>
12:22 pm - Sunday December 4, 2022

"ኢሬቻ ከገዳ ስርዓት እሴቶች የሰላም እና የአንድነት ምልክት ነው!" (ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ )

“ኢሬቻ ከገዳ ስርዓት እሴቶች የሰላም እና የአንድነት ምልክት ነው!”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የኢሬቻ በአልን አስመልክቶ ያስተላለፉት መልዕክት
የተከበራችሁ የኦሮሞ ሕዝቦች። ከሁሉ አስቀድሜ እንኳን ለዚህ የተከበረ የምስጋና፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የእርቅና የይቅርታ በዓል በሰላም አደረሳችሁ። ኢሬቻ የምስጋናና የምልጃ በዓል ነው።
የኦሮሞ ሕዝብ ሁሉን ነገር ለፈጠረው፤ ምድርንና ሰማይን፣ ወንዝንና ባህርን፣ ቀንንና ሌሊትን፣ ብርሀንና ጨለማን፣ ሕይወትና ሞትን፣ ክረምትንና በጋን፣ ዝናብንና ሐሩርን፣ ዕጽዋትን፣ እንስሳትንና ሰውን ለፈጠረ፤ ሁሉን ነገር ማድረግ ለሚችል ዋቃ (አምላክ) ምስጋናና ክብር የሚያቀርብበት ሥርዓተ-በዓል ነው።
የኦሮሞ ሕዝብ በኢሬቻ በዓል ላገኘው ፀጋና በረከት፣ ሰላምና ደስታ፣ ጤናና ዕድሜ፣ ፍቅርና ክብር፣ ብርሃንና ተሥፋ ፣ከአንድ ወቅት ወደ ሌላ ወቅት በአጠቃላይ ከዘመን ወደ ዘመን በሰላም ላሸጋገረው አንድ አምላኩ- ለዋቃ ምስጋና የሚያቀርብበት በዓል ነው። ኢሬቻ የሰላም በዓል ነው።
በዚህ በዓል ለሰላም፣ በሰው ልጅና በተፈጥሮ መሀከል ላለው በጸጋና በይቅርታ ለተመላው ግንኙነት፣ ለወላድነትና ለልምላሜ ፣ ለእንስሳት፣ ለዕጽዋት፣ ለሕጻናት፣ ለቤተሰብ፣ ለጎሳ፣ ለአገር፣ ለመላው ዓለምና ለመላው የሰው ልጅ ሰላምና ደህንነት የኦሮሞ ሕዝብ ፈጣሪውን ዋቃን ያመሰግናል፣ ይማጸናል፣ ይመርቃል።
በመሆኑም ኢሬቻ የምርቃት፣ የተማጽኖ፣ የዕርቅ፣ የይቅርታ፣ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት፣የምስጋና እና የበረከት በዓል በመሆኑ የሰላም በዓል ነው። እሬቻ መነሻው እና መድረሻው የመከበሩም አልፋ እና ኦሜጋ ሰላም ነው- ይህንን ይዘን እሬቻን ስንበይነው እሬቻ ማለት ሰላም ነው፡፡
ኢሬቻ የቃልኪዳን በዓል ነው። የኦሮሞ ሕዝብ የጾታ፣የእድሜ፣ የፖለቲካ አመለካከትና የሃይማኖት ልዩነት ሳይገድበው የጋራ ባህሉንና ታሪኩን፣ አንድነቱን፣ ወንድማማችነቱንና እህትማማችነቱን የሚገልጽበት ከመሆኑ ባሻገር ባህሉን ለማደስ፣ ለማጠናከር፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ቃል የሚገባበት ለፈጣሪ እና ለተፈጥሮ ምስጋናውን አቅርቦ ለቀጣይ ዘመኑም ለደግደጉ ብቻ ቃል ኪዳኑን የሚያጸናበት ሰላም ማጠንከርያ እና ቃልኪዳን ማሰርያ ሥርዓተ-በዓል ነው።
