>
11:04 pm - Sunday May 22, 2022

ሽመልስ አብዲሣ… ኢጆሌ “እንኳዕ ካባኹም ተፈጢርና!” (ይነጋል በላቸው)

ሽመልስ አብዲሣ… ኢጆሌ “እንኳዕ ካባኹም ተፈጢርና!”

ይነጋል በላቸው 

እንኳን ለትዕይንተ ብዙው የመስከረም ወር – 2012ዓ.ም – አደረሳችሁ፡፡ መለስ ዜናዊ እንዳልሞተ ተዓምራዊ በሚመስል የነገሮች አካሄድና ምስስሎሽ እየተረዳን ነው፡፡ ብዙ ግልገል መለሶች ሀገር ምድሩን ሞልተውታል፡፡ መለሳዊ መምህራንም ከየዕድሜ ክልሉ በብዛት አሉ፡፡ ዶ/ር ገመቹ መገርሣ የተባለው ገልቱ አንዱና አንጋፋው ነው፡፡ እነሕዝቅኤል፣ ፀጋየ አራርሣ፣ ጃዋርና ሌሎች ጎልማሣና ታዳጊ የጥፋት ዘመቻው አባላትም አሉ፡፡ ስለዚህ መለሲስም እንደፍልስፍናም እንደርዕዮትም እንደቡድናዊ ሃይማኖትና እንደግል እምነትም ገና ብዙ አሣር ሊያሳየን ዝግጅቱን አጠናቋል ማለት ነው፡፡ ሰሞነኛ የመሀል አዲስ አበባ ድፍረት የተሞላባቸው እንቅስቃሴዎች በሙሉ ኃይላቸው በግልጽ የሚያሳዩን ይህንኑ ነው፡፡

በመሠረቱ የሰሞኑ ኦነጋዊ ወጥ ረገጥ ተግባራት የጀመሩት ቀደም ብሎ ሲሆን መስመር የያዙለት ግን በእሥራኤላዊ ሰርጂካል ኦፐሬሽን የጠላት አመታት ሥልት ባህር ዳር ላይ የአማራውን ክልል አንኳር አመራር ካስወገዱ በኋላ እንደነበር በተለይ አሁን በግልጽ መገንዘብ አያቅትም፡፡ የለውጡ ሞተሮች በኅቡዕና በግልጽ ከመሀል አዲስ አበባ እስከ ባህር ዳርና መቀሌ ምናልባትም ከዚያም ባለፈ የሤራ ቁርኝት በአጭር ጊዜ ውስጥ ያከናወኑትና “በድል የተወጡት” ያ ጭካኔ የተሞላበት ኦፐሬሽን ውጤቱ ምን እንደሆነ አሁን በይፋ እያየነው እንገኛለን፡፡ ለዚህም ነው ይህ ሽመልስ የሚባል ሮጦ ያልጠገበ ልበ ድፍን ጢነኛ(ቄሮ) የላኪዎቹን ቀልብ የሳበ መስሎት የመለስን የመቀሌ ላይ ንግግር አሻሽሎ በመኮረጅ ሰሞኑን እዚችው ጉደኛ ከተማችን ውስጥ ሌሎቻችን የማንሰማና የማናውቅ መስሎት በኦሮምኛ የተናገረው፡፡ የበቀደሙን ብቻም አይደለም የተናገረ፡፡ ከዚያም በፊት ኦሮሞ ወጣቶችን ሰብስቦ ከአንድ የወሮበሎች ቡድን እንጂ ከክልል ፕሬዝደንት በማይጠበቅ አስነዋሪ ሁኔታ “አይዟችሁ! እኛም ከጎናችሁ ነን፡፡ የተዘጋ ኮንዶምኒየም ስታገኙ ሰብራችሁ ግቡ፡፡ሁሉም የኛው ነውና እንዳትፈሩ!…” የሚል መልእክት በማስተላለፍ በመስበርና በመሰባበር ቋንቋ ፍቅር የተለከፈ መሆኑን በተደጋጋሚ እያስመሰከረ ነው፡፡ ለጤና ያድርግለት፡፡

