>

በኢሬቻ ቀን የተከሰተው ብሄራዊ አደጋ (አብርሃ በላይ)

በኢሬቻ ቀን የተከሰተው ብሄራዊ አደጋ
አብርሃ በላይ
ዋሽንግተን ዲሲ ነው። ጊዜው ደግሞ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት እንደተጀመረ። አሜሪካና ሩዋንዳ ጦርነቱን ለማቆም ይሯሯጣሉ። ታድያ አንድ ሬስቶራንት ውስጥ ከአንድ የሩዋንዳ ዲፕሎማት ጋር ስለተቀጣጠለው ጦርነት ወሬ ጀመርን። ወድያው ጦርነቱን ከአሜሪካ ጋር ሆነው ለማስቆም ከሚሯሯጡት አንዱ መሆኑን ገባን።
አሜሪካና ሩዋንዳ ሻብያ ጠብ ጫሪ መሆኑን አውቀው፣ ስምምነቱ ለኢትዮጵያ በሚጠቅም መልኩ እንዲሆን ተናበዋል። “እኛ ኢትዮጵያን ለመርዳት እንሰራለን፣ ለአካሄዳችን የእግር ረመጥ የሆነብን ግን መለስ ዜናዊ ነው” አለን። ገረመን እንጂ አልደነገጥንም። ጠላት ምን ጊዜም ጠላት ነውና።
ቀጥሎ፣ ዲፕሎማቱ “ግን መለስ ኢትዮጵያዊ ነው ትላላችሁ?” አለን። “ከሆነ፣ ምከሩት። ካልሆነ ግን አስወግዱት! ሀገራችሁን እስኪያፈርስ ድረስ አትጠብቁት።” አለን። ይኸኔ ክው አልን። ከኛም አልፈው እነሱም አደገኛነቱን በልተውታል አልን። መለስ ግን የሚያስወግደው ጠፍቶ ጦርነቱ ማክሸፍ ብቻ ሳይሆን፣ ሀገራችንም ሲያፈርስ ኖረ። ያኔ ገና በጥዋቱ ጠላት ቢወገድ ኑሮ፣ ዛሬ በዘር ፖለቲካ የተዳከመችው ኢትዮጵያ የማንም መዘባበቻ አትሆንም ነበር።
በሰበብ አስባብ፣ የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተን ንግግር የሚያደርጉ ስልጣን ላይ ወተዋል። ወገኖቻችን ናቸው ብለን አምነን ስንኖር፥ የውጭ ወራሪ ይመስል “ነፍጠኞችን ሰብረን ትልቁን ከተማ ለመቆጣጥር በቅተናል” ብሎ እስከመደንፋት ተደርሷል። በጥዋቱ እንዲህ ከደነፉ፣ ረፋዱ ላይ ምን እንደሚሰሩ መገመት አያስቸግርም።
በሀገርህ ሰርተህ፣ ተከብረህ እንድትኖር እና የኢትዮጵያ ትውልድ እንዲቀጥል የምትፈልግ ወገን ሁሉ አንገቱን ብቅ ያረገውን ብሄራዊ አደጋ ለማክሸፍ ቆርጠህ ተነስ። ዝምታህ ለአገር አፍራሾች ድጋፍ ነው። አገር የሚፈርሰው በህዝብ ሳይሆን ጥላቻ ባሰከራቸው ጥቂት ጽንፈኞች መሆኑን ላፍታም መዘንጋት የለበትም።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ተከብራ ትኑር!
Filed in: Amharic