>

ለጓድ ታዬ ደንድዓ ፦ የይዋጣልን ፋከራውን ተቀብለናል!  አዎ ይለይልን! (አሰማህኝ አስረስ)

ለጓድ ታዬ ደንድዓ ፦ የይዋጣልን ፋከራውን ተቀብለናል!  አዎ ይለይልን!
አሰማህኝ አስረስ
ጓድ ታዬ ደንደዓ እሳቸውና ምናልባትም በርካታ ጓዶቻቸው የሚያስቡትን: በተግባርም እያደረጉ ያሉትን ሀቅ እንዲህ እስከማስረጃው ሲሰጡን ባናመሰግንዎት የኢትዮጵያ አምላክ ይቀየመናል።
እንግዲህ እርስዎ ስሜን እንደ ቀላል አንጠልጥለው ቢጠሩኝም አንድ ግምባር ውስጥ የምንታገል ጓዶች ስለሆንን በሌላ በኩል ደግሞ ታላቁን የኦሮሞ ሕዝብ የሚመራው ኦዴፓ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ስለሆኑ በማክበር እስከ ሙሉ ክብርዎ ጠርቸዎታለሁ።
እንግዲህ በጽሑፍዎ ያረጋገጡት ነገር ቢኖር ልክ የዛሬ አመት ዶክተር አብይ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ሲመረጡ ድምጽ ከሰጡት ሰዎች መካከል አንዱ ስለነበርኩ በዚህ ጉባኤ ወቅት ከተነበቡት የመግለጫ ሃሳቦች መካከል አንዱ አላግባብ በውሸት የተደረቱ ትርክቶችን እናስተካክላለን የሚለውን በግልጽ እና በማያሻማ መልኩ ጥሰውታል።
ይህን አቋምዎን እንኳን የአማራ ሕዝብ የራስዎ ፓርቲ ኦዴፓ (የእኔ ፓርቲ እህት ድርጅት) አይቀበለዎትም። እርስዎ ያራመዱት ፍጹም የተሳሳተ ትርክት በታላቁና አስተዋዩ የኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ምንም ተቀባይነት የለውም።
አሁን በነፍጠኝነት የምትከሱት አማራ አቅፎና ደግፎ ከራሱ እናንተን አስቀድሞ ለዚህ የስልጣን እርካብ እንዳደረሳችሁ ዘንግታችሁ የምትሄዱበት መንገድ ከሕዝብ ተነጥላችሁ እርቃናችሁን ትቀሩ እንደሁ እንጂ ታላቁ የኦሮሞ ሕዝብ አይከተላችሁም:: ምክንያቱም የኦሮሞ ሕዝብ በእኩልነት መኖር እንጂ ሌላውን ለመደፍጠጥ ፍላጎት የሌለው ስለሆነ።
በጣም የሚያሳዝነው ዘመኑ “የመደመር ነው” እያላችሁ በየአደባባዩ ትቀንሱናላችሁ: “ዘመኑ የይቅርታና የፍቅር ነው” እያላችሁ “ሰብረናቸዋል: ቀብረናቸዋል” የሚል የአደባባይ ዝማሬ ታውጃላችሁ። እኛ እየተናገርን ያለነው አካሄዳችሁ እጅግ አደገኛ እንደሆነ እና መላው ሕዝብ ይህንን የተሳሳተ ትርክት አምርሮ እንዲታገለው ነው።
የአማራን ሕዝብና ነፍጠኛን ለያይተን ነው የምናየው ላሉት ትህነግም በ27 አመት ቆይታው አማራና ነፍጠኛ አንድ ናቸው ብሎ አያውቅም። በተግባር ግን ነፍጠኝነትና ትምክህተኝነት ለአማራ የተሰጡ ቅጽል ስሞች እንደነበሩ ማወቅ ብቻም ሳይሆን በኮርስ ደረጃ እርስዎ ተጠምቀውበታል። እርስዎ ነፍጠኛ የሚል ቃል ከአፈዎ ሲያዋጡ አማራ ማለትዎ እንደሆነ እንኳን እኛ ትናንት የተወለደ ህጻን ይረዳዋል። 60 አመት ሙሉ ለጥላቻ መቀስቀሻ የዋለን ቃል እንደቀድሞው ስርዓት “አማራን አይደለም” የሚለው ተራ ማጭበርበር ነው። የአማራ ሕዝብ በዚህ ትርክት ምክንያት በየቦታው በተለይ በኦሮምያ እንደጎመን ታጭዷል: እንደ በሬ ታርዷል:: በኋላ የመጣው ባለእርስቱን መጤ ነህ ብሎ አፈናቅሎታል። ይህ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው:: ምን አልባትም እስከዛሬ ድረስ በማንአለብኝነት የቀጠለ አጸያፊ ተግባር ነው።
ስለአማራ ሕዝብ ድህነትና “ድንቁርና” የገለጹበት አግባብ የቃል አጠቃቀሙ ተገቢነት የለውም ብቻም ሳይሆን የአማራ ሕዝብ ደንቆሮ እንዳልሆነ እና ኢትዮጵያ አሉኝ የምትላቸውን ሃብቶች በሙሉ በአዕምሮው ያከናወነ በተፈጥሮው ባለብሩህ አዕምሮ እንደሆነ “አውቀው ካልተኙ” በስተቀር ከእርስዎ በላይ ማረጋገጫ የሚሰጥ ያለ አይመስለኝም።