ይህ ልጅ ጥሩ ልጅ ነው ሲባል እሰማ ነበር – “ይመስለኝ ነበር” ለማለቴ እኔም እንደዶ/ር ዳኛቸው ይቅርታ መጠየቅ ሳይኖርብኝ አይቀርምና ይሄው አሁኑኑ ጠየቅሁ፡፡ ተራማጅ አስተሳሰብ “ስላለው”ም በዶ/ር አቢይ ለትልቅ ሹመት እንደታጨና እንደተመረጠም ሰምቻለሁ፡፡ ግን እንደትንትናው የእሬቻ ዋዜማ ንግግሩ ከሆነ እሱን ራሱን ብቻ ሣይሆን የአቢይን ምርጫም ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱን ተረድቻለሁ፡፡ ፈረንጆች “Birds of the same feather flock together.” የሚሉት እኛም “ግም ለግም አብረህ አዝግም” ወይም “ቂጥኛም ከውርዴ…” የምንለው ወደን እንዳልሆነ ይህ በዶ/ር አቢይና እርሱ በሚጎትታቸው ተሹዋሚዎች መካከል በግልጽ የምንመለከተው አሳሳቢ ትስስር ጠቋሚ ነው፡፡

የሽመልስ አባት መጠሪያ አብዲሣ ባይሆን ተመኘሁ፡፡ ምክንያቱም አብዲሣ አጋ ጎሣን ከጎሣ ወይም ነገድን ከነገድ የሚያባላ ሣይሆን ለአንዲት እናት ኢትዮጵያ ክብር ሲል ሕይወቱን የሰዋ ብሔራዊ ጀግና ነበር፡፡ የሽመልስን ንግግር የሰማ ሰው ኢትዮጵያ በምን ዓይነት እጆች ውስጥ እንደወደቀች በመገንዘብ ሀዘኑ ገደብ አይኖረውም፡፡ እውነትም “ሀገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል” መባሉ በጣም ትክክል ነው፡፡

በአንድ የነገሮች ሂደት ላይ መጀመሪያ የሚመጡ ነገሮች መጨረሻም ላይ እንዴትና ለምን እንደሚመጡ ሁሌም ይገርመኛል፡፡ በአንድ እውነተኛ ምሣሌ ማስረዳት እችላለሁ፡፡

ወያኔዎች እንደገቡ ሰሞን አማራን ከሁሉም ጎሣዎች ጋር ለማጣመድና በያለበት ለማስጨረስ አማራ አስመስለው በአማራ ስም ብአዴን ብለው ካመጧቸው እንደታምራት ላይኔና በረከት ስምዖን የመሰሉ ጉዶች በተጓዳኝ በኦህዲድ ስም የወያኔን ዓላማ የሚያስፈጽሙ በርካታ የኦሮሞ ካድሬዎች ነበሩ፡፡ ከነዚህም አንዱ አምቦ አካባቢ ኦሮሞዎችን ይሰበስብና “… ነፍጠኛ አማሮች ምን ይሉን ነበር? … ይሉን አልነበረም? …. እያሉ ይተርቱባችሁ አልነበረም?… አሁን ታዲያ ምን ትጠብቃላችሁ?…” እያለ የአሁኑ “የእግዜር ሰው” (ለጥፋቱ ይቅርታ ስለመጠየቁ እርግጠኛ ባለመሆኔ ነውና ይቅርታ) ታምራት ላይኔ ሐረር ላይ አማሮችን ለማስፈጀት እንደደሰኮረው ዓይነት ዲስኩር ያ ነበልባል የኦነግ ካድሬም ወገቡን እየሰበቀ ሲናገር አንድ ሽማግሌ ተነስተው “ኧረ እየተስተዋለ! ምን ዓይነት ንግግር ነው የምትናገረው? ጠብን እየዘራችሁ ተዋደንና ተፋቅረን የምንኖረውን ወንድማማቾች ልታጨራርሱን ነው እንዴ…?” ብለው ሲናገሩ ተሰብሳቢው ሁሉ እርሳቸውን ደግፎ በማጨብጨብ ስብሰባውን በትኖ ወደየመጣበት ሄደ፡፡ ሤራቸው የከሸፈባቸው ካዴሬዎች ያን ሽማግሌ ከዚያ ቦታ ይዘዋቸው ሄዱና ደብዛቸውን አጠፏቸው፡፡

