>

ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት! (አቻምየለህ ታምሩ)

ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት!
አቻምየለህ ታምሩ
ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ጋቢና «ጋላ የሚባል አልነበረም»፤ «አማራ ያወጣልን ስም ነው» በሚል የመሰረተውን የፈጠራ ታሪክና የሐጢአት ክስ አንዱ የኦሕዴድ ባለሥልጣን እንዳዲስ ይዞት ተነስቷል። እንደባለሥልጣኑ ከሆነማ ጋላ የሚል ስም አወጣልን ያለውን አማራን ለመክሰስም ተጠያቂ የሆነ   «ነፍጠኛ»ም  ማግኘቱን ነግሮናል።
እስቲ  ጋላ የሚለውን ስም አማራ ሰጠን የምትሉ  የኦሮሞ ብሔርተኞች  ጋላ የሚለውን  ቃል የአማርኛ ትርጉም ንገሩን?  የቃሉን  የአማርኛ ግንድና ፍቺ እስኪ አስረዱን?
ለመሆኑ ጋላ የሚለው ቃል የኦሮምኛ ቃል እንደሆነ ስንቶቻችን ታውቃላችሁ? ጋላ ስለሚለው ቃል አመጣጥ ጥናት ያደረጉ የኦሮሞ ጥናት ባለሞያዎቹ  ፕሮፌሰር ኢኔሪኮ ቸሩሊ እ.ኤ.አ. በ1922 ዓ.ም. ባሳተመው «The Folk Literature of the Galla of Southern Abyssinia» ጥናት ውስጥ ገጽ 26 ላይ እና ፕሮፌሰር ዜትልማን ቶማስ እ.ኤ.አ. በ1994 ዓ.ም. «Nation der Oromo: Kollektive Identitäten, nationale Konflikte, Wir Gruppenbildungen» በሚል በጀርመንኛ ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ ገጽ 35 ላይ ጋላ የሚለው የኦሮምኛ ቃል መሆኑን አስቀምጠዋል።
ጣሊያናዊው ፕሮፌሰር ቸሩሊ  እንዳጠናው ጋላ የሚለው የኦሮምኛ ቃል ትርጉሙም ከእንግሊዝኛው wanderer ጋር አንድ ዓይነት መሆኑን ነግሮናል። ጀርመናዊው ፕሮፌሰር ቶማስ በበኩሉ ጋላ የሚለው ቃል የኦሮምኛ ቃል immigrant የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል አቻ መሆኑን አስረግጧል።
ጋላ የሚለውን ስም አማራ እንጂ ኦሮሞ ራሱን ለመጥራት የሚጠቀምበት ቃል   እንዳልነበረ የሚተርኩ ብዙ ቶን የኦነጋውያን  የፈጠራ ድርሰት ታትመዋል።  በቀድሞ ዘመን ተመዝግቦ የምናገኘውን ታሪክ ስንፈትሽ ግን ታላላቆቹ የኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን  ሳይቀር  ራሳቸውን  ጋላ እያሉ ይጠሩ እንደነበር ለመገንዘብ እንችላለን።
ባላፈው ካተምኋቸው የወለጋው ገዢ የደጃዝማች ሀብተ ማርያም አዋጆችና  የአባቆሮ ጋላ ዋሪ ስም  በተጨማሪ  ከታች የታተመው  አንጋሹ  ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ  ዲኔግዴ ለልጅ ኢያሱ የጻፉት ደብዳቤ እንደሚያሳየው ጋላ የሚለው ስም ለኦሮሞው ለሀብተ ጊዮርጊስ ስድብ አልነበረም። ኦነጋውያን እንደሚሉን ጋላ የሚለውን ስም አማራ ለኦሮሞ የሰጠው፤ ኦሮሞ በጭራሽ የማይጠቀምበት ስም ከነበር የዳግማዊ ምኒልክ፣ የልጅ እያሱ፣ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱና የአልጋ ወራሽ ተፈሪ  ዘመን የጦር  ሚኒስትር  የነበሩቱ  ንጉስ አንጋሹ፣  ንጉሥ ሠሪውና  አንጋሽ አፍላሹ  ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ  ዲኔግዴ በወቅቱ ሌላ  የበላይ አለቃና አዛዥ  ሳይኖርባቸው፣ እሳቸው ብቻ ብቸኛው የሀገሪቱ ቁንጮ  ባለሥልጣን፤ አራጊ ፈጣሪ በነበሩበት ወቅት ራሳቸውና ሕዝቡን ጋላ እያሉ አይጠሩም ነበር።
ስለዚህ ሳትመረምር ሀሳብ የሌለበትን የኦነግ የፈጠራ ወሬ ይዘህ  «ጋላ የሚባል አልነበረም»፤ «አማራ ያወጣልን ስም ነው» እያልህ አማራን ስትወነጅል የምትውለው  የኦሕዴዱ ሰውዬ  «ከመጠምጠም መማር ይቅደም» ፤ «ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት» የሚለውን የአያቶቻችን ጥልቅ ምክር ልንለግስህ እንደወዳለን!
Filed in: Amharic