>

ሰዎቻችን ተናግረው ከሚያስቡ አስበው ቢናገሩ ምናለ?!? (መስከረም አበራ)

ሰዎቻችን ተናግረው ከሚያስቡ አስበው ቢናገሩ ምናለ?!?
መስከረም አበራ
ኦህዴድ ያወጣውን መግለጫ “አይከፋም” በሚል መዝግቤዋለሁ፡፡እጅግ በጣም ጥሩ የሚሆነው ግን ባለስልጣናት አስበው ቢናገሩ እንጅ ተናግረው ባያስቡ ነው፡፡ መግለጫው ተናግሮ የማሰብ ነገር ይታይበታል፡፡ተናግሮ ማሰብ የተበላሸ ግንኙነትን ሙሉ በሙሉ ላይጠግን ይችላል፡፡አስቦ መናገርን የመሰለ ነገር የለም!
ሃገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታ ስሜት እንዳቀበለ የሚጎፈሉበት አይደለም፡፡ሰከን ተብሎም ከሆነልን ጥሩ ነው!ለማንኛውም በለስልጣናትም ሆኑ ምሁራን አስበው መናገር ቢችሉ ጥሩ ነው፡፡ ሚዲያዎችም “ከፍሎ አይቆርስ”(አማርኛ ግር ለሚላችሁ ተጠንቅቀው የማይናገሩ ለማለት ነው) የሆኑ ምሁራንን ለጊዜው ባይጋብዙ የተሻለ መስሎ ይታየኛል፡፡
 ባስልጣን አለመሆናቸው በጃቸው እንጅ ባለፈው በLTV ቀርበው ያወሩት ዶ/ር ገመቹ መገርሳም ብዙ ስተዋል፡፡ በበኩሌ የሰውየው     ንግግግር ውስጥ ያዝናናኝ ነገርም ነበረ፡፡
ዶ/ር ገመቹን የሚያስከነዱ አክራሪ የኦሮሞ ናሽናሊስት ምሁራንን እድል ገጥሞኝ ማዋራት የቻልኩባቸው አጋጣሚዎች ስለነበሩ የሰውየው ንግግር እምብዛም አልገረመኝም፡፡ በሌላ በኩል የኦሮሞ ናሽናስት ምሁራን ጠጋ ብለው ሲያናግሯቸው ደግሞ በግሌ የምወደውን ትህትና፣ሰው አክባሪነት፣የሰው ሃሳብ ለመስማትም ሆነ የራሳቸውን ለማጋራት ዝግጁነት እና ቅንነትም ስላስተዋልኩባቸው አሁን አሁን እንደ ወትሮው በንግግራቸው ግራ አልጋባም፡፡
በበኩሌ ዋናው ነገር በሰውነት መልካም ግንኙነት መፍጠር መቻል ይመስለኛል፡፡እኔ ባየሁት መጠን ደግሞ አንድ ቤት የሚቀመጡ የማይመስሉ ፖለቲከኞች እንደ ሰው የመገናኘት እድል ሲፈጠርላቸው ሰዋዊ የወዳጅ ግንኙነት ሲመሰርቱ ስላየሁሩ ሁሉ በሩቁ በቲቪ እንደምናየው እንዳልሆነ ገብቶኛል፡፡ ሁሉም እንደምው የተራራቀ ሃሳብ ያለው ሁሉ በግንባር ተቀራርቦ እንዲነጋገርማድረግ ቢቻል ነገሮች እንደሚቀየሩ ከግምት ያለፈ እምነት አለኝ፡፡