ሽመልስ ግን በፕሬዝደንት ደረጃ መስቀል አደባባይ ላይ ያን ንግግር በማድረጉ ይሸለም እንደሆነ እንጂ ዝምቡን እሽ የሚለው የለም፡፡ የግብጽን ባንዲራ ቀለማት ቦታ በመለዋወጥ ተኮርጆ የተሠራውን የኦሮሞ አባገዳ ባንዲራ ከእናት ሀገሩ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ባንዲራ አስበልጦ ለባዕዳን ዓላማና ፍላጎት ሲል ለገንዘብ ጥቅም የተንበረከከው ጃዋርም ልዩ ሽልማት እንደሚያዘጋጅለት ግልጽ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ የመጨረሻው መጀመሪያ ነው፡፡ ኢትዮጵያን እየመሩ የኢትዮጵያ የሆነን መጥላትና መጠየፍ ዕንቆቅልሽ ነው፡፡ ከዚህና ከሌሎች ትንቢታዊ ጥቁምቶች በመነሣት መረዳት የሚቻለን ነገሮች ሁሉ እያቀጣጩ ያሉት ወደ ሀገራችን ነፃነት መሆኑን ነው፡፡ ሊነጋ ሲል ጨለማ ብቻ ሣይሆን መርገምታዊ የልጆች ልምሻም እንደሚከሰት በዐይናችን በብረቱ እየተመለከትን ነው፡፡ “የቡና ስባቱ መፋጀቱ ነው” ይባላል፡፡ የመጥፎ መጥፎ የሚባለው ነገር ወዳጅ መስሎ አብሮህ ካንተ ጋር እንደእስስት እየተለዋወጠ ሲኖር ነው፡፡ ቁርጡን የምታውቅለት ጠላትህ ግን ብዙም አይጎዳህም፡፡ ስለሆነም የሽመልስ ጉዳይ ከእንግዲህ ችግራችን አይሆንም፡፡ እንዲያውም በእርሱ መስተዋትነት ብዙ ነገሮች ግልጽ ይሆናሉ፡፡
እዚህ ላይ መለስም ሆነ እርሱን መሰል የጠፋ ትውልድ ምሣሌ የመጣበትን ነገድ ሊወክል እንደማይችልና እንደማይገባም ሁሉ ሽመልስም መላውን የኦሮሞ ሕዝብ እንደማይወክል መታወቅ አለበት፡፡ ዝርዝር ውስጥ መግባት አያስፈልገንም፡፡ ከያንዳንዱ ማኅበረሰብ ውስጥ በጥባጩን ክፍል በመቶኛ ሥሌት እናውጣ ብንል ግፋ ቢል ከአንድ እስከ አሥር መቶኛ ቢሆን ነው፡፡ ልፉ ሳይሰጥ አንድ – ሲከፋ አሥር፡፡ ዝርዝሩን ለሌላ ቀን እናኑረው፡፡ ችግራችን እነዚህ በጣት የሚቆጠሩ አፈንጋጮች የመሪነቱን ዕድል እያገኙ ጤናማውን የማኅበረሰብ ክፍል በነሱ ቁጥጥር ማድረጋቸውና በመርዛማ ፕሮፓጋንዳቸው የዋሃንን እየበከሉ ለጥፋት ማነሳሳታቸው ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ብልሹ ድርጊት ደግሞ በኛ ሀገር ብቻ ሣይሆን የትም ሀገር ያለ ነው፡፡

ስለዚህ በሕወሓት ምክንያት መላውን የትግራይ ሕዝብ መውቀስ ወይም መጥላት፣ በኦህዲድና ኦነግ ምክንያት መላውን የኦሮሞ ሕዝብ መውቀስና መጥላት፣ ትናንት በተፈጠረው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)ም ሆነ በድንጉጡ የሕወሓትና አምሣያው ኦህዲድ አሽከር የሆነው አንጋፋው ብአዴን ምክንያት መላውን አማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ መውቀስና መጥላት ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡ ለማንኛውም አዲስ አበባ ላይ የሰበረም ሆነ የተሰበረ አንድም የኅብረተሰብ ክፍል እንዳልነበረና እንደሌለ ወደፊትም ሊኖር እንደማይችል ታሪክ ሊያስተምረን ወንበር ዘርግቷልና እነማሙሽ ሽመልስ ዕድሜና ጤና ከሰጣቸው በቅርቡ ያዩታል፡፡ ፊታውራሪ ዲነግዴ፣ ቀ.ኃ.ሥ፣ መንግሥቱ ኃ/ማ፣ ጄ. ጃጋማ ኬሎ… ይሰባብራሉ እንጂ አይሰበሩም፡፡ የፈለጉትን ያጡ ባንዳዎችና የባንዳ ልጆች ተሰብረው ከሆነ ገና ነገም ይሰበራሉ – ይህን ያዝ፡፡

