ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ
* ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ
* ‹‹በውስጡ ሰላም የሌለው ሰው ለሌላው ሰላም መስጠት አይችልም!››
– የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል የኦሮሞ አመራሮችን በአንድ ጥላ ሥር የሚያሰባስብ (ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ) እንዲመሰረት ተስማምተዋል
– በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል
በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የኢህአዴግና የኦዲፒ ሊቀመንበር እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የኦዲፒ ምክትል ሊቀ መንበርና የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀ መንበር አቶ ሌንጮ ለታን ጨምሮ በርካታ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተሳትፈዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መልእክት፥
• ‹‹አሁን ባለንበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ባህል እና ሀሳብ እንደሌለው መገዳደል እና መሰዳደብ ትክክል አይደለም፤ ፖለቲካችንን ማዘመን ይጠበቅብናል፡፡ ባሉን ሀሳቦች ላይ በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት ህጋዊ በሆነ መንገድ ፍላጎታችንን ከግብ ማድረስ እንችላለን፡፡
• የፖለቲካ ሀሳቦቻችንን ለህዝብ ለመግለፅ እና ለመታገል የሰው ልጅ መታሰር፣ መንገላታት እና መጎዳት የለበትም፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተወያየን መስራት እንችላለን። ይህ ሀሳብ እዚህ ብቻ የሚቀር ሳይሆን በመላ ሀገሪቱ ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችም የሚሰራ ይመስለኛል፡፡
• በውስጡ ሰላም የሌለው ሰው ለሌላው ሰላም መስጠት አይችልም፤ ለራሳችን የተሻለ ሀሳብ ከሌለን ለሌሎች ማካፈል እንችልም”ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ስለዚህ እየተወያየን እና እርስ በእርስ እየተማማርን የሀገራችንን ፖለቲካ ለማዘመን መወያየትና በጋራ መስራት በጣም ወሳኝ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
• በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ከ30 እና 40 ዓመታት በፊት ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎች አሁን ላይ እንደ አዲስ ጥያቄ ሆነው መቅረብ አይችሉም ያሉት ዶክተር አብይ፥ አሁን እያደገ ያለውን እና እንደ ሀገር ትልቅ ሃላፊነት የወሰደውን ህዝብ በምን መልኩ አዳዲስ ሀሳብ አምጥተን ሀገሪቱን ማሸጋገር እና በአፍሪካ ቀንድ የራሳችንን ሚና መጫወት አለብን የሚለው ላይ መስራት ይጠብቃል።
• የኦሮሞ ህዝብ ከእኛ የሚጠብቀው ይህንን ነው፤ የኦሮሞ ሽማግሌዎች የትገቡ ለሚለውም ምላሽ የሚሰጥ እና ለወጣቶችም ትምህርት የሚሰጥ ነው።
• ቀጣዩ ምርጫ ያለምንም ጥርጥር ግልጽ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ ይሆናል፤ ህዝቡም ከዚህ በኋላ በሃሳብ የፈለገውን አካል የመምረጥ እድል አለው።
– በኦሮሚያ ክልል ሰላምን አስመልክቶም በክልሉ የሰው ህይወት እየቀጠፉ ያሉ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ጥሪ የቀረበ ሲሆን፥ በክልሉ ግጭቶችን ለማስቆም እና ሰላምን ለማስፈን በጋራ ለማስራት ተስማምተዋል።
በመጨረሻም በስብሰባው ላይ የተካፈሉ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በስምምነት ሰነዱ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።