 ሆኖም ፖለቲከኞችም ሆኑ ምሁራን ብድግ ብለው የሚያወርዱት ያልተገራ ንግግራቸው የሚያበላሸው ነገር የለም ማለቴ አይደለም፡፡ ለራሳቸውም ቢሆን ምሁርነትን ከስሜታዊነት ጋር እኩል ማስኬድ ምሁራዊ ክብራቸውን የሚመጥን አይደለም፡፡ከዶክተር ገመቹ ንግግር ውስጥ በጣም ያስደነገጠኝ “ኢትዮጵያ ትልቅ ችግር አለባት፡፡ የኢትዮጵያ ችግር ኦሮሞ ነው፤የኦሮሞ ችግር ኢትዮጵያ ነች” ያሉት ነገር ነው:: እንዴትም አድርጌ ባስበው ትርጉሙን ላገኘው አልቻልኩም፡፡”መደመር መስቀል ነው” ያሉትን ነገርም ቀለል አድርገነው እንለፍ ካልን እንጅ እሱም በጣም አደገኛ ንግግር ነው፡፡”የኦሮሞ ተማሪዎች ልዩ ተግዳሮት ስላላቸው በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የኦሮሞ ተማሪዎች ዲን ይቋቋምላቸው” ያሉት ነገርም በጤና ነው ማሰኘቱ አይቀርም፡፡ “ጥምቀት ኦሮሞነትን አጥቦ የሚወስድና በአማራነት የሚቀይር ነገር  ነገር ነው” ብለው ሲያርፉት ነገሩ እንዴት ነው አስብለውኛል፡፡ ኦሮሞ ሲጠመቅ አማራ ከሆነ አማራ ሲጠመቅስ አንግሎ-ሳክሰን መሆኑ ነው? ማለቴ አልቀረም፡፡
ቤቲሻ ‘ምን ቢቆርጥዎት ነው ኢትዮጵያዊ ሴት ሞልቶ የውጭ ዜጋ ያገቡት’ ብላ ለጠየቀችው ጥያቄ “ምን አገባሽ?” ብለው ያጥረገርጓታል ብየ ፈርቼላት ነበር፡፡ ብዙም ሳያካብዱ የመለሱበት ነገር ሰውየው ገራገርነትም እንደማያጣቸው ጠቆም አድርጎኛል፡፡ ለቤቲ ግን ይህ ግላዊ ነገር ለባለቤቱ ብቻ የሚተው መሆኑን ማን በነገራት?! ስለ መደመር ስትጠይቃቸው “አንች ተደምረሽ ከሆነ ልምድሽን አካፍይኝ እንዲረዳኝ” ያሏት ነገር ፈገግ አድርጋኛለች፡፡ ቆየት ብለው ደግሞ “መደመር አለመሬን በምን አውቃለሁ?” ብለው ቁጭ አሉ፤”በክርስቶስ ማመን አለማመኔንስ ቢሆን ማን ያስረዳኛል?” ሲሉ ደገሙና ሳቄን አበረቱት፡፡
“ስለመደመር ለማንበብ ጉጉት አለኝ” ያሉት አንብበው አቋም ለመያዝ ከቅንነት ያሉት ነገር ይመስላል፡፡ ጎጃም ሄደው ስላዩት የህዝብ ድህነት የተናገሩት ነገርም ሰውየው ስሜታዊ ብቻ እንዳልሆኑ፣ሰው ለመረዳትም ቅንነት እንደማይጡ ያመለክታል፡፡የዋቄ ፈና እምነት ተከታይ መሆናቸውን አበክረው ከተናገሩ በኋላ ስለ እምነቱ አንኳር አእማዶች እንዲናገሩ ሲጠየቁ የተደነባበሩት ነገር የሃይማኖቱ ተከታይ ነኝ ያሉት ክርስቲያን ተብሎ አማራ ላለመሆን(በራሳቸው “Conception” መሰረት አማራ እኩል ይሆናል ክርስቲያን ስለሆ)  ሽሽት የያዙ ያስመስላቸዋል፡፡
ማንኛውም  ምሁራንም ሆኑ ባለስልጣናት አስቦ መናገርን ገንዘብ ቢያደርጉ ምኞቴ ነው! ተናግሮ ማሰብ ይቁም…..
Filed in: Amharic