>

"የሰበረም ሆነ የተሰበረ ህዝብ አናውቅም!!!" (አቶ መላኩ አላምረው)

“የሰበረም ሆነ የተሰበረ ህዝብ አናውቅም!!!”
አቶ መላኩ አላምረው 
“የሚሰበር ነፍጠኛ እንዲሁም የተሰበረ ሕዝብ አናውቅም!!!
* የተሰባበረች ሀገር ጠግነው በክብር ያቆሙ እንጅ የትኛውንም ሕዝብ የሰበሩም ሆነ በማንም የሚሰበሩ ነፍጠኞች አልነበሩም፤ የሉም፤ አይኖሩምም!!!
ለሀገር ዳር ድንበር መከበር አጥንታቸው የተስበረና ደማቸው የፈሰስ እንጅ የራሳቸውን ወንድሞች የሰበሩ ነፍጠኞችን አናውቅም።
እኛ የምናውቀው ነፍጠኛ መይሳውን አፄ ቴዎድሮስን ነው። እርሱ ቅስሟ ተሰባብሮ የተበተነችን ሀገር ለመሰብሰብ ላይ ታች ሲዋከብ በገዛ ወገኑ ሸፍጥ በመስዋእትነት የነፍሱን ምድራዊ ጉዞ ሰብሮ ወደ ሰማይ ከፍታ በመሸኘት ራሱን ለሀገር የሰጠ የምንጊዜም ጀግናችን የልባችን ንጉሥ የእጃችን ሰንደቅ ነው።
እኛ የምናውቀው ነፍጠኛ ተሰባብራ የተበታተነችን ሀገር ጠጋግኖና የመላው ኢትዮጵያውያንን ወኔ ሰብስቦ በዐድዋ ተራሮች ላይ የጠላት ፋሽስትን ቅስም ሰባብሮ በክብር ማማ ላይ ለዘለዓለም ቀጥ አድርጎ ያቆመንን አባ ዳኘው እምዬ ምኒልክን ነው።
እኛ የምናውቃቸው ነፍጠኞች በዐድዋ ተራሮች ስር ከጠላት ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው ፋሽስትን ከእግር ከአንገቱ ሰባብረው ማንም በማይሰብረው የነፃነት ምሶሶ ላይ የነፃነት ሰንደቅ ያውለበለቡልንን እነ ራስ አሉላ አባነጋን፣ እነ ፊታውራሪ ገበየሁን፣ እነ ባልቻ ሳፎን፣ እነ ንግሥት ጣይቱን፣ እነ ንጉሥ ሚካኤልን፣ እነ ራስ መንገሻ ዮሐንስን፣ እነ ራስ መኮንንን፣ እነ ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስንና ሌሎች እልቆቢስ ጀግኖችን ነው።
እኛ የምናውቀው ነፍጠኛ ጠላት ጥልያን ዳግም በቀል ተጠምቶ ሲመጣ ነፍጠኞችን አስተባብሮ ፋሽስትን ቁም ስቅሉን አሳይቶ፣ በዱር በገደሉ እየሰባበረ በመጣል ነፃ ምድርን ለንጉሡ ያስረከበውን አባኮስትር በላይን ነው።
እኛ የምናውቀው ነፍጠኛ በጠላት ምድር በሮም አደባባይ የኢትዮጵያ ሐውልት ተሰብሮ ሰንደቅ አላማዋ ሲረገጥ ሲያይ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ ጎራዴን ከጠላት እጅ ነጥቆ ፋሽስትን ከእግሩ ከአንገቱ ከወገቡ እየሰባበረ የጣለውን ዘርዓይ ደረስን ነው።
እኛ የምናውቀው ነፍጠኛ በምድረ ጥልያን የውጭ ዜጎችን አስተባብሮና የነጭ ጦር መርቶ ጠላትን እየሰባበረ ድባቅ በመምታት የሀገሩን ሰንደቅ ባልተሰበረ ዓላማ ላይ ከፍ አድርጎ በማውለብለብ ነጮሽ ለዜግነት ተንበርክከው የለመኑትን ጥቁሩን አብዲሳ አጋን ነው።
እኛ የምናውቃቸው ነፍጠኞች ሀገር በቅኝ ተገዝታ የሕዝባቸው ቅስም እንዳይሰበር ነፍጥ አንግበው የተዋደቁትን እነ አቢቹን፣ እነ መንገሻ ጀምበሬን፣ እነ ሽፈራው ገርባውን፣ እነ ኃይለየሱስ ፍላቴን፣ እነ ራስ አበበ አረጋይን፣ እነ ሸዋረገድ ገድሌን፣ እነ ጃጋማ ኬሎን፣ እነ ደጃዝማች ዘለቀ ደስታንና ተዘርዝረው የማያልቁ አእላፍ ጀግኖችን ነው።
እኛ የምናውቃቸው ነፍጠኞች አሁን አለን የምንለውን ባህል፣ እምነት፣ ትውፊት፣ ቅርስና ማንነት ከቅኝ ገዥዎች ጠብቀው ያቆዩልንና በዓላትን ባከበርን፣ አምልኳችንን በገለጽን፣ ቅርሳችንንም ባየን/ባሳየን ቁጥር በክብር ልንዘክራቸው በምስጋና ልናስባቸው የሚገቡ፣ በአጥንታቸው ስብርባሪ የጠላትን እግር እየወጉ ነፃ ምድርን እስከ ውብ ባህልና እምነቱ ያወረሱን የሀገርና የሕዝብ ጠበቃ ባለውለታዎቻችን ናቸው።
የራሱን ወንድም ሕዝብ የሰበረም ሆነ በወንድሙ የተሰበረ/የሚሰበር ነፍጠኛ አልነበረም፤ አላየንም፤ አናውቅምም።
ይልቅ ያልነበረና የሌለ የሽንፈት ታሪክን በመተረክ የሕዝባችንን ልብ አንስበር። በጀግኖች የቆመችን ሀገር አቃጠን መያዝ አቅቶን የምንችለውን ለመሸከም ስንውተረተር ተሰባብረን ትውልድንም እንዳናሰብር ለራሳችን ያለንበትን ሀገራዊ ቁመና እናቃጠው!!!”
እናመሰግናለን!
Filed in: Amharic