በዚህ ረገድ እንዲህ ያለ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ የአንድ ሕዝብ የማንነት መገለጫና ይህ ማንነት ከትውልድ ወደትውልድ እየተላለፈ ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርግ ለመሆኑ ኢሬቻ ሕያው ማረጋገጫ ነው፡፡ ስለሆነም ለኦሮሞ ልዩ የገጽታ መግለጫና የደስታ በዓል ሆኖ ከጥንት ጀምሮ በየዓመቱ ሲከበር ኖሯል፤ ዘንድሮም በዚህ ዘመን የተሻገረ ስበቱ እና ውበቱ በግሩም ድምቀት ይከበራል፡፡
ፍልስፍናው ረቂቅ፣ ሕግጋቱ ፅኑ፣ ሥርዓቱ ብርቱ፣ ተሳታፊው እልፍ አእላፍ ነው፤ ኢሬቻ!! ኦሮሞ በኢሬቻ የሕይወትና ሞት ቅብብሎሽን (ክረምት አልፎ ጸደይ ዞሮ መምጣቱን፣ ጭለማ አልፎ የብርሃን ሸማ መተካቱን) ማሬዎ ማሬዎ በማለት የዋቃን ድንቅ ሥራ ያመሰግንበታል፡፡ እናም ኢሬቻ ይህ ተፈጥሮአዊ ሕግ ሳይዛነፍ ዓመታዊ ዑደቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ለማመስገንና ለመለመን የሚከበር ድንቅ በዓል ነው። የተራራቀው ሊቀራረብ- የተጠፋፋው ሊሰባሰብ- የደፈረሰው ሊጠራየጨለመውም ሊበራ… የዋቄፈታ ቀን ሲደርስ አመስጋኙ የኦሮሞ ህዝብ በፍጹም ምስጋና እና እልልታ ከመልካው ዳርቻ ይገናኛል፡፡
የእሬቻ በዓል የኦሮሞ ልዩ ውበት እና የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እንዲሁም የውጭ ዜጎች እና ቱሪስቶች በደስታ እና በፌሽታ የሚሳተፉበት ልዩ የአንድነት ማጠናከርያ ሥርዓት ነው።
ኢሬቻ የትውልዶች ቅብብሎሽ- የአብሮነታቸውም ህልው መሆን ድንቅ ዋቢ ማኅተም ነው! በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የገዳ ሥርአት ከፍልስፍናዊ መሠረቱ ጋር የዲሞክራሲ ሥርዓት እንደምን በእድሜ እኩዮች መብት፣ ግዴታና ትውልዳዊ ሚናዎች ሳይዛነፍ እንደሚተገበር ይንፀባረቁበታል፤ ይከናወንበታል፡፡
ታላቅ ታናሹን የማብቂያ፤ ታናሽ ደግሞ ታላቁን የማክበሪያ በዓል ሆኖ ለትውልድ እየተወራረሰ ዛሬ ላይ የደረሰው የኢሬቻ በዓል ከአምልኮነቱ ባሻገር ለዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት ሁነኛ ምንጭ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በዚህም ሂደት የአቃፊነት እና የአክባሪነት እሴቶቹን ለትውልድና ለዓለም አበርክቷል፡፡
ኢሬቻ በሕብረትና በአንድነት ተያይዘው የሚያከብሩት በዓል ነው። የክረምቱ ጨለማ አልፎ ብርሃን የሚሆነው፤ ምድር ከጎርፍና ከወጀብ ተላቃ የምትለመልመው ለአንድ ሰው ወይም ለአንድ ወገን ብቻ አይደለምና በረከትና ጸጋውን ሁሉም በጋራ የሚቋደሰው ነው፡፡ ለዚህ የጋራ በረከትና ጸጋ ምስጋናና ምርቃት የሚቀርበውም ለየብቻ እና በተናጠል ሳይሆን በሕብረትና በአንድነት ነው፡፡
