>
1:30 am - Saturday December 10, 2022

የዶ/ር አብይ  መሸለም! የፕ/ት ትራምፕ የይገባኛል ቅሬታ...!!!! (ታምሩ ገዳ)

የዶ/ር አብይ  መሸለም! የፕ/ት ትራምፕ የይገባኛል ቅሬታ…!!!!
ታምሩ ገዳ
የዘንድሮው  የሰላም ኖቤል ሽልማት ለኢትዮጵያው ጠ/ሚ/ር ለዶክተር አብይ አህመድ አሊ መስጠቱን የሽልማት ሰጪው ድርጅት  ከኖሮዊይ  ይፋ አድርጓል፣ደስታውንም ገልጿል።
ሸላሚ ድርጅቱ በሰጠው አስተያየት “ዶ/ር አብይ  አህመድ በአፍሪካ ቀንድ በተለይ ደግሞ በኢትዮ-ኤርትራ መካከል እርቀ ሰላም እንዲሰፍን  ፣የትብብር መንፈስ እንዲጎለብት ላበረከቱት አድተዋጽኦ የክብር ሽልማቱ  ተሰጥቷቸዋል” ብሏል።
ጠ/ሚ/ር  አብይ  አህመድ በበኩላቸው “ሽልማቱ ለኢትዮጵያኖች እና ለአፍሪካዊያን  ኩራት  እና ታላቅ ክብር ነው፣ ብዙዎችም በአውንታነቱ እንደ ሚቀበሉት ተስፋ አደርጋለሁ።ስለሽልማቱም ከልብ አመሰግናለሁ”ሲሉ ሽልማቱን  በጸጋ ተቀብለውታል።ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ  የተበረከተላቸውን ሜዳሊያ፣የምስክር ወረቀት እና የገንዘብ ስጦታን  የፊታችን ታህሳስ(ዲሴምበር)ወር በግንባር በመገኘት ወይም በተወካያቸው አማካኝነት ኖርዌይ(በኦስሎ ከተማ) ይቀበላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ለጠ/ሚ/ር አብይ  አህመድ የእንኳን ደሳሎት መልእክት ካስተላለፉት  አለማቀፋዊ ተቋማት መካከል የአለም የአካባቢ ጥበቃ  ፕሮግራም(UN Environmental program) አንዱ ሲሆን ባለፈው ሐምሌ ወር በኢትዮጵያ ውስጥ  በአንድ ቀን 350 ሚሊዬን የዛፍ ችግኞችን በመትከል የአለም ሪኮርድ የተሰበረበት ስኬትን በምስል አስደግፎ  ደስታውን ገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ዋና ጽሐፊ  አንቶኒዬ ጉቴሬዥ፦ 
” ሽልማቱ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተጀመረውን ጤናማ ግንኙነትን  ለማጎልበት ላሳዩት መልካም ራእይ ሲሆን ፣በዚያ ታሪካዊ የፊርማ ፕሮግራም ላይ በመታደሜ  ትልቅ ክብር ይሰማኛል”ሲሉ  ጉቴሬዥ ደስታቸውን ገልጸዋል።
የአለም አቀፍ ቀውስ አጥኚው  ዊሊየም ዳቪሰን፦ 
 “ለዶ/ር አብይ የተበረከተው የኖቤል ሽልማት  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያኖች ለተያያዙት የዲሞክራሲ፣የሰላም እና ደህንነት ግንባታ ምርኩዝ ሊሆናቸው ይችላል” ሲል ግምቱን ሰንዝሯል።
ምንም እንኳን የሰላም ኖቤል ሽልማቱ በዶ/ር አብይ ስም ቢበረከትም  ከኤርትራ ጋር ለተደረገው የእርቀ ሰላም  ሂደት የፕ/ት ኢሳያስ አፈርቂን ሚናን ያልዘነጋው የኖሮዊጂያው ሸላሚ ድርጅት” ሰላም በአንድ ሰው/ቡድን  ጥረት ብቻ አይመጣም፣ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ የሰላም እጃቸውን ሲዘረጉ ፣ፕ/ት ኢሳያስም  እጃቸውን ዘርግተው በመቀበላቸው  የሰላም ሂደቱ እውን እንዲሆን እገዛ አድርገዋል”ሲል  ለአቶ ኢሳያስ ያለውን እክብሮቱን ገልጿል።
በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር የሆኑት እስጢፋኖስ አፈወርቂ በትዊተር ገጻቸው ፦
“የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ህዝቦች በደማቸው፣ በላባቸው እና በእንባቸው በእኩዮች ላይ ዳግም  የተቀዳጁት ድል ነው”በማለት ሽልማቱን አወድሰዋል።
የመብት ተሟጋቹ አሚኒስቲ ኢንተርናሽናል፦
የዶ/ር አብይ መሸለምን በደስታ የተቀበለው ሲሆን “በአገሪቱ የሚታዪትን ጎሳ ተኮር ውጥረቶችን በማርገብ እና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ብዙ ሊሰሩ ይገባዎታል” በማለት አስጠንቅቋል።
ፒፕል የተሰኘው ታዋቂ መጽሔት ፦
ሽልማቱን በማስመልከት ባወጣው ዘገባ  በብዙዎች ዘንድ የዘንድሮውን የኖቤል ሽልማትን ታሸንፋለች ተብሎ ሰፊ ቅድመ ግምት የተሰጣት የ 16 አመቷ ሲዊድናዊት የአከባቢ አየር ተቆርቋሪት  ግሪታ ቱምበርግ   ባለመሸለሟ ደጋፊዎቿ “በጣም ተገርመዋል” ብሏል።
የእንግሊዙ ታይምስ እና ዘ ሰን ጋዜጦች ዘጋቢ የሆነችው ጃኪ ሀሪሰን ፦
በተዊተር አካውንቷ ላይ  እንዳሰፈረችው”ይህቺ የአከባቢ አየር መበከል ህይወታችንን ለአደጋ መዳረጉን ፣ ለአለም መሪዎች  በግንባር ያሳወቀች፣  ለውጥ ለማምጣት እድሜ እንደ ማይገድብ በተግባር ያስመሰከረች ፣ትውልዱን በሙሉ ያንቀሳቀሰች ታዳጊ ወጣቷ፣ቱምበርግ፣የዘንድሮው የኖቤል ሽልማትን አለማግኘቷ አስገርሞኛል፣ማመንም አልቻልኩም”ስትል አስተያየትዎን ሰንዝራለች።
አንርዱሽ  ናሪያናን የተባለች አስተያየት ሰጪ ፦ “ምንም እንኳን ቱምበርግ የዘንድሮው የኖቤል ተሸላሚ ባትሆንም ፣በአለማችን ላይ የፈጠረችው ተጽእኖ ከሽልማት በላይ ነው ፣ትግሉ ተጀመረ እንጂ  ገና አልተጠናቀቀም” በማለት ተጽናንታለች።
በታዋቂው የታይምስ መጽሔት፦ “የወደፊቱ  ተጽኖ ፈጣሪዎች መካከል አንዷ” የተባለችው እንዲሁም ” የአመቱ ጨዋታ ቀያሪት”የሚል ውዳሴ ያገኘችው ቱምበርግ   የዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማቱን ካላገኘች በሳይንስ በኩል ላላት ቀና አመለካከት ሲባል “የሳይንስ ተሸላሚ ትሁን” ሲሉ የጠየቁ አልጠፉም።

