>

ጅቡቲም ወግ ደርሷት ወረረችን - ገደለችንም!!!  (ዘመድኩን በቀለ)

ጅቡቲም ወግ ደርሷት ወረረችን ገደለችንም!!! 
ዘመድኩን በቀለ
*  “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ!!!”
★ መቼም ይህን ዜና እነ OMN እና ድምጺ ወያነ ከቅማንት ዜና፣ እነ ኢቲቪና ፋናም ከኖቤል ሽላማቱና ከቤተ መንግሥቱ ዕድሳት ጊዜ ተርፏቸው እንደማይዘግቡት ይታወቃል። እናም ሌሎቻችሁን ግን በፈጣሪ ስም እለምናችኋለሁ። ለአፋር ድምጽ እንሁነው።
•••
ጅቡቲ እንኳ ከአቅሟ ወጉ ደርሷት እንኳን ሰዉ ግመሉ ሳይቀር ለሰንደቅ ዓላማዋ ልዩ ፍቅር ያለውን ኢትዮጵያዊውን አፋሩን ወንድሜን ወረረች ገደለች የሚል ዜና ከመስማት በላይ ምን የሚያበግን ነገር አለ?
•••
በትናንትናው ዕለት ከጁቡቲ የተነሱ ናቸው የተባሉ ሠርጎ ገብ አሸባሪዎች በኢትዮጵያዊው የአፋር ክልል በአፋምቦ ወረዳ በውድቅት ሌሊት ጨለማን ተገን በማድረግ ብዙ ህፃናት፣ ሴቶች እና ሽማግሌዎች በተኙበት በአሸባሪዎች ቶክስ መደብደባቸው ተሰምቷል።
•••
በዚህም ምክንያት ብዙ ሰው እንደሞተ እና እንደቆሰለም ከአካባቢው የሚወጡት ሪፖርቶች ያሳያሉ። ዕደሜያቸው ከ7-12 ዓመት ያሉ ህፃናትም ሳይቀር የአሸባሪዎቹ ሰለባ እንደሆኑ እና ዓይነስውራን ሽማግሌዎች እና አዛውንቶችም ቤታቸው ድረስ በመግባት በጥይት ደብድበው እንደገደሏቸው ተሰምቷል።
•••
ከአሸባሪዎቹ ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ አሸባሪዎቹ ብቻቸውን እንዳልሆኑና ከጀርባቸው የውጭ ኃይል እንዳለበት ለማወቅ መቻሉን ነው የዓይን እማኞች የሚናገሩት። በርካታ የፈረንሳይ ጦር መሳሪያም ከአሸባሪዎቹ እጅ መማረኩም ተነግሯል። ከሟቾቹ አሸባሪዎች እጅ በርካታ የሠነድ ማስረጃዎችንም በቁጥጥራቸው ሥር ማስገባታቸውንም የአፋር ታጣቂዎች እየተናገሩ ነው።
•••
ጥያቄው በቀደመ ጊዜ የኢትዮጵያ የባህር በር ዘበኛ የነበረውና በሴራ ከውኃው አካባቢ እንዲርቅ የተደረገው ኢትዮጵያዊው የአፋር ህዝብ እንዲህ በጠራራ ፀሐይ እየተገደለ እያየ የኖቤል የሰላም ተሸላሚው የኢትዮጵያ መንግሥትና የኢትዮጵያ ሱሴ ኦቦ ለማ መገርሳው የፌድራል የመከላከያ ሰራዊት ለምን ዝምታን መረጡ? ፈረንሳይ ከዐቢይ ጋር የተነጋገረችው ነገር ይኖር ይሆን እንዴ?
•••
ኤርትራ በትግራይ ድንበር አካባቢ ያልተለመደ ፀባይ እያሳየች ነው ይባላል። ሱዳን የጎንደር ገበሬ ሰቅዞ ገድግዶ ይዟት ነው እንጂ አባ ጃሌው ዋርካው ስር ምሳ መብላት ያማራት ይመስላል። ደቡብ ሱዳንም ጋምቤላ አካባቢ ትልከሰከሳለች አሉ። ኬንያም ሁለት ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኟትን መንገዶች መዝጋቷ ተነግሯል። የሶማሌው አልሸባብም በኦሮሚያ ቢሮ መክፈትን በይፋ መንግሥታችን ነግሮናል። እናስ ምንድነው ነገሩ?
•••
ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚሉት ላይ ዱላ የበዛ ይመስላል? ዐማራ፣ አፋር፣ ጋምቤላ ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ …  … …
★ወገን የሚጮህላቸው  ለሌላቸው ለኢትዮጵያውያኑ አፋር ወንድሞቻችን ድምጽ እንሁናቸው። በተለይ ኢትዮጵያን የምትወዱ ለአፋር ድምጽ ሁኑት።  ዜናውን በመላው ዓለም ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እናሰማላቸው።
•••
ሻሎም !  ሰላም !
ጥቅምት 3/2012 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።
Filed in: Amharic