>

የሚካኤል ጎርቫቾቭ ፕሮስትሮይካና፤ የአብይ አህመድ የመደመር ፖለቲካ !! ( አሥራደው ከፈረንሳይ )

የሚካኤል ጎርቫቾቭ ፕሮስትሮይካና፤ የአብይ አህመድ የመደመር ፖለቲካ !!

አሥራደው ከፈረንሳይ

መንደርደሪያ :
* ” አገሬ ተባብራ – ካልረገጠች እርካብ፤ ነገራችን ሁሉ – የዕንቧይ ካብ: የዕንቧይ ካብ “ (ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ)
* ” የጨው ተራራ ሲናድ: ሞኝ ይስቃል፤ ብልህ ያለቅሳል “ (ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን)

ማስታወሻ :

ወገኖቼ ዛሬም መጣጥፌን በጥያቄ መጀመሩን መርጫለሁ፤ ጥያቄዎቹ በኔ አይምሮ ብቻ የሚመላለሱ ሳይሆን፤ የአገር ጉዳይ ያገባናል: ወይም ግድ ይለናል የሚሉና፤ በጋራ ወይም በማህበራዊ እሳቤ በማመን፤ ከጎሠኝነትና ከጎጠኝነት ይልቅ፤ የተጎናጎነው አብሮነታችን፤ ለአገርና ለዜጎች ደህንነት ይበጃል የሚሉ ወገኖቼም ጭምር በመሆናቸው ነው ::
እናም፤ የሚካኤል ጎርቫቾቭ ፕሮስትሮይካና፤ የአብይ አህመድ የመደመር ፖለቲካ: ምንና ምን ናቸው ?!
* አጀማመራቸው * አካሄዳቸው * መጨረሻቸውስ ?!
* ሚካኤል ጎርቫቾቭ፤ ሶቪየት ህብረትን እንዳፈራረሰ፤ አብይ አህመድም ፤ ኢትዮጵያን ላለማፈራረሱ ምን ዋስትና አለን ?!
* በዚህ ድርጊት ተጠቃሚው ማን ነው ?! ተጎጂውስ ?!
ዛሬ በአገራችን ኢትዮጵያ ላይ ያንጃበበው የዘርና የጎሣ ጆፌ (ጥንብ አንሳ)፤ ጥርሶቹ የተሳሉ፤ ጥፍሮቹ የደነደኑ፤ ዓይኖቹ ያፈጠጡ፤ ሆዱ የመቃብርን ያህል የሰፋና ጥልቅ ጉድጓድ የሆነ በመሆኑ፤ ነገ አገራችን የኛ ለመሆኗ ዋስትና የለንም ::
– የዘርና የጎሣ ፖለቲካው -የፖለቲካ ሱቅ በደረቴዎች ብዛት – የሃይማኖት ሽኩቻው – የምጣኔ ሃብቱ (ኢኮኖሚው ውድቀት) – የውጭ እዳው ክምር – የወጣቱ ሥራ አጥነት – በዜጎች መሃል የተገነባው የዘር ግንብ – የመፈናቀል አደጋ – የፍትህ እጦት – የኑሮ ውድነት – የትምህርት ጥራት ዝቅጠት፤ – ለውዳሴ ፖለቲካ እንጂ ፤ ለትችትና ለገንቢ ሃሳቦች በር መዘጋት፤ – የእስር ቤቶች አፍ ዳግም በስፋት ተከፎ: ጋዜጠኞችንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ዜጎችን መዋጥ ፤ – ሕዝብ በሚከፍለው ግብር፤ የሚተዳደሩ፤ የዜና ማሰራጫዎች ዘወትር የባለጊዜዎች ፕሮፓጋንዳ መርጫ መሳሪያ ብቻ መሆን፤….. ወዘተ
በዚህ ላይ፤
በየሆቴሉ የሚቀለቡ ዝሙት ፖለቲከኞች፤ የታሪክ ክህደትና ድለዛ፤ የሕዝቡ አድፋጭነት: ሌላው ሞቶለት እሱ ለመኖር ፤ የምሁራን አገርና ወገንን ከመታደግ ይልቅ ለሆድ አዳሪነት መሽቀዳደም፤ የአገር ሃብት በተደራጁ ሌቦች ምዝበራ፤ የህወሓት ሴራና ድንፋታ፤ የኦህዴድ ባለ ተረኝነት፤ የኦነግ/ኦህዴድ ጥምር ዛቻና ዘረፋ፤ የብአዴን ዕውር ድመትነት ሎሌነት (አሽከርነት)፤ የአንድነት ሃይሉ ተኝቶ ማንኮራፋት፤ የከተሜው ዳተኝነት፤ ተደማምረውበት አገር እየታመሰች ነው ::
የብአዴን ዕውር ድመትነትና ሎሌነት፤
የህወሓት የኩበት ጥፍጥፍ የሆነው ብአዴን ተብዬ ድርጅት፤ በኔ ዕይታ ጓያ እንደሰበረው የማሽላ ጠባቂ ይመሰላል::

