>
5:13 pm - Sunday April 19, 5311

የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ ... ፖለቲካ አዙሪት የተጠናወታት አገራችን፤  (ያሬድ ሀይለማርያም)

የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ … ፖለቲካ አዙሪት የተጠናወታት አገራችን፤ 
ያሬድ ሀይለማርያም
የዛሬዋ ኢትዮጵያ ለኤሊያስ እና ለጃዋር፤ 
በቅርብ ጊዜ የእስክንድር ነጋ እና የጃዋር ኢትዮጵያ በሚል አገራችን ሁለቱን ዜጎች በምን ሁኔታ እንደያዘቻቸው ጽፌ ነበር። አዎ ያ አይነቱ ስሜት ዛሬም የኤሊያስ ገብሩን የፍርድ ቤት ውሎ ስሰማ እና ጃዋር በኦሮሚያ ክልል ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን አፈራራሚና አስታራቂ ሆኖ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊት ቆሞ ሳይ “አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፤ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” የሚለውን አገር ይከዳቻቸውን፣ አብዮት የበላቸውን፣ ሕዝብ ባላየ ድምጹን ያላሰማላቸውን፣ ሹማምንት የፈረጠሙ ክርኖቻቸውን የፈተኑባቸእውን እነዛን ለአገር እና ለሕዝብ የታገሉ ምርጥ የኢትዮጵያ ጀግኖች እንጉርጉሮ አስታወሰኝ።
ኤሊያስ ገብሩ ደፋር እና ለእውነት የቆመ ጎበዝ ጋዜጠኛ ነው። አንደበቱ የተቆጠበ፣ አገር ወዳድ እና ሰው አክባሪ ነው። ለሰላም እና ለፍትህ ካለው ቀናዒነት ውጭ አንድም ቀን ጸብ ጫሪ፣ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ ወይም አመጽ ቀስቃሽ የሆነ ነገር ሲጽፍም ሆነ ሲናገር ሰምቼው አላውቅም። በተቃራኒው ግን በድፍረት መንግስት ላይ የሚያየውን ህጸጽ ከዘመነ መለስ እስከ ዘመነ አይብ ሲተሽ እና ሲነቅፍ አውቀዋለሁ። ዛሬ ፖሊስ በፍርድ ቤት በኤሊያስ ገብሩ ላይ ያቀረበውም ማስረጃ ይህንኑ ጥሩ አድርጎ ያሳያል። ኤሊያስ አብይንም ሆነ ማንንም ከመተቸት የሚሰንፍ ጋዜጠኛ አይደለም። ምግቱ ልክ ነው ወይም አይደለም የሚለው ሌላ ጉዳይ ሆኖ። ኤሊያስ ትግልን አንባገነኖች አፍንጫ ስር ሆኖ ነው የሚታገለው እንጂ እንደ ጃዋር በብዙ ሺህ ማይልስ እርቀት ላይ ሆኖ በስማ በለው አልነበረም። ለዚህም የከፈለው ዋጋ ጥሩ ማሳያ ነው።
በተቃራኒው ትግልን በኢንተርኔት ሲያጧጡፍ የነበረው ልጅ ጃዋር ወደ አገር ቤት ሳይገባም ሆነ ከገባ ወዲህ ከሚናገራቸው እና ከሚሰራቸው ነገሮች ከሦስቱ ሁለቱ ጸብ ጫሪ፣ ሕዝብን ሰዳቢ፣ አንድን ማህበረሰብ የሚያጥላላ፣ ጌጎችን ለወንጀል አድራጎት የሚያነሳሳ፣ አመጽን የሚቀሰቅስ፣ ሁከትን የሚያስፋፋ፣ የመንግስት ፖሊሲዎችን የሚያደናቅፍ፣ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን የሚጣጥላላ እኩይ ብሔረተኛ ነው። በጅዋር አድራጎት እና ቅስቀሰ የዜጎች ህይወት ጠብቷል፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት ወድሟል፣ ሌሎች በርካታ የወንጀል አድራጎቶችም ተፈጽመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩንም መስደብ የሚያሳስር ከሆነ እንደ ጃዋር ግጥም አድርጎ ልባሽ ጨርቃቸው እንኳ እንዳይሸጥ አድርጎ የሰደባቸው ሰው ያለ አይመስለኝም። ስልጣን እንዲለቁም ጠይቋል፤ ከመንግስቱ ኃይለማርያም ጎንም አስቀምጧቸዋል።
ዛሬ ለሕዝብ መብት የጋገለው እና ለሰብአዊ መብቶች የተሟገተው ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሃሰት ስማቸውን አጥፍተሃል በሚል በሽብር ወንጀል ተጠርጥቶ በእስር እየማቀቀ ነው። የንጹሃን ዜጎች ደም በእጁ ያለው ጃዋር ደግሞ ሲሰድባቸው በቆየው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊት ቆሞ አፈራራሚና ሸምጋይ ነው።
ፍትህ ለኤሊያስ ገብሩ እና ለሌሎች በተመሳሳይ መልኩ ታስረው ለሚማቅቁ ዜጎች!
ፍርድ ጀዋር መሃመድ ለፈጸማቸው የወንጀል አድራጎቶች!
ፍትህ ዛሬም በብልሹ አሰራር ለሚማቅቁት የፖሊስ፣ አቃቤ ሕግ እና የፍርድ ተቋማት!
Filed in: Amharic