የከብቶች አብዮት መጨረሻው ውርደትና ሞት!
ሀይለገብርኤል አያሌው
የጆርጅ ኦርዌል (animal farm)የእንስሳት እድር በሚለው ምርጥ ምናባዊ ድርሰት የዚህችን አለም አምባገነኖች መነሻና መጨረሻ በምሳሌ እያዋዛ ያስተምራል:: በድርሰቱ ያሉ የቤት እንስሶች የሰውልጅ አገዛዝ ላይ አምጸው አሳዳሬያቸውን በማባረር እራሳቸውን በእራሳቸው የማስተዳደር ስልጣን እንደተቆናጠጡ ያትታል:: በድሉ ዋዜማ ሁሉም ደስተኛ ለመሆን ቢችልም ውሎ ሲያድር ጥቂት አሳሞች ማህበረ እንስሳቱን በውሸት ትርክት በማማለልና በተቀነባበረ ሴራ በማደናገር የእንስሳቱ የበላይና ፈላጭ ቆራጭ ለመሆን የበቁበትን ወግ እያዋዛ ያሳያል::
ፈላስፉው እንዳለው “ሰው ማህበራዊ እንስሳ ነው”:: ሕግና ስርዐት ቀርጾ መንግስታዊ አስተዳደር መስርቶ በመኖሩ ሰው ከእንስሳት የሚለይ ማህበራዊ ዋጋ ያለው ፍጥረት አድርጎታል:: የሰውን ልጅ ከእንስሳ የሚለየው ድንበር ማሰብ ማገናዘብና የአስተዳደር ስርዐት ዘርግቶ መኖር መቻሉ ነው:: በሁለት እግር መራመድና በልሳን መናገር ብቻውን ሰውን ሰው አያደርገውም::
ዛሬ ላይ እንደሰው ተፈጥረው እንደ እንስሳ የሚኖሩ ሰዎች ማየት ተለምዷል:: በገባውም ባልገባውም እንደ መንጋ ከብት የሚነዳ እንደ ወራጅ ኩሬ በቀየሱለት ቦይ የሚጏዝ ከየት እንደመጣ ወዴት እንደሚሄድ የማያውቅ ሕሊናውን ለጢቅት ነውረኞች ያስረከበ ሰው መሳይ ሰው በተለይ በሃገራችን ከቅርብ ግዜ ወዲህ እንደ አሸን ፈልቷል::
የተማረ መሃይም የምሁር ደንቆሮ የጭለማ መንገደኛ በርክቷል:: ሕሊናው በከባድ የባርነት ሰንሰለት የታስረ ውርደቱን ክብር ሃሰቱን እውነት እርኩሰቱን ቅዱስ ያደረገ መንጋ የሃገር ስጋት ሆኗል::
4 ሚሊዮን ሕዝብ በነበረበት ዘመን 5 ሚሊዮን ተገሎብኛል ብሎ በድፍረት ለመናገር የማያፍር የታሪክ ምሁር አባት አያቶቹ የደሙለትን የነጻነት ባንዲራ እረግጦ ለማዋረድ የሚጥር አልጫ ትውልድ በጥቂት ነውረኞች ሴራ የእንስሳትን ባህሪ እንዲላበስ እየተደረገ ነው::
በእንስሳት እድር መድብል ውስጥ ታታሪና ጠንካራ ሰራተኛ የነበሩት የጋማ ከብቶች የጡረታ ዘመናቸው በደስታና በምቾት እንደሚያሳልፉ በሕብረት ስምምነታቸው ላይ አጽድቀው ነበር:: ነገር ግን አብዬቱን ጠልፈው የአንድ ቡድን የበላይነትን ያነበሩት እሳሞች እንስሳቱ ባረጁ ግዜ እንኳን ጡረታ ሊወጡ ለአራጆች አሳልፈው በመሸጥ ይነግዱባቸው እንደነበር ይተርካል:: ዛሬም የወጣቱን ሕሊና በመስለብ በጥላቻ ትርክትና በአመጽ አነሳስተው እንደ እንስሳ ወደ እርድ የሚነዱ የፖለቲካ ነጋዴዎች በትውልዱ ሕልውና ላይ እያካሄዱ ያለው አሻጥር በግዜ ካልተገታ መጨረሻው ውርደትና ሞት ለመሆኑ ባለፈው አንድ አመት ያየነው ብቻ በቂ ነው::