እርግጥ ነው – ጥቂት አሰለጦች ብዙኃንን የማወናበድ አቅምና ችሎታ እንዳላቸውና ከፍተኛ ውድመት ማድረስ እንደሚችሉ አለመረዳት የዋህነት ነው፡፡ ብዝኃነት ከጥበብና አስተዋይነት ይልቅ ወደ ጉልበትና ዐመፃ ይቀርባል፡፡ መንጋ ወይም በፈረንጅኛው “ሞብ” የምንለው ነገር የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡ በመንጋዊ አካሄድ ብስለት የለም፤ቆም ብሎ ማሰብ የለም፡፡ ጠቃሚን ከጎጂ የመለየት አስተውሎት የለም፤የአሁኒቷም ሆነች የዱሮዋ ዓለም በአብዛኛው የምትመራው ደግሞ በዚህ የመንጋ ደም ፍላት ነው፡፡

ከክርስቶስ ሞት ወዲህ እንኳን ጀምረን እስከትናንቱ የሻሸመኔው የዝቅዝቅ ስቅላትና የአማራው ክልል የሐኪሞች የድንጋይ ውግራት እንዲሁም በዚሁ ክልል የበቀደምለታው የሰዎች ህገ ወጥ ግድያና ሬሣቸው ለጅብ መሰጠት ድረስ ያለውን የመንጋ ፍርድ ብንመለከት ሰዎች ከሌሎች ወንድምና እህቶቻችን እንስሳት በእጅጉና በሚያሳፍር ሁኔታ የምናንስ መሆናችንን በቀላሉ እንገነዘባለን፡፡ እርግጠኛ ነኝ ዝንጀሮዎች ከዚህ ዓይነቱ የመንጋ ብያኔ የጠዱ ናቸው፡፡ እነሱ ከኛ ይበልጥ “ያስባሉ”፤ ከተፈጥሯዊ ጠባያቸው ላለመውጣትም ከኛ በላይ ይጥራሉ፡፡ እኛ ግን ለአንዲት እንጀራና ለአንዲት የሥልጣን ወንበር ስንል የማንሆነው የለም፡፡ ለሥጋዊ ፍላጎቶቻችን ስኬት ለኃጢኣትም ሆነ ለወንጀል በጣም ቅርብ ነን፡፡…

ለማንኛውም ቀኑ ቀርቧል፤ ቀኑን የምትጠብቁ ተስፋ ሳትቆርጡ ጠብቁ፡፡ ከዚህ በላይ ተስፋ የሚያስቆርጡና ባስቀመጣችኋቸው የማይገኙ ብዙዎች ዜጎች ሊያስደምሙን ወደ አደባባይ ገና በብዛት ይወጣሉና ተስፋችሁ ሰው ሳይሆን ቸሩ ፈጣሪያችን ይሁን፡፡ በቀላሉ ቅስማችን እንዳይሰበር ፈጣሪ አምላክ ይራዳን፡፡ እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ፡፡ በሙስሊሙና ክርስቲያኑ መካከል የምናየውን በመንፈስ የሚያስቀና ፍቅር አምላካችን እውነተኛና ዘላቂ ያድርገው፡፡ አይዞን – እንደጨለመ አይቀርም ይነጋል፡፡

ዛሬ ሌሊት ካነበብኳቸው መጣጥፎች የሚከተለውን ልጋብዛችሁ፤ በጣም ድንቅ ናትና ያላነበባችኋት አንብቧት፡፡
ርዕስ – “ኦሮማራ ጥምረት ኦሮማይ ሆኗል! ቀጣዩ አሰላለፍስ…!?!` (አንተነህ ሙሉጌታ)

 

ይነጋል በላቸው yinegal3@gmail.com

Filed in: Amharic