>

ዓለማችን በኢትዮጵያ ላይ ማላገጧን ቀጥላለች! (አምባቸው ደጀኔ - ከወልዲያ)

ዓለማችን በኢትዮጵያ ላይ ማላገጧን ቀጥላለች!

አምባቸው ደጀኔ – ከወልዲያ

እኛ “ቁንጅና እንደተመልካቹ ነው” የምንለውን እነሱም “Beauty lies in the eyes of the beholder.” ይሉታል፡፡ አዎ፣ አንድን ነገር የምታይበት አቅጣጫና ልታሳካ የምትፈልገው በጎም ሆነ ክፉ ዓላማ መላ እንቅስቃሴዎችህንና ድርጊቶችህን ይወስናል፡፡ ላንዱ ሸፋፋ የሆነ ለሌላው ቀጥ ያለ ሊመስል(ሊሆን) ይችላል፡፡

ሀገር እዚህ ትተረማመሳለች፡፡ እዚያ ጋ ደግሞ የኖቤል ሽልማት ይሰጠናል፡፡ ይህ መልእክት “በርቱና ተጨራረሱ” የሚል ማበረታቻ ይመስላል፡፡ ይህ እውነት በራሱ አወዛጋቢ ነው – እንደተመልካቹ፡፡

በተመሳሳይ ቀን የተፈጠሩ ሁለት ሰበር መረጃዎችን ልግለጽ፡፡ አንደኛው የጠ/ሚ አቢይ የኖቤል ሽልማት አሸናፊነት (ልብ አድርጉ – ሊያውም በሰላም!) ሲሆን ሌላው ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ጎሐ ጽዮን አካባቢ በቄሮዎች ታግተው መዋልና በየመንገዱ ማደር ነው፤ ምክንያቱ ሲጠየቅ ደግሞ “የነገ እሁዱን የባልደራስ ሰልፍ ለመሳተፍ ‹ብዙ ወጣቶች ከአማራው ክልል ወደ ‹ፊንፊኔ› እየጎረፉ ነውና ያንን ማስቆም አለብን› ብለው ነው” የሚል ነው፡፡ ለበቀደሙ የእሬቻ በዓል ከምድረ ኦሮሞ አካባቢ ያ ሁሉ ቄሮ ሲመጣ ግን አንድም ሰው ዝምባቸውን እሽ ያለ አልነበረም – ጥጋብ ማለት አንዱ መገለጫው ይሄ ነው፡፡ ለመቻቻልና ለመከባበር ተብሎ እንጂ ሁከት መፍጠር ቢታሰብና ቢፈለግ ኖሮ አንድ ሰውም ቢሆን በቂ ነው፡፡ አምስት ሰዎች ተዓምር መፍጠር ይችላሉ፤ ደግሞ ለሁከት! ፍቅር ግን ከሁሉም ይበልጣል፡፡ ከቆሻሻ ገንዳ የተጣለን ሕጻን አንድ ውሻ በአፉ አንጠልጥሎ በፍቅር ወደ ሰዎች ቢያመጣው ያ ልጅ የሀገር መሪም መሆን ይችልና ሀገርን ከውድመት ሊታደግ ይችላል፡፡ ለዚህም ነው በፍቅር እንጂ በጠብ ሰውን በማሸነፍ አወንታዊ ዕድገትና ብልጽና ማስመዝገብ የሚያቅተን፡፡ በጥፋት የተጀመረ ማለቂያውም ያው ጥፋት ነው፡፡

