>

የሚሰማ ባይኖርም፤ ቢኖርም ስለ ዛሬ እና ስለ እሁዱ ሰልፍ ይህን ለማለት ወደድኩ!!! (ኢያስፔድ ተስፋዬ)

የሚሰማ ባይኖርም፤ ቢኖርም ስለ ዛሬ እና ስለ እሁዱ ሰልፍ ይህን ለማለት ወደድኩ!!!
ኢያስፔድ ተስፋዬ
¹- እስክንድር ነጋ ሰላማዊ ሰልፉን የጠራው በማሳወቂያ ወረቀት ላይ በግልፅ እንደሚታየው በግሉ እንጂ በባለአደራው ስም አይደለም። በሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ አዋጅ መሰረት ደግሞ ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ቡድን ሰላማዊ ሰልፍ የመጥራት መብት አለው። በመሆኑም እስክንድር እንደ ግለሰብ ህግን በሚገባ ተከትሎ ነው ሰልፍ የጠራው።
2-ሀ- ዛሬ የተወሰኑ ወጣቶች እስክንድር መግለጫ ከሚሰጥበት ቢሮ ስር “ዳውን ዳውን ነፍጠኛ” “ባላደራው ህገወጥ ነው” ወዘተ የሚሉ መፈክሮች በማሰማት መጠነኛ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል። ይህ መጠነኛ ሰልፍ ያለምንም የእውቅና ደብዳቤ ፍቃድ ካገኘ እስክንድር የጠራው ሰልፍ ለምን እውቅና አያገኝም?
ለ- ዛሬ ተቃውሞ ያሰሙት ወጣቶች እና በእስክንድር በኩል የነበሩ ወጣቶች ግጭት ውስጥ ሊገቡ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ እየታየ የአዲስ አበባ እና የፌደራል ፖሊስ ጥግ ጥጉን ይዞ በመቆም እንደ ድራማ የሚከታተለው ነገር በፍፁም ተገቢ አይደለም።
ሐ- ወጣቶቹን አደራጅቶ እየላከ ያለው አካል የመንግስትን እና የመስተዳድሩን ስም ብቻ ሳይሆን እያሰደበ ያለው – ከመታሰር እና ከመገደል ውጭ ምንም ትርፍ ያላገኘውን የኦሮሞ ህዝብም በሌሎች ጥርስ ውስጥ እያስገባ እና ተረኛ የሚል ታርጋ እያስለጠፈበት መሆኑን ማወቅ አለበት። በተለይም ከጀርባ “አለሁላችሁ” የሚለው የፀጥታ ኃይልም ሆነ በተለያየ መንገድ ለወጣቶቹ ድጋፍ እያደረጋችሁ ያላችሁ ሰዎች ሌላውን መጉዳት ብቻ ሳይሆን የራሳችሁን ጥቅምም በዘላቂነት የሚያስከብርላችሁን መንገድ እየተከተላችሁ አይደለም እና ታረሙ።
መ- ከአማራ ክልል የሚመጡ መኪናዎችን መንገድ ላይ አስቁሞ ለሰልፉ ነው የሚመጡት እያሉ ማስቆም፤ አስወርዶ ማጉላላት ከዛም እንዲመለሱ ማድረግ እጅግ አሰቃቂ ፋሺዝም ነው ። ከተጓዦቹ ውስጥ ለህክምና ለትምህርት ለስራ ለተለያየ ጉዳይ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ ይኖራል። ለሰልፉም ቢመጡ መብታቸው ነው።  ይህ ድርጊት የኦሮሞን ህዝብ ከሌላው ወገኑ በሰላም እንዳይኖር የተሸረበ ትልቅ ደባ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ። ሊታሰብበት ይገባል።
3- እስክንድር ነጋ በዛሬው መግለጫው ላይ እንደተናገረው የማሳወቂያ ደብዳቤ ካስገባ በኋላ እስካሁን በመንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ ባለመኖሩ “መንግስት በዝምታ ውስጥ ፈቅዶልናል ማለት ነው” ብሏል። ይህ ከህግ አንፃር ልክ ነው። ህጉ ራሱ መንግስት በ12 ሰአት ውስጥ መልስ ካልሰጠ እንደተፈቀደ ይቆጠራል ነው የሚለው።
መንግስት እስካሁን ለምን ዝምታን እንደመረጠ ግልፅ አይደለም። ሰዎች ሰልፉ ተፈቅዷል ብለው አስበው እሁድ ወደ አደባባይ መውጣት ከጀመሩ በኃላ በጉልበት ሊያስቀር ነው ወይስ ምን አስቦ ነው ዝም ያለው? ለምን ነገሮች ሳይባባሱ መልስ አይሰጥም?
.
4- እንግዲህ ጨዋታው ፖለቲካ ነው- ፖለቲካ ቁማር ነው-
እስክንድርን መንግስት ሰልፉን እንዳያደርግ ቢከለክለው አትራፊው ማነው? እስክንድር።
የእስክንድርን መግለጫ ለመረበሽ የሄዱ ወጣቶችን መንግስት በዝምታ በማየቱ አትራፊው ማነው? እስክንድር።
ከማንኛውም ግርግር፣ ክልከላ እና አፈና የሚያተርፈው እስክንድር ነው። እስክንድር እና ባልደራሱ እስካሁንም የፖለቲካ ህይወታቸው የቀጠለው በመንግስት የተሳሳቱ uncalculated ግብታዊ የክልከላ እርምጃዎች ነው።
በዛሬው ጨዋታም ቁማሩን የበላው እስክንድር ነው።
.
መንግስት የእሁዱን ሰልፍ ፈቅዶ እና ጥበቃም አድርጎ ሰልፉ ቢካሄድ የሚያተርፈው መንግስት ነው።
ሰልፉ ላይ ብዙ ሰው ቢወጣና በሰላም ቢያልቅ ከለውጡ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ የተደረገ የመጀመሪያው ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ይሆናል። ይህ በራሱ ለመንግስት እንደ አንድ ስኬት ይቆጠርለታል። በሰልፉ የተነሱ ጥያቄዎችን እና የሚሰሙ ድምፆችን ይዞ ራሱን ይገመግምበታል። ይህም ስኬት ነው።
.
ሰልፉ ብዙ ሰው ያልተገኘበት እና ቀዝቃዛ ከሆነም እስክንድር ለራሱ የቆመበትን የሚያይበት እና የአዲስ አበባ ህዝብ ማን እና ምን ጋር እንደቆመ መንግስት የሚያይበት ይሆን ነበር።
.
በመጨረሻም ሰልፉ እንደተከለከለ ቀረም ሆነ ተፈቀደ- ማንም ወጣት የሚጋጭበት እና ደም የሚፈስበት- የከተማዋ ሰላም የሚታወክበት መሆን የለበትም።
.
በተረፈ መንግስት እየሄደበት ያለው አካሄድ ለኦሮሞ ህዝብ ያለ ስራው- ባልዋለበት ውሎ- መጥፎ ስም የሚያሰጠው መሆኑን የኦሮሞ አክቲቪስቶች ሊገነዘቡ ይገባል።
የሚሰማ ከተገኘ የኔ አስተያየት ይሄ ነው።ይኸው ነው!
Filed in: Amharic