ፕ/ት ትራምፕ:-“የኖቤል ሽልማት ለእኔም ሊሰጥ  ይገባል ” 
  መሪዎች ፣ፓለቲከኞች አቀንቃኞች ለበረከቱት አስተዋጽኦ  ውዳሴ እና ሽልማት እንደሚገባቸው ሁሉ አንዳንድ መሪዎች ሽልማት ከልተሰጠኝ ሞቼ እገኛለሁ ሲልም ይታያሉ።
  ለምሳሌ ያህል እስከ አሁን ድረስ ለኖቤል ሽልማት ታጭተው ይሁን አይሁን ለጊዜው  በውል ያልታወቀው  ፣ነገር ግን ባለፈው ጊዜ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ለመደራደር ፍቃደኝነት ያሳዩት ፣ የአሜሪካው  ቱጃሩ ፕሬዝዳንት ዶናል ትራምፕ ሰሞኑን  ኒዮርክ ላይ  ተካሄዶ በነበረው  አመታዊ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ከፓኪስታኑ ጠ/ሚ/ር  ኢምራን ከሃን ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ከአንድ  ከጋዜጠኛ  “የኖቤል ሽልማት  ለማግኘት ይሻሉን  ?” ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ   ፕ/ት ትራምፕ ሲመልሱ”እውነት ሸላሚዎቹ በትክክል የሚሸልሙ ከሆነ እኔ ላከናወንኳቸው በርካታ ስራዎች የኖቤል ሽልማት ሲያንሰኝ ነው”ብለዋል።
 በመቀጠልም  ስለ  የኖቤል ሽልማት  ተሻላሚው የቀድሞው የአሜሪካ ፕ/ት ባራክ ኦባማ  ያወሱት ፕ/ት ትራምፕ  ” ኦባማ ስልጣን በያዙ ማግስት  የኖቤል ሽልማት እንዴት እንዳገኙ እሳቸው  ኦባማ እንኳን የሚያውቁ አይመስለኝም” በማለት ለማጥላላት  እና የእርሳቸውንም ለኖቤል ሽልማት  ብቁነትን ለማጉላት ሞክረዋል።
Filed in: Amharic