የሆኑ በድሮ ጊዜ ለአንዳንድ ብሔረሰቦች ተገቢና መደበኛ ስም ሆነው ያገለግሉ የነበሩ  ከጊዜ በኋላ በዚህ ስም መጠራት አልፈልግም ላሉት ሁሉ በሚፈልጉት ስም መጠራት እንደሚችሉ: ከዚህ ቀደም ይጠሩባቸው የነበሩ ሰምችም እንዲቀየሩ ተደርጎ ያደረውን ዛሬ የሌላውን ትኩረት ለመሳብ “ነፍጠኞች ያወጧቸው ስሞች” ብለው መደርደርዎ የእርስዎን አላዋቂነት እንጂ የጉዳዩን ትክክለኝነት አያሳይም።  እነዚህ የጠቀሷቸው ስሞች አንዳቸውም በአማርኛ ቋንቋ ትርጉም አልተሰጣቸውም። እንዲያውም አንዳንዶቹ ስሞች የአፋን ኦሮሞ ትርጉም ያላቸው ሆነው እናገኛቸዋለን። ለምሳሌ “ወላሞ” የኦሮምኛ ቃል ነው። አንዳንዶቹ አሁንም ድረስ ጥቅም ላይ የሚውል መጠሪያዎች ናቸው። በዚህ ጉዳይ ላይ በዝርዝር ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ።
የህግ ምሩቅ እንደመሆንዎ የሚያሸንፉበትን ኬዝ ቢመርጡ ጥሩ ነበር። በዚች አገር ታሪክ ውስጥ ማን አጥፊ እንደነበር ማን ከየት እንደመጣ: የትኛው አካባቢ የማን እንደሆነ የኦሮሞ ምሁራን  የጻፏቸውን ሰነዶች ብቻ እንደማስረጃ በማቅረብ ተከራክሮ ማሸነፍ ይቻላል።
አሁንም የነፍጠኛ ልጅነቴን አስረግጬ እነግርዎታለሁ። ነፍጠኛ አገር አቀና እንጂ አገር አላጠፋም። ነፍጠኛ የአባቶቹን እርስት ለእርስዎ አካፈለ እንጂ የማንንም ግዛት አልወረረም ። የማነንም ባህል አላወደመም። ነፍጠኛን መጡበት እንጂ አልመጣብዎትም። እንግዲህ ለዚህ ሁሉ ማስረጃው የኦሮሞ ምሁራን የጻፏቸው ሰነዶች ናቸው።
እነ አጼ አምደጽዮን (1314-1344) እና አጼ ዘርዓያዕቆብ (1434-1468) እስከ ቀይ ባህር መጨረሻ ድረስ ኢትዮጵያን አስፋፍተው የገዙ መሆኑ ይታወቃል። ከዚያም ኢማም አህመድ ኢብን ኢብራሂም አልጋዚ (አህመድ ኢብራሂም)  በተለምዶ ግራኝ አህመድ (1527-43) ወታደርቹን እያስከተለ  በቱርኮች እየታገዘ እስከ አክሱም፣ ሀዲያ: ወላይታ ገስግሶ ከፍተኛ ደም አፋሳሽ ጦርነቶች ተደርገዋል። ይህ ዘመን ቤተ ክርስቲያኖች: ንዋየ ቅድሳት በግፍ የወደሙበት ጊዜ ነበር።
በዚያ ዘመን በክርስቲያን መንግስት ላይ የደረሰውን ውድመትና የአቅም መዳከም እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኦሮሞ ጦረኞች በተለይም ከ1522- 1618 ከመዳ ወላቡ፣ ሀሮ ወላቡ፣ ቱሉ ቁርቁር፣ ሀሮ ወለል በመነሳት እስከ አሸንጌ ሀይቅ ትግራይ ድረስ መስፋፋታቸው ብዙ ማንነቶችን እየደመሰሱ መምጣታቸው በታሪክ ውስጥ ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል።
እነ አጼ ሚኒሊክ ያደረጉት የቅድመ አያቶቻቸውን እርስት በማስመለስ ኢትዮጵያ የበለጠ አንድነቷ እንዲጠበቅ ነው። ያውም በአብዛኛው ያለ ደም አፋሳሽ ጦርነት ነው የአሁኒቷን ኢትዮጵያ የገነቡት። ይህ ነፍጠኝነት የሚያስከስስ ከሆነ እና እኛ የነፍጠኛ ልጆች በህግ የምንጠየቅ ከሆነ የእርስዎ ቅድመ አያቶች በ16ኛው ክፍለ ዘመን ያደረሱትን መጠነሰፊ ጥፋት ሒሳቡን የሚያወራርደው ማን ነው? በእርስዎ ስሌት እርስዎ ነዎት ማለት ነው።
እውነት ከእኛ ጋር ናት። ታሪክም ከእኛ ጋር ነው። እኛን የሚያስጠይቀን ምንአልባት እስካሁን የአባቶቻችንን እርስት አለማስመለሳችን ይሆናል። እርስዎ እንዳሉት በፍትህና ርትዕ እንዳኝ ከተባለ ሁላችንም ማስረጃዎቻቸውንን ይዘት ፍርድ ቤት እንቅረብ። የሚሉት የፍትህ ስርዓት በነጻነትና በገለልተኛነት የሁላችንን ሰነዶች መርምሮ ፍርድ ይስጥ። የዛኔ አላግባብ የአባቶቹን እርስት የተቀማው የነፍጠኛ ዘር ፍትህ ያገኛል። ሁሉም ወደነበረበት ይመለሳል።
የይዋጣልን ፋከራውን ተቀብለናል! 
አዎ ይለይልን!
Filed in: Amharic