>
4:23 pm - Sunday December 5, 2021

መንግስታዊ የዘር ማጥፋት አዋጅ !! (ሀብታሙ አያሌው)

መንግስታዊ የዘር ማጥፋት አዋጅ !!
ሀብታሙ አያሌው
የኔ ፕሬዝዳንት ልክ ናቸዉ! እሽሩሩዉ ይበቃናል!  – ታዬ ደንደ
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሊቀመንበርነት የሚመራው የኦዴፓ ፓርቲ ክፍተኛ  አመራር አቶ ታዬ ደንደአ በፅሑፋቸው ምንም በማያሻማ መንገድ የብሔረሰብ ስም ለይተው  በመግለፅ በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ተፈፅሟል ለሚሉት አጀንዳቸው ሒሳብ ማወራረጃ ዛሬ የዘር-ማፅዳት የሚያስክትል ፅሑፍ በይፋ ለቅቀዋል።
(በነገራችን ላይ በአፄ ምኒልክ ዘመን ተፈፅመ የሚሉት የውሸት ትርክት የኢትዮጵያ ህዝብ ጠቅላላ ብዛት  5 ሚሊዮን አካባቢ በነበረበት ዘመን ያለምንም ማስረጃ
 “5 ሚሊዮን የኦሮሞ ህዝብ ተገድሏል”  የሚል የውሸት ትርክት ዋነኛ የፖለቲካ መሳሪያቸው እንደሆነ ይታወቃል። )
ከቀናት በፊት የዚሁ የኦዴፓ ከፍተኛ አመራርና የክልሉ ሊቀመንበር  አቶ ሽመልስ አብዲሳ “ነፍጠኛውን በሰበረን ቦታ ሰብረን ከተማውን ተቆጣጥረናል…”  ማለቱ ይታወቃል።  ይህ ቦታና ጊዜ ተመርጦ ታቅዶ በዓላማ የተነገረን የጥላቻ አዋጅ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና “ተናጋሪው ንግግሩን በፅሑፍ ቢያዘጋጁው አይሳሳትም ነበር” በማለት የጥላቻው አመለካከት ሊያመጣ የሚችለው አደጋ ሳይሆን ነገሩ በጊዜ መነቃቱ የፈጠረበትን ቁጭት መናገሩንም እናስታውሳለን።
ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና “በጽሑፍ ቢሆን አይሳሳትም ነበር” በማለት ነገሩ ድንገት በመድረክ ሞቅታ የተነገረ ለማስመሰል ህዝብ በመዋጮ በገነባው ሚዲያ በይፋ የኦዴፓ ዘብ ሆኖ የቆመበት ብዙዎችን ያስቆጣ ተግባር ሳይውል ሳያድር በሌላኛው የኦዴፓ አመራር በግልፅ በፅሑፍ ቀርቧል።  ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ሆይ አሁንስ ኦዴፓ የማይሳሳተው ምን ቢያደርግ ነው ?
ሽመልስ አብዲሳ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከማንም በላይ የቀረበ የቤተመንግስቱ ልዩ ባለሟል እንደነበረ ከዚያም በልዩ ሁኔታ ክልሉን እንዲመራ እምነት ጥሎ ለመሪነት እንደሾመው ስናስታውስ ደግሞ የመከራው ዶፍ ከየት እንደሚቀዳ ያስታውሰናል።
ከዚህ በላይ ሳይርቁ ከዚህ በላይ ሳይገዝፉ የክህደት ቁልቁለታቸው፤ የትዕቢታቸው ልቅ በግልፅ መውጣቱ እንደ ትልቅ  እድል ሊታይ ይገባዋል።  የኦነግ አማራ ጠል ፖለቲካ ኢትዮጵያን ለመናድ  በቤተመንግስቱ እንደ እንጉዳይ ፍልቶ ንፁሃንን ሊቀጥፍ እየተሰናዳ ይገኛል።
አሁን ሁሉም ነገር ግልፅ ሆኗል።  መፍትሔውም አንድና አንድ ነው። መደራጀት መደራጀት መደራጀት…ለአፍታ አለመዘናጋት ማንኛውንም ተራ ልዩነት ጥሎ እንደ ችቦ በጋራ መቆም !!
የኔ ፕሬዝዳንት ልክ ናቸዉ! እሽሩሩዉ ይበቃናል!
