>
12:07 am - Monday May 23, 2022

ትንሽ ስለ ኖቤል ሽልማት!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ትንሽ ስለ ኖቤል ሽልማት!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
Le Duc Tho (Phan Dinh Khai) ተብሎ የሚጠራው ቬትናማዊ የ1974  ኖቤል አሸናፊ የተናገረው፤ “peace has not yet been established.”
ዶ/ር አብይ እንግዲህ በውስጥ ሰላማችን ላይ ደግሞ ወገብዎትን ታጥቀው እና ቆፍጠን ብለው ይሥሩና የኢትዮጵያ ሕዝብም ደግሞ ደጋግሞ ይሸልምዎት። 
እኔን ጨምሮ ብዙዎች ዛሬ ያገኙትን ሽልማት በደስታ ተቀብለነዋል። የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክታችንንም አስተላልፈናል። የኖቤል ሽልማት ዋነኛ ትኩረቱ ያደረገው አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ጋር ባላት ግንኙነት፤ በተለይም በጎረቤት ከኤርትራ ጋር የነበራትን የረዥም ጊዜ ፍጥጫ በተሾሙ ማግስት እልባት በማስገኘትዎ እና በቀጠናው ላይ ሰላም እንዲሰፍን በተጫወቱት ጉልህ ሚና ነው። የዳርዳሩ ሰላም መሆን ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብም ትልቅ ጠቀሜታ ስላለው የሸላሚዎቹን ትኩረት ስቧል።
ጥቂቶች ደግሞ አገሪቱ ውስጥ አፍጠው የሚታዩትን ችግሮች በማንሳት የሕግ የበላይነት እና የፖለቲካ መረጋጋትን በአገሪቱ ውስጥ ማስፈን ላቃተው መሪ፣ መድሏዊ አስተዳደርን እያሰፈነ ያለ የፖለቲካ ፓርቲን ለሚመራ ሰው፣ የመንጋ እንቅስቃሴን ማስቆም የተሳነው፣ ለውጡን አቅጣጫ ያሳተ፣ የሚኒሊክን ታሪክ ዳግም ያነገሰ እና ሌሎች ምክንያቶችን ደርድረው ይህ ሽልማት አይገባውም የሚል ሙግት ሲሰነዝሩ አይቻለሁ።
ትንሽ ስለ ኖብል ሽልማት፤
የኖብል ሽልማት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው በ1901 እ.ኤ.አ ነው። ሽልማቱም የተሰየመው  Alfred Nobel በተሰኘ እና በ1896  እ.ኤ.አ ሕይወቱ ያለፈ ሲውዲናዊ የኬሚስትሪ ባለሙያ እና ኢንጂነር የነበረው ከበርቴ ነጋዴ ሰው ስም ነው። ሽልማቱ ሰላምን ጨምሮ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሰዎች የሚሰጥ እና ትልቅ አለም አቀፍ እውቅናን እና ተቀባይነትን ያገኘ ሽልማት ነው። ይሁን እና ይህ ሽልማት ሁሌም ለውዝግብ እና ለጭቅጭቅ የተጋለጠ ነው። በተለይም ከሰላም ጋር ተያይዞ የሚሰጠው ሽልማት እጅግ አወዛጋቢ ከመሆኑም በላይ የአለም ፖለቲካ ተጽዕኖም  ሰለባ ነው።
ይህን ሽልማት በመሸለማቸው ትልቅ ውዝግብ ካስነሱት ሰዎች መካከል የPalestine Liberation Organization (PLO) መሪ የነበሩት ያሲር አራፋት አንዱ ናቸው። አራፋት በ1994 ለዚህ ሽልማት ሲታጩ የሚመሩት ድርጅት በሽብርተኝነት የተፈረጀ ነበር። ብዙ የፖለቲካ ሽኩቻም አስነስቷል። ብልኹ አራፋት ሽልማቱ ካሸነፉ በኋላ ለሰላም አብረዋቸው ለለፉት ሺሞን ፔሬስ እና ይዛቅ ራቢን አካፍለዋል። ለፌዝም ቢሆን የሲውዲን ሕግ አውጪ ክፍል አዶልፍ ሂትለርን በ1939 በእጩነት አቅርቦት ነበር። ይሁንና አለምን ያስደመመ ነገር ቢሆንም በቀሰቀሰው ቁጣ ወዲያው ከእጩነት ተሰርሷል። በተመሳሳይ ሁኔታም በ1945 እና 1948 ጆሴፍ ስታሊን እንዲሁ በእጩነት ቀርቦ ነበር።
እውቁ የፈረንሳይ ፈላስፋ እና ደራሲ Jean-Paul Sartre በ1964 በድንቅ ሥነ ጽሑፍ ጸሃፊነት ታጭቶ ተሸልሞ ነበር። ይሁን እና ይህ ታላቅ ፈላስፋ ይህን የኖቤል ሽልማትም ሆነ ሌሎች ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸውን ሽልማቶች አልቀበልም በማለት ሽልማቱን ሳይወስድ ቀርቷል። ዋና ምክንያቱም በሽልማቱ ዙሪያ የሚነሱት የፖለቲካ እና ሌሎች አሻጥሮችን መቃወም ይፈልግ ነበር። እሱን ተከትሎም የቬትናም ፖለቲከኛ Le Duc Tho ወይም በዋና ስሙ Phan Dinh Khai ተብሎ የሚጠራው ሰው 1974 የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ነበር። ይህ ሰው ተሸላሚ የተደረገው የቬትናምን ጦርነት እንዲቆም አድርገሃል በሚል የሰላም ሽልማት ነበር። ይሁንና ግለሰቡ “peace has not yet been established.” የሚል መልዕክት አክሎ ሽልማቱን አልቀበልም ብሏል።
