>
5:13 pm - Friday April 18, 5451

ኖቤል ጌጥ አይደለም!!! (በፍቃዱ ሞረዳ)

ኖቤል ጌጥ አይደለም!!!
በፍቃዱ ሞረዳ
በስዊዲናዊዉ ኬሚስት፣ኢንጂነርና ኢንዱስትሪያሊስት አልፍሬድ ኖቤል ስም የተሰየመዉና ‹‹ ኖቤል›› ተብሎ የሚታወቀዉ ሽልማት በሠላም ስም ለአፍሪካዊያን ሲሰጥ ዘንድሮ ለአሥራ አንደኛ ጊዜ ይመስለኛል፡፡ በአልበርት ሉቱሊ ተጀምሮ ፣
በ1978 የግብፅ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት ከእስራኤል የወቅቱ መሪ ቤጊን ጋር ተካፈሉት
በ1984 ቄስ ዴዚሞንድ ቱቱ
በ1993 ኒልስን ማንዴላና ፍሬዴሪክ ዴክላርክ
በ2001 ኮፊ አናን
በ2004 ኬንያዊቷዋ ዋንጋሪ ማታይ
በ2005 ግብፃዊዉ መሀመድ አልባራዲ ከዓለም የአቶሚክ ኢነርጂ ጋር የተጋራዉ
በ2011 የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኤሌን ጆንስን ከየመን ዜጋ ተዋካል ከርማ ጋር የተጋሩት
በ2015 የቱኒዚያ ሠራተኞች ሕብረት
በ2019 ኢትዮጵያዊዉ አብይ አህመድ የለዉጥ ኃይል ከሆኑት ጓዶቻቸዉና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የተጋሩት፡፡   ማንኛዉንም ሽልማት ማሸነፍ ጥሩ ነዉ፡፡ ተሽሎ የመገኘትና የስኬት ማረጋገጫ ነዉና፡፡ የሠላም ኖቤልን ማሸነፍ በራሱ ሠላምን፣እድገትን፣ዲሞክራሲን… አያመጣም፡፡
   የኒልሰን ማንዴላ ኖቤል ለደቡብ አፍሪካ ምስኪን ጥቁሮች የፈየደዉ ነገር የለም፡፡ ዛሬም ከእጅ አዙር የባዕዳን ተፅእኖ አላላቀቃቸዉም፡፡ ዛሬም የሀገራቸዉ መሬት ባለቤቶች አይደሉም፡፡ ሽልማቱ የማንዴላ ታሪክ ማስጌጫ እንጂ ለደቡብ አፍሪካ ጭቁን ሕዝብ የተጠበቀዉን ጥቅም አላስገኘም፡፡
    በ1991 የሰላም ኖቤል ሽልማትን ያገኙት የያኔዉ በርማ የአሁኗ ማይንማር ሕዝብ የመብት ተሟጋች ( አሁን የሀገሪቷ መሪ ናቸዉ) ኣን ሳን ሱ ኪ ሽልማታቸዉ አልተባረከላቸዉም፡፡ ይልቁንም እርሳቸዉ ሥልጣን ( የይስሙላ) ከያዙ በኋላ በሩሂንጋ( ጃ) ሙስሊሞች ላይ ከደረሰዉ ጭፍጨፋና መፈናቀል ጋር በተያያዘ ሽልማታቸዉ እንዲነጠቅ ወይም እዉቅናዉ እንዲነሳ የሚል ትልቅ ዘመቻ ተከፍቶባቸዋል፡፡
  44ኛዉ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በ2009 የሠላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ ነበሩ፡፡ ሽልማታቸዉ በተለይም ለምስኪን ጥቁር አሜሪካዊያን ሕይወት የፈየደዉ ነገር የለም፡፡ የጓንታናሞን ማገቻ( እስር ቤት) እንኳን ሊያዘጋቸዉ አልቻለም፡፡ ሊቢያ የተበታተነችዉና ጦሱ ለሁሉም አፍሪካዊያን ወገኖቻችን እንዲተርፍ የሆነዉ በግንባር ቀደምትነት በኖቤል አሸናፊዉ ባራክ ኦባም አመራር ነዉ፡፡
