትም በሚለው መርሃቸው መሰረት በቀጥታም ሆነ በውክልና ህዝባችን ላይ ሰላሙን የመንሳትና ጸጥታውን የማደፍረስ እንቅስቃሴ ውስጥ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ በዚህ ሂደት እጅግ ብዙ ሕዝባችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለንብረት ውድመትና ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መስተጓጎል ተዳርጎ ይገኛል፡፡
የቅማንትን ሕዝብ ስም እንደ ሽፋን በመጠቀም በአማራ ጠል የፖለቲካ ቡድኖች ሙሉ ድጋፍ የአማራ ሕዝብ መካከል የውክልና ጦርነት እያካሄደ ያለውና ራሱን የቅማንት ኮሚቴ ብሎ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን በአለፉት አራትና አምስት አመታት በማእከላዊ ጎንደርና ምእራብ ጎንደር ዞኖች ከፍተኛ ጥፋት አድርሷል፣ በማድረስም ላይ ነው፡፡ ይህ ቡድን በክልሉ መንግሰትና መሪ ድርጅቱ አዴፓ እንዝህላልነትና ድክመት ከአማራ ጠል ኃይሎች የሚያገኘውን የማያቋርጥ ድጋፍ በመጠቀም እንደለመደው ከሰሞኑ በማእከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ ከመተማ ወደ ጎንደር ተሳፋሪዎችን ጭኖ ሲጓዝ በነበረ ሚኒ ባስ  እና ቅኝት ላይ በነበሩ የጸጥታ አካላት ላይ በፈጸመው የተጠናና የተደራጀ የሽብር ጥቃት ብዙዎች ሲገደሉ፣ ብዙዎች እንዲቆስሉ ሆነዋል፡፡ አካባቢው አሁንም በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ሲገኝ፣ ከጎንደር ከተማ ወደ መተማ የሚወስደው አውራ ጎዳናም ተዘግቷል፡፡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተቋርጧል፡፡ አሸባሪው ቡድን በአማራ ጠል ኃይሎች ፕሮፖጋንዳ በመታገዝ የጥፋት አድማሱን ለማስፋት እየሰራም ይገኛል፡፡ በመሆኑም፡-
1) መንግስት የአሸባሪ ቡድኑ ላይ ፈጣንና የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የሽብር እንቅስቃሴውን እንዲያስቆም፣ እሱን ተከትሎ የተፈጠረውን የጸጥታ መደፍረስም እንዲያረጋጋ አንጠይቃለን፡፡
2) ወቅቱ ሰሊጥ የሚታጨድበት ወቅት ስለሆነ መንግስት መንገዶች ሰላምና ደህነነታቸው የተጠበቁ እንዲሆኑ በማድረግ ሊደርስ የሚችለውን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ ለመከላከል ይቻል ዘንድ በልዩ ትኩረት እንዲሰራና እውን እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡
3) መንግስት በዚህ የሽብር እንቅስቃሴ ውስጥ የተሳተፉና ድጋፍ እያደረጉ ያሉ አካላትን ለሕግ እንዲቀርቡ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡ በተለይም በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ እንታገላለን ብለው በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡና በዚህ ጥፋት ውስጥ በሽፋን ሰጭነት እየተሳተፉ ያሉ አካላት በአስቸኳይ ከዚህ የጥፋት መንገዳቸው እንዲመለሱ እናሳስባለን፡፡ መንግስትም ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን፡፡
4) ይህ የሽብር ወንጀል እና የጸጥታ መደፍረስ ከመከሰቱ በፊት ጀምሮ ከፍተኛ የፕሮፖጋንዳ ሽፋን እየሰጡ ያሉ በክልል መንግስታት ባለቤትነት ስር ያሉ ሚዲያዎችን ጨምሮ በኦሮሞ እና ትግሬ ጽንፈኛ አካላት የሚዘወሩ ሚዲያዎች ከዚህ የጥፋት ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ እናሳስባለን፡፡ መንግስትም በእነዚህ የጥፋት መልእክተኞች ላይ ተገቢውን ሕጋዊ እርመምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን፡፡
5) ይህን የሽብር ድርጊትና እሱን ተከትሎ የተፈጠረውን የጸጥታ መደፍረስ በተመለከተ መረጃ የምታሰራጩ ወገኖች በከፍተኛ ኃላፉነትና ጥንቃቄ እንድታደርጉ እያሳሰብን በተለይም የሕዝባችን አንድነትና ደህንነት፣እንዲሁም የጸጥታ አካላትን እንቅስቃሴ በተለከተ ጎጅ መረጃዎችን ከመልቀቅ እንድትቆጠቡ እናሳስባለን፡፡
6) ሕዝባችን በተለመደው አስተውሎቱና ጀግንነቱ ነገሮችን በንቃት እንዲከታተል እያሳሰብን በአንድ ላይ በመቆም የተደገሰውን ተጨማሪ ጥፋት እንዲያከሽፍ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
በመጨረሻም ለሞቱት ወገኖቻችን ቤተሰቦችና መላው ሕዝባችን መጽናናትን እንመኛለን፡፡
አዲስ አበበ፣ ሸዋ
Filed in: Amharic