>
12:23 am - Thursday December 1, 2022

ግልፅ ደብዳቤ ለክቡር ዶ/ር ዓብይ ኣሕመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር (መርስዔ ኪዳን)

ግልፅ ደብዳቤ ለክቡር ዶ/ር ዓብይ ኣሕመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

 

 

መርስዔ ኪዳን
ከሜኔሶታ ሃገረ ኣሜሪካ

 

በቅድሚያ በታሪክ ከፍተኛ የሆነው የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ በመሆንዎ እንኳን ደስ ኣለዎ ለማለት እወዳለሁ። የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ እርስዎ በኢትዮጵያና በጎረቤቶቿ ሰላም ለማስፈን ባደረጉት ጥረት እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ በተለይ ደግሞ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከኤርትራ መንግስት ጋራ ያደረጉትን የእርቅ ተነሳሽነት ጠቅሶ ለእነዚህ ስራዎችዎ እውቅና በመስጠት የኣመቱ የሰላም የኖቤል ተሸላሚ መሆንዎን በድረገፁ ኣስታውቋል።

የኣገራችን መሪ ለዚህ ከፍተኛ ሽልማት እና እውቅና መብቃት ሁላችንን ሊያስደስተን የተገባ ሆኖ ሳለ ኣንዳንድ ኢትዮጵያውያን ወገኖችዎ ግን የደስታው ተቋዳሽ እንዳንሆን የሚያደርጉን እርስዎንም በተሰጠዎት የኣለማቀፍ እውቅና ልክ እንዳናከብርዎ የሚያደርጉን ነገሩች ኣሉ። ይህ የተሸለሙት ሽልማት እንደነ ማህተመ ጋንዲ ያሉ ታላላቅ ሰዎች የተሸለሙት ሽልማት ነው። እኛም እንደነዚህ ታላላቅ ሰዎች እንዲሆኑ ምኞታችን ነው። የነኚህ ታላላቅ ሰዎች ኣንዱ መለኪያ ለሰብኣዊነት ያላቸው ከፍተኛ እይታ እና ከጊዜያዊ ነዋያዊና የስልጣን ጥቅም ይልቅ ዘላቂ የሆነ ለሰው ልጅ የሚበጅ እሳቤ ያላቸው መሆናቸው ነው። በዚህም ምክኒያት ከቂመኝነትና ከበቀልኝነት የፀዱ ናቸው።ክቡርነትዎም በዚህ በተሰጠዎ ኣለማቀፍ እውቅና ደረጃ ራስዎን ከፍ ኣድርገው ሁላችንንም ኢትዮጵያውያንን የደስታው ተካፋይ ሊያደርጉ የሚችሉበት እድል ኣለ።

ኣብዛኞቻችን የትግራይ ብሄር ተወላጆች እርስዎ ስልጣን ላይ ከመጡ ወዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ብሄር ተወላጆች እስር ቤት በመግባታቸው ለውጡ ለኛ ሳይሆን እኛ ላይ እንደመጣ እንድንቆጥረው ተገደናል። በተለይም እንደቀድሞ የስራ ባልደረባዎ እንደነ ኮሎኔል ቢኒያም ተወልደ ያሉ ወጣት ምሁራን እንዲሁም ወታደራዊ መሪዎች እንዲሁም ነጋዴዎች በእርስዎ ትእዛዝ መታሰራቸው እጅግ ኣሳዝኖናል። በዚህም መሰረት በመላው ኣለም የምንገኝ የትግራይ ብሄር ተወላጆች ‘ወፍሪ ሓርነት’ በሚል መሪ ቃል እስረኞቻችን እንዲፈቱ ትግል ለመጀመር በመዘጋጀት ላይ እንገኛለን። ኣለም ኣቀፍ የሜዲያ ተቋማትና፣ የሰብኣዊ መብት ተቋማትን ለማስተባበርም ስራው እየተጀመረ ነው። ከነዚህ ተግባራት ኣንዱ ራሱ የኖቤል ኮሚቴው ላይ ጫና ማሳደርንም ሊያጠቃልል ይችላል።

የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ እውቅናውን ሊሰጥዎት ከተነሳባቸው ምክኒያቶች ኣንዱ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን መፍታትዎ እንደሆነ በመግለጫው ጠቅሷል። ታዲያ እርስዎም ይህን ከፍተኛ የስብእና መለኪያ የሆነ እውቅናና ሽልማት በሚመጥን መልኩ ራስዎን ከጊዜያዊ እልህና በቀለኛነት በማፅዳት ወደስልጣን ሲመጡ የገቡልንን የይቅርታና የፍቅር ቃላት ወደተግባር እንዲለውጡ እማፀንዎታለሁ። ዛሬ በፖለቲካ ለውጡ ምክኒያት እስር ቤት የሚገኙ የትግራይም ሆነ የሌላ ብሄር ተወላጅ ኢትዮጵያውያንን በምህረት ከእስር ቢለቅቁ ለዚህ ሽልማት ያበቃዎትና በመላ ኢትዮጵያውያን ላይ ተስፋ የጫሩት የይቅርታና የፍቅር ቃላትዎን ተግባራዊ ማድረግዎን ያሳያል። የተሰጠዎት የሰላም የኖቤል እውቅና ተገቢ መሆኑን ያረጋግጣል። ስለሆነም ኣንዳችን ከምንሸነፍ በእርስዎ ይቅርታ ኣድራጊነት ሁላችንም እናሸንፍ። የትግራይንም ሆነ የሌሎች ብሄሮች የፖለቲከኛ እስረኞች ይፍቱ!

በመጨረሻም መልእክቴን በደንብ በሚገልፁት በቴዎድሮስ ካሳሁን ስንኞች እቋጫለሁ።

ለለውጥ ያጎፈረው ዙፋን ላይ ሲወጣ

እንደ አምናው ባለቀን ያምናውን ከቀጣ

አዲስ ንጉሥ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ

ይቅር በለውና የበደለን ወቅሰህ

ምህረት አስተምረን
አንድ አድርገን መልሰህ

 

በድጋሜ እንኳን ደስ ያለዎ!

መርስዔ ኪዳን
mersea.kidan@gmail.com

Filed in: Amharic