እናም የኢሬቻ በዓል ለጋራ ብልጽግና በአንድ ድምጽ ምስጋና የሚቀርብበት ነው፡፡ የዘንድሮውን የኢሬቻ በዓል ስናከብር የኢሬቻ የሰላምና የአንድነት ተምሳሌትነት በአንድነት በማሳየት እና ለዘመናዊ ዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ መሰረት የሆነው የገዳ ፍልስፍናና ሥርዓት ለአገራችን ሰላምና ብልፅግና የምናውልበት እንደሆነ ደግመን ደጋግመን በማረጋገጥ ነው፡፡ እንዲሁም በዓሉ ቱባ የሆነውን የአገራችንን እና የተቀረው ጥቁር ሕዝብ እሴትን ለዓለም በግልጽ የምናሳይበትም ጭምር ነው፡፡ ከገዳ ሥርዓታችን ባገኘነው የመመካከር፣ የመግባባት፣ እና የአመራር ጥበብም ትውልድ የተሰዋለትን የሀገር ልማት የማሳለጥ ዓላማ ለመጠበቅ በዓሉ ቀን ከሌሊት ለመትጋት ቃል የምንገባበትና ለብልጽግናችን ተሥፋ የምንሰንቅበት ነው፡፡
ኢሬቻ ከኦሮሙማ መገለጫዎች ሁሉ ደማቁና አሳታፊው ነው። ኦሮሙማ አካታችነት ነው፡፡ ኦሮሙማ በግልጽ መወያየትና በሀሳብ ልዕልና መግባባት ነው፡፡
ኦሮሙማ ይህኛው ትውልድ ዛሬ ላይ ሆኖ ነገን ለቀጣዩ ትውልድ የሚገነባበትን ታሪካዊ ሚና መጫወት ነው፡፡ ኦሮሙማ ከሜልባ እስከ ምችሌ ያለው ሥልጣን መተካካትን ዛሬ ላይ ሆነን ነገን መገንባት ይቻል ዘንድ ተሞክሮን የምንለዋወጥበት ሥልት ነው፡፡
ኢሬቻ ወደ ነባር ኦሮሙማ ሥርአቶች በመመለስ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ቃል ኪዳን ለመግባት የምንሰባሰብበት የህብረታችን በአል ነው፡፡ ኦሮሙማ ከመራራቅ መቀራረብ፣ ከመወቃቀስ መተባበር ፣ ተኳርፎ ጀርባ ከመስጠት ተናግሮ መደማመጥ እንደመሆኑ ይህን ፀጋ ያለበሰንን ፈጣሪን ለማመስገን የኢሬቻን በዓል ስናከበር በዋቃ በረከት ተሸልመን ነገን ልንገንባ፤ መፃይ ጊዜያችንን ልናሳምር ከራሳችን ጋር ቃል ገብተን ሊሆን ይገባል፡፡
ኢሬቻ ንፅህና ነው። በኦሮሙማ ቂም ይዞ ፀሎት፣ ሳል ይዞ ስርቆት አይታሰብም፤ ቦታም የላቸውም፡፡ ከምስጋና በፊት ለተግባርና ልቦና ንፅህና ልዩ ስፍራ ይሰጣል፤ በንጹህ ልብ ፈጣሪውን የሚለምን ኦሮሞ የወደቀውን ያነሳል፡፡ ከጥላቻ ፍቅርን ይመርጣል፡፡ ጉዞው በጥበብ እና በትህትና ነው፡፡
ከተንኮል ይልቅ በጎነትን መርጦ ቅንነትን እንደ መሳርያ ይጠቀማል፡፡ ኦሮሙማ አለመግባባትን በምክር እና በንግግር መፍታትን ይመርጣል፡፡ ካመረረና የመረረው ሲገጥመውም ተራግሞ እርጥቡን ያደርቃል፡፡ በኛ በአሸናፊዎቹ ትውልድ የማይቻለውን እንደሚቻል ላሳየ ትውልድ፣ ጥላቻ ታሪከ ሆኗል፡፡ የመርገምትን ዘመን ተሻግረናል፤ ዛሬ ላይ የደረሰበት የትግል ምዕራፍም ያሉንን ጥሩ ተሞክሮዎች ቀምረን በመደጋገፍ የምንተባበርበት ጊዜ ነው፡፡
ኢሬቻ በኦሮሞ ሕዝቦች እና ሌሎች የኢትዮጵያ ወንድምና እህት ሕዝቦች ትግል ዛሬ ላይ የደረስንበትን ምዕራፍ በውል ተረድተን፣ ያገኘነውን ቆጥረን ማወቅና ጠብቀን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የምንተባበርበት በአል ነው፡፡