እጅግ በርካታ አውቶቡሶች ከዐባይ ድልድይ እስከ ጎሐ ጽዮን ከዚያም በኋላ ባሉ ከተሞች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ በመታገዳቸው ተሣፋሪዎች ለተጨማሪ ወጪና እንግልት ተጋልጠው በየትናንሽ ከተሞች እንዲያድሩ ተገደዋል፡፡ አሁን በደረሰኝ መረጃ ደግሞ ወደ ደጀን ተመልሰው እዚያው እንዳደሩና እስከአሁኒቷ ቅጽበት (ቅዳሜ ጥቅምት 1 ቀን 2012 እኩለ ቀን ነው አሁን) በዚያቸው ከተማ እየተጉላሉ ናቸው፡፡ የከተማው ሕዝብ ግን እጅግ የሚያስደንቅ ሥራ እየሠራ ነው፡፡ ከየቤቱ እህል ውኃ በማምጣት ተሣፋሪዎችን እየመገበና እያጽናና እንደሚገኝ በስልክ ግንኙነት መረዳት ችያለሁ፡፡ ድርድሩ ካልተሳካም ወደ ባህር ዳር የመመለስ ወሬም አለ፡፡ አሁን በደረሰኝ መረጃ ደግሞ እገታው በጎጃም መስመር ብቻ ሣይሆን በደብረ ብርሃንና በሌሎች አማራ ወደ አዲስ አበባ ይገባባቸዋል ተብለው በሚጠረጠሩ ሥፍራዎችም እንደሆነ ሰማሁ፡፡ ሰውዬው “ግልጽ ጦርነት እንገባለን” ያለውን በተግባር እያሳዬ ነው – የሰላም ኖቤል ተሸላሚው፤ በጣም ጀግና ነውና! ማፈሪያ፡፡ (በአሁኑ ወቅት ኢንተርኔት በቅጡ እየሠራ አይደለም፤ ባንኮች በኔትወርክ ጥርዥ ብርዥ ማለት ምክንያት ተጨናንቀዋል፡፡ ሠልፉ ለጉድ ነው፡፡ እኔ ራሴም ይቺን ጽሑፍ ለመላክ በጣም ተቸግሬያለሁ፡፡ እየተመላለስኩ የማርማት ኔትወርክ እስኪመጣልኝ ነው፡፡)
በነገራችን ላይ ይህን ድፍረት የተሞላበት ድርጊት ለመፈጸም ትዕዛዙ ከጃዋርና መሰል አክራሪ ኦሮሞዎች ሊፈልቅ ቢችልም ካለ ዶ/ር አቢይና ቡድኑ ቡራኬ እውን ሊሆን እንደማይችል መታወቅ አለበት – በጭራሽ፡፡ ይህ ልጅ መልካም መልካም ተግባራትን ለራሱ በመሳብ ክፉ ክፉዎቹን እርሱ ራሱ ዐቅዶ ቢተገበሩም እንኳን ወደፈረደባቸውና ክፉ ተግባር ወደሚያምርባቸው አማካሪዎቹ አክራሪ ኦሮሞዎች ማላከክን ሥራየ ብሎ ተያይዞታል፡፡ እንጂ በራሱ አስተዳደር ይህን የመሰለ የጭቡ ሥራ ሲሠራ ከርሱ ባርኮት ውጪ እንደማይሆን ሁላችንም የማናምን ጅሎች ከመሰልነው ጅሉ ራሱ ነው ፡፡ … ለማንኛውም ይህ ሁሉ ቲያትር እየተከናወነ ያለው ታታሪው መሪያችን የሰላም የኖቤል ሽልማት ባገኘበት ዕለት መሆኑ ይህን ልዩ ቀን በድምቀት ለማሰብ በኦህዲድና ኦነግ ታልሞ መሆን አለበት፡፡ በዕንቆቅልሽ የተሞላች ዓለም፡፡ በዕንቆቅልሽ የተምበሸበሸች ኢትዮጵያ፡፡
በመሠረቱ ዶ/ር አቢይ በመሸለሙ የተሰማኝ ነገር የለም፡፡ የብዙዎችን ስሜት እንደምጋራ አምናለሁና ነገሩ የማይሞቀን የማይበርደን ሰዎች እንደምንኖር ግልጽ ነው፡፡ የማይሞቀን በሀገራችን ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን ኦነግ ኦህዲዊ አጠቃላይ ደባና ተንኮል ስለምንረዳ ነው፡፡ የማይበርደን ሰውዬው ባሳየው “ለቤት ቀጋ፣ ለውጭ አልጋ”ዊ የማይናቁ ተግባራት ይህን ሉሲፈር-ቀመስ ሽልማት ቢያገኝ በተለይ የሀገራችንን ስም ከማስጠራት አኳያ አወንታዊ ጎን ስላለውና “ምቀኞች” ላለመባልም ጭምር ነው፡፡ እንጂ በአክራሪ ዘረኛ ኦሮሞዎች ሀገር ከራስጌ እስከ ግርጌ እየተወረረች ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎችም ከሥራም ከመኖሪያ ቦታም ከሥልጣንም ከርስትም ከሀብትም በገፍና በግፍ እየተፈናቀሉ በሚገኙበት ሁኔታ ይህን ሽልማት መደገፍ የፍትህን ዐይን በጋሬጣ እንደመደንቆል ነው፡፡

በአንድ ሀገር ውስጥ ሁለት ሀገር ወይም መንግሥት ሊኖር አይችልም – እንደመጽሐፉ ለሁለት ጌቶች መገዛት የማይቻልም በመሆኑ፡፡ ዶ/ር አቢይም የጭንቅና የጣር ቀን በርሱ ላይ ከመምጣቱ በፊት (እስካሁን ካልመጣ(በት)) ከሁለቱ አንዱን መምረጥ ይኖርበታል፡፡ ሕዝብን ማስፈጀትና ማሰቃየት የለበትም፡፡ አንድም የ16ኛውን ክፍለ ዘመን የኦሮሞ መስፋፋት (Oromo Migration or Invasion?) በሚያስንቅ መልክ ሌት ተቀን እየተሠራ የሚገኘውን ሁሉንም ነገር ኦሮሞና የኦሮሞ የማድረግ ዘመቻ አስቁሞ ለሁላችን የሚሆን ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡ አለበለዚያ “እነዚህን ሰዎች አልቻልኳቸውም፣ ቀን ስክብ የዋልኩትን (ሲክብ ከዋለ!) ማታ ይንዱብኛል” ብሎ አንዳች ሀገራዊ መፍትሔ ማፈላለግ ይኖርበታል – በርግጥም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ከሆነ፡፡ ይቺ “ቢያዩኝ እስቅ ባያዩኝ እሰርቅ” ዓይነት የጨላጣ ዱርዬና ሌባ አካሄድ ብዙ ርቀት አታስኬድም፡፡ የዕድል ጉዳይ ሆኖ እንጂ እንዲያውም እስካሁንም ድረስ መጓዟ የሚገርም ነው፡፡ በተጨማሪም መናፈሻና ቤተ መንግሥትን ለቱሪዝም መስህብነት ማዘጋጀት መልካም መሆኑ እንዳለ ሆኖ ለድሃው ሕዝባችን ግን ለጊዜው ጠብ የሚልለት ነገር አልተገኘም፤ ሰላምም አጥተን ኅልውናችን አደጋ ላይ ወድቋልና አቢይ ይህን ጉዳይ አይዘንጋው፡፡