ሌላው አወዛጋቢ እና አስደማሚ የነበረው የኖቤል ሽልማት “extraordinary efforts to strengthen international diplomacy and cooperation between peoples” በሚል በ2009 ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኦባማ የተበረከተው ነበር። ፕሬዚዳንቱ በተሾሙ በዘጠኝ ወር ጊዜ ውስጥ የተበረከተላቸው ይህ ሽልማት ከመቼውም ግዜ በበለጠ የኖቤል ሽልማት የአለም ፖለቲካ መቆመሪያ መሆኑን ያመላከተም ነበር። The New York Times የተሰኘው ጋዜጣ “stunning surprise” ብሎታል። ኦባማ ሽልማቱ ተሰጥቷቸው ሳይውሉ እና ሳያድሩ ነበር ሊቢያን እና ሶሪያን የመሰሉ ጠንካራ እና የተረጋጉ አገሮች እንዲፈርሱ ያደረጉት። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ሰዎችም በሁለቱ አገራት ላይ በተከፈተው ጦርነት አልቋል። ሌሎች ሚሊዮኖችም ተሰደዋል። ለነገሩ በ 2015 Geir Lundestad የተሰኙት የኖቤል ሽልማት ማህበር ዳይሬክተር በጻፉት ማስታወሻ እና ለአሶሼትድ ፕሬስ በሰጡት መግለጫ ለፕሬዚዴንት ኦባማ ሽልማት መሰጠቱ እጅግ ስህተት እንደነበር እና መጸጸታቸውንም ገልጸዋል።
የኖቤል ሽልማት ብዙ ተመሳሳይ እና አወዛጋቢ ክስተቶችን እያስተናገደ መጥቶ ዛሬ እኛ ቤት ገብቷል። ዶ/ር አብይ አህመድ ከላይ እንደጠቀስኳቸው ሰዎች ያን ያህል አወዛጋቢ እና ቅሬታም ይሚነሳባቸው ሰው አይደሉም። መሸለማቸውን የሚቃወሙት ሰዎች ሁለት ፍሬ ጉዳይ ነው የሚያነሱት፤ አንደኛው ፈጠነ፤ ገና ምን ሰሩና የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ የአገሪቱን ሰላም መች በቅጡ አስጠበቁና የሚል ነው።
ለእኔ እነዚህ ሁለቱም መሟገቻዎች ብዙም ውሃ የሚቋጥሩ አይደሉም። አንደኛ የውጪው አለም የሚገደው እና ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው ከውስጣችን በኛ መካከል ስላለው ቅራኔ እና መጎነታተል ሳይሆን የአፍሪቃ ቀንድ እና የአካባቢው ሰላም ነው። መመዘኛውም በግልጽ እንደሚለው ከኤርትራ ጋር ባደረጉት የሰላም ስምምነት እና በአካባቢው ሰላም እንዲመጣ ባደረጉት ጥረት የሚል ነው። የአለም ፖለቲካ ነጸብራቅም ነው።
እኛ በጎጥ እና በሰፈር ተቧድነን ስለተናቸፍን አለምን ግድ አይለውም። ችግሩ ብሶ ለጎረቤት እስካልተረፈ ድረስ የጎሳ ፖለቲካ አንዱ የአለም ኃያላን መሸቀጫ መሆኑን መዘንጋት አይገባም። ስለዚህ ለራሳችን ስንል የውስጥ ችግራችንን ለመፍታት ብንደክም ይበጃል። አገርህ ላይ ሰላም አስፍነሃል ብሎ የሚሸልምህ የለም። እንደዛማ ቢሆን ብዙ ሰላም ውለው ሰላም የሚያድሩ አገራት መሪዎች ሁሉ በየአመቱ ተሸላሚ ይሆኑ ነበር። በአገር ውስጥ ሰላም ማስፈን እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ የመንግስት ተፈጥሯዊ ግዴታ ስለሆነ አያሸልምም። ካሸለመም ሸላሚው የአገሬው ሕዝብ ነው። አንድም በምርጫ ካርድ አለያም በመልካም ስም።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤
በሕግ የበላይነት መጥፋት፣ በመንጋ እርምጃ፣ በሰላም እጦት እና በብሔር ፖለቲካ እየታመሰች ያለችውን አገርዎትንም ይታደጓት እና የኢትዮጵያ ሕዝብ በምርጫ ካርዱ ይሸልምዎት።
አሁንም እንኳን ደስ አለዎት!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
Filed in: Amharic