ኢሬቻ አገር የመገንባትና የማልማት ኃላፊነትን በትጋትና በነባር ኦሮሙማ እሴቶቻችን ወደ ላቀ ድል የምንሻገርበት የቃልኪዳን በዓላችን ነው። ይህ በአል ከመቶ አመታት በላይ ርቆን ዛሬ ላይ በእጃችን ላይ የገባው ከማንም ክልከላ ነጻ ሆኖ የትውልድን ታሪካዊ ሚና ለመወጣት የመታደል ወርቃማ አጋጣሚ ነው፡፡ ይህ እድል የኦሮሞ ሕዝብ በአሸናፊነት ሥነ ልቦና እና በላቀ ሃሳብ የፍቅር አምባነቱን ማረጋገጥ የጀመረበት ሂደት እንደመሆኑ ካወቅንበትና ዋጋ ከሰጠነው ለመላው ሕዝብ አንድነትን ለማረጋገጥ፣ ሰላም ለማስፈን፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ እውነተኛ የፌደራሊዝም ሥርዓት ለመገንባት ፣ ዲሞክራሲን ለማስፋፋት እና መሰል ጉዳዮችን ለመተግበር ጉልበት ሰጪ ሥንቅ ሆኖ ያገለግላል፡፡
ኢሬቸ ሰላም ነው፣ ሰላማችን በእጃችን ነው፡፡ ሰላማችንን መጠበቅ ነባር እሴቶቻችንን ማጠናከር ነው፡፡ በላቀ ሃሳብ የበለጠ ድልን ማሳካትም ነው፡፡ ሰላማችንን ካረጋገጥን የአገር ግንባታ ሂደትም ዕውን ይሆናል፡፡
ኢሬቻ የገዳ ፍልስፍናን፣ እሴቶችንና አስተምሮዎችን ለአገር ግንባታ ለማዋል ቃል የምንገባበት ነው፡፡ ኢሬቻ ሁሉም ሃይማኖትና፣ የእድሜ ደረጃና አመለካከት ያላንዳች ልዩነት የሚሳተፍበት የብዝሀነትና የአንድነት መድረክ ነው። በበዓሉ ላይ ልዩነት እንደውበትና ጥንካሬ ተወስዶ የኦሮሞ አንድነት፣ /ኦሮሞነት/ ይወደሳል፣ ይዘመራል፣ ይገነባል፣ ይታደሳል፣ ይጠነክራል። የአንድነት፣ የፍቅር፣ የወንድማማችነት፣ የመቻቻል ቃል ኪዳን ይገባል፤ ይታደሳል። የበለጠ አንድነት ይፈጠራል፤ ከዘመን ወደ ዘመንም ይሻገራል፡፡
የኢሬቻን ልዩ ባህሪ ወስደን ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያን ለመገንባትና የብሔር ብሔረሰብ ብዝሀነትን መጠቀም አለብን፡፡ ኢሬቻ የተስፋና የመሻገር በዓል ነው። ከአንድ ወቅት ወደሌላ ወቅት መሻገሪያ ነው፤ ከክረምት ወደ ቢራ (ጸደይ)። የክረምት ወራት ከባድ ወቅት ነው፤ ብዙ ተግዳሮቶች አሉት– ወንዞች ይሞላሉ፤ ደራሽ ውሀ ሰውና እንስሳ ይወስዳል፤ በረዶ ይጥላል፤ መብረቅ ይወርዳል፤ ጨለማው ብርቱ ነው፡፡ ጨረቃ፣ ከዋክብትና ጸሐይ በጥቁር ደመና ይጋረዳሉ፡፡
ከወንዝ ማዶ ካሉት ዘመዶች ጋር መገናኘት ይቋረጣል፤ ገበያ መሄድ ይከብዳል። የበጋ ወቅትም ብዙ ተግዳሮቶች አሉት… መሬት በድርቀት ይሰነጣጠቃል፤ ዛፎች ቅጠሎቻቸው ይረግፋል፤ የግጦሽ ሳር ይደርቃል፤ ከብቶች ይከሳሉ፤ አውሎ ንፋስ ይበረታል። እነዚህ ፈታኝ ሁኔታዎች አላፊዎች ናቸው፤ ተስፋ የሚያስቆርጡ የዓለም ፍጻሜ አይደሉም። ከማዶ ብሩህ ተስፋ አለ፤ ከክረምቱ ባሻገር የተዘራው ቡቃያ ፍሬ ያፈራል፣ አበቦች ይፈካሉ፣ ምድር አረንጓዴ ትለብሳለች፣ ከናፈቁት ዘመድ ጋር መገናኘት፣ ገበያ መውጣት፣ መነገድ፣ ከአድማስ ባሻገር በተስፋ ይታያሉ።