ታዬ ደንደአ
በኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ ዋዜማ ፕሬዝደንት ሽመልስ ለህዝቦች ባህል እና ማንነት መጥፋት የነፍጠኛን ስርዓት መኮነኑ “ነፍጠኛ እኛ ነን” ባዮችን አስቆጥቷል። የክፍለ ዘመኑ አሳፋሪ ክስተት ነዉ። በኢትዮጵያ ነፍጠኝነት እና አማራነት አንድ ስለመሆናቸዉ የሚተርክ አመለካከት የለም። ካለም ትክክል አይደለም። ነፍጠኝነት የአገዛዝ ስርዓት ነዉ። ያ ስርዓት ደግሞ በአማራ ህዝብ ስም ነገደ እንጂ ለደሀዉ አማራ ጉዳት እንጂ ጥቅም አላመጣም። የአማራ ህዝብ ዛሬም ከወንድሞቹ እኩል ወይም ይበልጥ በድህነት እና በድንቁርና እየማቀቀ ነዉ።የዝህ ህዝብ ችግር ከህዝባችን ችግር እኩል ይሰማናል።
የነፍጠኛ ስርዓት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ዉድመትን አስከትሏል። የህዝቦችን ቁሳዊ እና መንፈሳዊ መብቶችን በጭካኔ አጥፍቷል። ወላይታን “ወላሞ” ፣ትግሬን “አጋሜ”፣ ጉሙዝ፣አኟክን እና ሌሎች ጥቁሮችን “ባሪያ” ወይም “ሻንቅላ”፣ ጋሞን “ዶርዜ”፣ ጌድዮን “ደራሳ”፣ ኦሮሞን “ጋላ”፣አፋርን “አዳል”፣ ሶማሌን “ሽርጣም” እና ወዘተ በማለት ለሁሉም ብሔሮች የስድብ ስም በመስጠት ባህላዊ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅሟል። በዝህ ህደት ደግሞ እንደ ኦሮሞ የተጎዳ የለም። ነፍጠኝነት የፈፀብን በደል ወደር የለዉም። አብዘኛዉ ወሎ ማንነቱን ያጣዉ በነፍጠኛ ስርዓት ነዉ። ወረ-የጁ፣ ወረ-ኢሉ፣ ወረ-ቃሉ፣ ወረ-ኢመኑ፣ ወረ-ባቦ እና ሌሎች የተፈጥሮ ማንነታቸዉን ያጡት በባህላዊ ዘር ማጥፋት ነዉ። በሸገር የጉለሌ፣ የኤካ፣ የገላን እና የአብቹ ጎሳዎች በነፍጠኛዉ ስርዓት ጠፍቷል። በጨለንቆ፣ በጉለሌ እና በባሌ የጅምላ ጭፍጨፋ ተፈፅሟል። በአኖሌ የአባቶች እጅ እና የእናቶች ጡት በጭካኔ ተቆርጧል። ልጆች ወንድነታቸዉን ተሰልበዉ ጃንደረባ ተደርጓል። በሸገር ጊዮርጊስ እና በሌሎች አከባቢዎች የጅምላ ስቅላት ሲፈፀም ኖሯል። ወንዶች እና ሴቶች በህይወት ተቀብሯል። ይህ ከባድ ጥፋት ነዉ!
አሁን አሁን “ነፍጠኛ ነን” የሚሉ ወገኖች እየታዩ ነዉ። እነ አሰማሔኝ አስረስ “ነፍጠኛ” መሆናቸዉን ብቻ ሳይሆን በዝህ ማንነታቸዉ እንደሚኮሩ አስረግጧል። መልካም አጋጣሚ ነዉ። የነፍጠኛዉ ስርዓት ላደረሰዉ ዉድመት ተጠያቂ ባለመገኘቱ እና የወደፊቱ እንደሚበጅ በመታመኑ በርካታ ጉዳዮች በዝምታ ታልፏል። አሁን የጉዳዩ ባለቤቶች ተገኝቷል። በህግ ህሳቡን እናወራርዳለን። ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሀል።
ከለዉጡ በኋላ በርካታ ትንኮሳዎችን አይተናል። እነ አሰማሔኝ በፌዴራል መስሪያ ቤቶች ከ60-80% ድርሻ ይዞ 20% ድርሻ እንኳን ያልያዘዉን ኦሮሞ “ባለጊዜ” በማለት በ”ሁሉም ኬኛ” ተሳልቋል። የሰዉነት ዉሀ-ልክ መሆናቸዉን ደስኩረዉ ሌሎች ብሔሮችን በመናቅ የነፍጠኝነት አጀንዳን በግላጭ አራምዷል። ሸገርን እና አከባቢዋን በጎጃም ሰዎች ካስወረሩ በኋላ ህገ-ወጥ ግንባታ እንዳይፈርስ በአቋም ተከራክሯል። ነገሮችን ለማለዘብ ሲባል ህገ-ወጥነትን እና አስነዋሪ ስድብን ታግሰናል። አሁን የሚበቃን ይመስለኛል። እዉነትን በመናገር የመሸበት ማደር በዉሸት ትርክት ላይ የተመሠረቱትን ችግሮች ይፈታል። አማራዉ “ቆማጣን ቆማጣ ካላሉት ገብቶ ይፈተፍታል” የሚለዉ ይሄኔ ይሆናል። ቢለይልን ይሻላል። ለእብሪተኞች ትዕግስት ሞኝነት ይመስላል!  እሽሩሩዉ ይበቃል!
Filed in: Amharic