የዛሬ ስንት ዓመት ገደማ ያራ ፋውንዴሽን የተባለ የማዳበሪያ ነጋዴ ድርጅት ለመለስ ዜናዊ 200 ሽህ ዶላር አካባቢ ሸልሞት ነበር፡፡ በወቅቱ ያ ሽልማት የተገኘው በሎቢ(በሸልሙልን ውትወታ) እንደሆነም ሰምተናል፡፡ ያልተገባ ነገር ሰዎችን እንዴት ሊያስደስታቸው እንደሚችል ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ትንሽነት ነው፡፡ የአእምሮ መጫጫት ውጤት ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሥነ ልቦናዊ ደዌ የተመቱ ደግሞ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡

ከዚህ በሽታ ለመፈወስ ጤናማ አስተሳሰብና አመለካከት እንዲኖረን መጣር ነው፡፡ “የሰው ወርቅ አያደምቅ” ይባላል፡፡ በጎመን የሚደልሉት ሆድ አቀበትን ላለመውጣት ለሚለግም ጉልበት ያጋፍጥና ትንሽ ሮጦ ካሰቡት ግብ ሳይደርሱ ባጭር መቅረት የማያመልጡት ክፉ ዕጣ ይሆናል፡፡ የኛ በልሆነ ነገር መደሰትን እንጠየፍ – በምናምነው ይሁንብን፡፡

ስለዚህ እባካችን ወገኖቼ – የኛ ያልሆነን ነገር በማግባባትም ይሁን በገንዘብ፣ በ“ፎርጅድ”ም ይሁን በ“ፌክ” በምንም ዓይነት ህገ ወጥና የኅሊናን ሚዛን ባልጠበቀ ሁኔታ የኛ በማድረግ ከመደሰትና በመከነ አስተሳሰብም ሰዎችን ከመበደል እንቆጠብ፡፡ ሁሉም ቀሪ ነው፡፡ አሥር ፒኤች ዲ ቢኖርህ አንዱንም ይዘኸው አትቀበርም፡፡ 100 ቢሊዮን ዶላር ቢኖርህ ድምቡሎ አብራህ አትቀበርም – ከመቀበርህ ቤተሰቦችህ እስከሕይወታቸው ህልፈት እየተቧቀሱ ይራኮቱባታል እንጂ፡፡ ሰማይንና ምድርን የሚያንቀጠቅጥ ሥልጣን ቢኖርህ ስትሞት ግን የምሥጥ መጫወቻ ነህ፡፡ በቁንጅናና ውበትሽ ሽዎችን የምታማልይ ብትሖኚ ስትሞች ግን የሉሲን ዐጽም አስታውሽ – በቃ ልክ እንደርሷው ነሽ – ፈርተው ይሸሹሻል እንጂ አይጠጉሽም፡፡ ታዲያ በዚህች መከረኛ ምድር መጽናኛችን ምንድን ነው? …. ከመቃብር በላይ ለሚቆም መልካም ተግባራት ብንተጋ ግን ትውልድ አይረሳንም፡፡
በላባችንና በጥረታችን ላልመጣ የማይገባን ነገር አንማረክ፡፡ በሀሰት የትምህርት መረጃ ዶክተሮች፣ ኢንጂነሮች፣ ባለኤምኤና ቢኤ ዲግሪ ባለቤቶች የሆኑ በዓለማችን እጅግ ብዙ ዜጎች አሉ፡፡ በነዚህ ሰዎች ምሥኪኗ ዓለማችንም እነሱም ያሳዝናሉ፡፡ ከነዚህም ሰዎች አንዱ የቀድሞው የኡጋንዳ መሪ አንዱ ነው – ፊልድ ማርሻል፣ ሼክ ዶክተር የዓለም ሎሪየት ፓትርያርክ ወኢማም የዕድሜ ልክ ፕሬዝደንት ዘኡጋንዳ፡፡ እንደነዚህ ያሉ ዜጎች የአመራሩን ቦታ ሲጨብጡ ሀገርም እንዴት ልታብድ እንደምትችል አስቡት፡፡ ይህች ጽሑፍ ስሙ ካልተዘነጋኝ ለ“ኢንጂኔር ዶክተር” ሣሙኤል ትሁንልኝ፡፡

“ሌተናል ጄኔራል ዶክተር ኢንጂኔር” አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ) – ማዕረግ ግን ደስ ሲል!

Filed in: Amharic