ኢሬቻ ፈተናዎቹን በጽናት ተቋቁሞ ወደ ብሩህ ጊዜ በተስፋ የመሻገር በዓል ነው። በኦሮሞ ንጽረተ ዓለም (worldview) ውስጥ ጸለምተኝነት የለም፤ በተስፋ የተሞላ ነው። የኢሬቻ የሰላም፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የእርቅ፣ የመቻቻል፣ የወንድማማችነት እሴቶች የሽግግሩን ፈተናዎች የሚያሻግሩና ወደብሩህ ጊዜ የሚያደርሱ ናቸውና የአገራችንን መፃይ ጊዜ የምናይበት ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ በሽግግር ወቅት ውስጥ ነች።
በሽግግር ወቅት ደግሞ ፈተናዎች ይበዛሉ። ያለመተማመን፤ ተጠራጣሪነት፣ ጨለምተኝነት፤ ሕገ ወጥነት ያጋጥማሉ። በዚህ ወቅት የኢሬቻ የአምልኮ ፍልስፍና የሚያስተምረን የእነዚህ ሁኔታዎች መከሰት የዓለም ፍጻሜ፣ ወይም የአገር መፍረስ እንደሆኑ አይደለም። ከውጣ ውረዶቹና ከፈተናዎቹ ባሻገር ተስፋ አለ፤ የተሻለ ዘመን የተሻለ አገር እንደሚኖረን ማሰብ ያስፈልጋል፤ ለዚህም በጽናት በተስፋ በጋራ በመቻቻል በወንድማማችነት መንፈስ መቆምን ኢሬቻ ያስተምረናል። በዚህ አጋጣሚ ፈተናዎቹን በመቻቻል፣ በመረዳዳት፣ በመደመር፣ በእርቅ፣በይቅርታና በሰላም መሻገርን መርሆ እናድርጋቸው፡፡
ኢሬቻን አገራዊ የምስጋና በዓላችን ነው። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ሌሎች ብዙ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በመሆን ኢሬቻን ማክበር ጀምረዋል። ኢሬቻ የብሔር ልዩነትን ግንብ የሚያፈርስ የአብሮነት ድልድይ ነው። በዓሉን ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ማክበር የጀመሩት ሕዝቦች ከበዓሉ እሴቶችና ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር የሚጋሩት የጋራ እሴቶች እንዳሉ ያሳያል። በመሆኑም ኢሬቻን በአገር አቀፍ ደረጃ የመላ ኢትዮጵያውያን የጋራ የምስጋና በዓል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢሬቻ በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መሀከል የበለጠ ትስስርና መግባባትን ይፈጥራል።
በኢሬቻ ባህልና ወጋችንን እናሳድግበት። ከብዝሀ ባህላችን ውስጥ የምንጋራቸውን የእርስ በርስ ትስስርና ወንድማማችነትን የሚገነቡትን እሴቶች አጉልቶ በጋራ ማወደስ ለአገራዊ አንድነት ግንባታ ትልቅ ፋይዳ አላቸውና ታላቁን ክብረ በአል ለዚህ ታላቅ አላማ እንጠቀምበት። በዚህም መሰረት ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ኢሬቻን በጋራ እንዲያከብሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
የክረምቱን ዶፍና ጨለማ ያሸጋገረን ዋቃ አምላክ ይመስገን ፣ ኢሬቻ የፀደይ በረከት የምንቋደስበት፣ ወደ አዲስ የድል ምዕራፍ ለመሸጋገር ቃላችንን የምናድስበት እና በፍቅር በማቀፍ ጥላቻን የምናሸንፍበት በዓል ይሁንልን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
መስከረም 22 ቀን 2012 ዓ.ም
Filed in: Amharic