ጓያ የሰበረው የማሽላ ጠባቂ፤ እግሩ ከመሰበሩ የተነሳ፤ ማሽላውን እየቀነደሉ የሚበሉትን ዝንጀሮዎች ሮጦ ሄዶ ማባረርና ማዳን ስለማይችል፤ የወፍ መጠበቂያ ሟሟው ላይ እየተቁነጠነጠ፤ ወዮልህ! መጥቼ ጉድህን ባላሳይህ እያለ ከመፎከር ባሻገር፤ ከሟሟው ወርዶ ማሽላውን በዝንጀሮዎች ከመበላት አያድንም ወይም አይከላከልም :: ብአዴንም ይኸው ነው ::

እልፍ ብሎም ፤
ያልታደለች ፍየል – አስር ትወልዳለች፤ ልጆቿም ያልቃሉ – እሷም ትሞታለች ::
እንዳለው ያገሬ አዝማሪ፤ ብአዴን እያደረገና እያስደረገ ያለው ይኸው ነው ::
ህግ በጎሣ መነጥር እየታየ በሚተረጎምባት አገር ፤ የዜጎችና የአገር ደህንነት ይኖራል ማለት ዘበት ነው ::
ህወሓት ትግራይን የጎረቤት አገር ካደረገ ይኸው ሁለት አመት ሊያስቆጥር ነው፤ እራሱ የማያከብረውን ህገ መንግስት፤ አክብሩልኝ እያለ ጭራሹን በመደንፋት፤ እኛ የሌለንበት ለውጥ ሊኖር አይችልም እያሉ ይፎክራሉ :: በእጅጉ የሚያሳዝነውና አጠያፊው ጉዳይ፤ የህወሃት ደንደሳም ሌቦች በትግራይ መሽገው ከህግ በላይ የመሆን ቡራኬ (ኢሙኒቲ) ተቸሯቸው፤ በአንፃሩ በአዲስ አበባ፤ በጎንደር፤ በጎጃምና በወሎ…..ወዘተ እስር ቤቶች አፋቸውን በሰፊው ከፍተው ወገኖቻችንን እየዋጡ መሆናቸው ነው ::

ዓብይ አህመድ በጌዴኦ፤ በላፍቶ፤ በሱሉልታ፤ በሰላሌ፤ በጎጃም፤ በጎንደር፤ በአፋርና በሌሎች የአገሪቱ ክፍል: በኦነግ/ኦህዴድ ጥምር ደባ ሲፈናቀሉ እያየና እያወቀ ፤ በኢትዮጵያ ስም እየማለ፤ ዝምታን በመምረጡ ፤ የሁንዱማ ኬኛ የዘርና የጎሣ ባለተረኞችን ልብ አሳብጧል፤ ብሎም ምኞታቸውንና ድርጊታቸውን ወደ ማጽደቁ ተቃርቧል ::

አብይ አህመድና አጋሮቹ የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም ብቻ ለማስከበር ነው የቆሙት፤ ወይስ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም ?! ወቅቱ ጥርት ያለ መልስ የሚያስፈልግበት ላይ በመሆናችን ሕዝብ መልስ ይሻል :: አብይ አህመድ ነገ ለልጆቹ የሚያወርሳቸው ኢትዮጵያዊነትን ነው ወይስ ኦሮሞነትን ??!! እኛስ ??!!

Filed in: Amharic