     እነሆ አብይ አህመድ በብረት ምጣድ ላይ ተቀምጠዉ እንዳሉ የኖቤል ሽልማት አሸናፊነት የምስራች ደርሷቸዋል፡፡ ደጋፊዎቻቸዉና ወዳጅ ዘመዶቻቸዉ ተደስተዋል፡፡ እኔም በቅን ልቦና ተደስቻለሁ፡፡ በቅን ልቦናም ‹‹ ምነዉ በቀረበት?›› ብያለሁ፡፡ በምቀኝነት አይደለም፡፡አሳዝኖኝ ነዉ፡፡
       ከኤርትራዊያን ወንድሞቻችን ጋር የተፈጠረዉ መቀራረብ፤ የደቡብና የሰሜን ሱዳን ጉዳይ፣ የኤርትራና የጂቡቲ፣ የኬንያና የሶማሊያ…የሠላም ጉዳዮች ሲነሱ አብይ አሕመድ የአንበሳ ድርሻ እንዳለዉ መካድ አይቻልም፡፡ በሀገር ዉስጥ እስር ቤት ቁጭ ብለዉ ዕለተ ሞታቸዉን ብቻ ይጠባበቁ የነበሩ ተስፋ የለሾች እንደገና ተስፋ እንዲዘሩ ያደረገዉ የአብይ አሕመድ ቡድን ጥረት መሆኑን ማስተባበል ራስን ማታለል ነዉ፡፡ ምንም እንኳን የትግሉ ዋና ባለቤት ሕዝቡ ራሱ ቢሆንም፡፡
 የእኔ ወደሀገሬ መመለስና እናቴን ማየት መቻል በራሱ አንድ የኖቤል ሽልማት ሊያስገኝ የሚገባ ተግባር ነዉ ሆኖ ይሰማኛል፡፡   ይህ ሁሉ ሆኖም ግን የሰዉዬዉና የጓዶቻቸዉ ብሎም የሀገሪቷ ዜጎች አሳር ገና አላበቃም፡፡ አያድርገዉ እንጂ በአዲስና አስቀያሚ አሳር ጅማሮ ላይ የምንገኝ ይመስላል፡፡ ሀገሪቱ በትልቅ የቅንነት ቸነፈር እየተመታች  ትገኛለች፡፡
  ብዙዎች ለአብይ አሕመድ የ‹‹ እንኳን ደስ አለዎት›› መልዕክት በመፀፍ ላይ በሚገኙበት በአሁኑ ሰዓት ቀላል ቁጥር የሌላቸዉ ዜጎች የተቃዉሞ መግለጫ  እየፃፉ ይሆናል፡፡ በር ዘግተዉ የሽልማት ዉግዘት መፈክር ለተቃዉሞ ሠልፍ እያዘጋጁ ይሆናል፡፡ በየዱሩም ጠመንጃ የሚወለዉሉ አያሌ ናቸዉ፡፡  በ360 ድግሪ ዙሪያ ለሟርትና እርግማን የሾሉ ምላሶች ይታያሉ፡፡
    አብይ አሕመድ እንደኒልስን ማንዴላ ሽልማቱን ልፈዉ ‹‹ በቃኝ ልረፍ›› የሚሉ ሰዉ አይመስሉኝም፡፡ ‹‹ እንዴት ትልቁን የዓለም የሠላም ሽልማት አሸንፌ በሰዉ እጨክናለሁ፡፡ እንዴት ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዘዥ ሆኜ እነዚህን ዝም እላለሁ;…›› በሚል ዉጥረት ዕድሜዉን በግማሽ እንዲሳጥር የተሰጠዉ መድኃኒት ሁሉ ይመስለኛል፡፡
ኖቤል ጌጥ አይደለም፡፡ይልቁንስ ሸክም እንጂ፡፡   አብይ አሕመድ ሸክሙን ትችልበትን ትከሻ ይስጥህ፡፡ እኛንም ሸክምህን ለመጋራት የሚያስችለንን ልቦና ይስጠን፡፡
     ዛሬን ሳይሆን ነገን አሻግሮ የሚያዩ፣ ከ‹‹ እኔ›› ይልቅ ‹‹እኛ›› የሚሉ፣ በጎ ሃሳቦችን እያጎለበቱ የጎደሉትን ደግሞ በትዕግሥትና በመነጋገር ለመሙላት የሚተጉ፣…ቅን ዜጎች ሲኖሩን እንደሕዝብ መጪዉን የኖቤል ሽልማት እናሸንፋለን፡፡
  ለአሁኑ ግን ዶክተር አብይ አሕመድ፣የትግል አጋሮች፣ ወዳጆችና ቤተሰቦች  እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ Bashaasha baga gammadde!
Filed in: Amharic