>

ዐብይ አህመድ፣ የሰላም ሽልማቱ አሳፋሪ ምርጫ (መስፍን አረጋ)

ዐብይ አህመድ፣ የሰላም ሽልማቱ አሳፋሪ ምርጫ

መስፍን አረጋ

የኖቤል የሰላም ሽልማት ኮሚቴ የዚህን ዓመት የሰላም ሽልማት ለኢትዮጵያው አምባገነን ዐብይ አህመድ ለመሸለም በመወሰኑ፣ ሽልማቱን ለታላቁ ሰላማዊ ታጋይ ለማህተማ ጋንዲ ላለመሸለም በመወሰኑ ከደረሰበት ቅሌት እጅግ ለከፋ ቅሌት ራሱን በራሱ ዳርጓል፡፡ ዐብይ አህመድ በዘር ማጥፋት ወንጀል ከተከሰሰችው የ1991 ዓ.ም (እ፣ኤ፣አ) የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ ኡንግ ሳን ሱ ኪ (Aung San Suu Kyi) እጅግ የከፋ አሳፋሪ ተሸላሚ እንደሚሆን ምንም ጥረጥር የለውም፡፡

ዐብይ አህመድ በርስበርስ ጦርነት በምትታመሰው በሶርያ ውስጥ ከተከሰተው ውስጣዊ ፍልሰት (internal displacement) እጅግ የከፋው የዘመናችን ትልቁ ውስጣዊ ፍልሰት በጦቢያ ውስጥ ባፍንጫው ሥር ሲከሰት በበላይነት የተቆጣጠረ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በጦቢያ ውስጥ በቅርቡ ለመከሰት የሚያስገመግመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያቀናበሩት ወንጀለኞች መሪ በመሆን እጁን በጦቢያውያን ደም ለመታጠብ አመችውን ጊዜ በጉጉት የሚጠባበቅ አረመኔ ነው፡፡

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ‹‹መግባባት›› ከተጀመረ ሁለት ዓመት ቢያልፈውም፣ እስካሁን ድረስ የሰላም ስምምነት አለመፈረሙ ብቻ ሳይሆን፣ የመፈረሙ ዕድል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ ነው፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያና ኤርትራ አሁንም ድረስ ጦርነት ላይ ናቸው ማለት ነው፡፡ በመሆናቸውም፣ ዐብይ አህመድ የሰላም ሽልማት የተሸለመው በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም ስላወረደ ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡

ዐብይ አህመድ የሰላም ሽልማቱን የተሸለመው በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የሰላም ሂደት (peace process) እንዲጀመር ስላደረገ ነው እንዳይባል ደግሞ፣ የሂደቱ ዋና ተዋናይ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አልተሸለሙም፡፡ ስለዚህም ይህን በምንም ዓይነት መሥፈርት አግባብነት የሌለውን፣ በሰላም ከመቀለድ የሚቆጠር የሰላም ሽልማት ማንሳት የሚበጀው ለራሱ ለሰላም ሽልማት ኮሚቴው ነው፡፡ ለጦቢያውያንና ለኤርትራውያን ግን ዐብይ አህመድ ተሸለመ አልተሸለመ ለውጥ የለውም፡፡

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic