>

ያልተነገረው የአባ ዱላዎች ጡት የመቁረጥ፣ ዐይን የማፍረጥ፣ አፍንጫ የመፎነንና እጅ የማሳጠር  ታሪክ፣ ሥርዓትና ወግ!    (አቻምየለህ ታምሩ)

ያልተነገረው የአባ ዱላዎች ጡት የመቁረጥ፣ ዐይን የማፍረጥ፣ አፍንጫ የመፎነንና እጅ የማሳጠር  ታሪክ፣ ሥርዓትና ወግ! [ክፍል ፩]  
አቻምየለህ ታምሩ
ኦነጋውያን ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን የጭካኔ ቁንጮ፣ ጥቁር እባብ፣ የዱር አውሬ እና የአፍሪካ ሂትለር አድርገው የፈጠሩትን ታሪክ እየጋቱ ያሳደጉት የቁቤ ትውልድ፣ የፈጠራ ታሪክ ያከፋውን የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን ‹ጭካኔ› እንጂ ዳግማዊ ምኒልክ በአዋጅ ያስቀሩትን ‹አባቶቼ› የሚላቸው አባዱላዎች ለዘመናት ሲፈጽሙ የኖሩትን የዘግናኝ ግፍና ጭካኔ ታሪክ ባለቤት መኾኑን ከቶ አያውቅም።
ኦሮምያ የሚባለው ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ባዘጋጀው የጉዞ መርሐ ግብር፣ በጃዋር መሐመድና በሌንጮ ለታ ፊታውራሪነት የተመራ ቡድን፣ የተስፋዬ ገብረ አብ ‹የቡርቃ ዝምታ› ልብወለድ የፈጠረውን የአርሲ አኖሌ ሐውልት ጎብኝቷል። የጉዞ መርሐ ግብሩ ታዳሚ የነበሩ የቁቤ ትውልድ ወጣቶች አንድ እጃቸውን በኮትና በሸሚዛቸው ውስጥ ጠቅልለው የተቆረጠ እጅ የሚመስል ነገር እያሳዩ ከአኖሌ ሐውልት ጀርባ የተነሱትን ፎቶ በፌስቡክ አሰራጭተዋል። እነዚህ ወጣቶች ተቆረጠ የተባለውን እጅ ታሪክ ለማስታወስ የተነሱትን ፎቶ መሳይ ታሪክ ሲፈጸም የኖረው ‹አባቶቻችን› እያሉ በሚመኩባቸው ከዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በፊት በኖሩ አባዱላዎች መኾኑን፣ ይኽንን አባገዳዎች በሠላማዊ ሰዎች ላይ ሲፈጽሙ የኖሩትን ጭካኔም በአዋጅ ያስቀሩት ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ መኾናቸውን አያውቁም። አለማወቅ ደፋር ስለሚያደርግ ‹አባቶቻችን› የሚሏቸው አባዱላዎች ሲፈጽሙ የኖሩትን ጭካኔና አረመኔነት የዳግማዊ ምኒልክ ሥራ አድርገው በራሳቸው ሲሳለቁ ሲውሉ አያፍሩም።
የሩቁን ዘመን የዐይን ምስክሩን የአባ ባሕረይ ‹ዜናሁ ለጋላ›ን፣ በተመሳሳይ ዘመን የተጻፈውን የዐፄ ሠርፀ ድንግል ዜና መዋዕል፣ ፖርቱጋላዊው የዐይን ምስክር ማኑኤል አልሜዳ እየተዘዋወረ ከጎበኘ በኋላ በጉዞ ማስታወሻው ያሰፈረውን እና የግራኝ አሕመድ ወረራ ማብቂያ አካባቢ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የፖርቱጋል አምባሳደር ጆን ቤርሙዴዝ  በዐይኑ አይቶ በመዘገበው ታሪክ ውስጥ የምናገኘው የኦሮሞ አባ ዱላዎች፣ አባ ገዳዎች እና ሉባዎች ያደረሱትን ሰብዓዊ ጥፋትና ቁሳዊ ውድመት ለጊዜው አቆይተን፣ የቅርቡን ዳግማዊ ምኒልክ በአዋጅ ያስቀሩትን የአባ ዱላዎች ግፍና ጭካኔ፣ የእጅና የጡት ቆረጣ፣ የንጹሐንን ዐይን እንደ ሙጀሌ እያወጡ እና ብልትና እግር እየቆረጡ ይዝናኑ የነበሩበትን ጭካኔ ታሪክ ብቻ ወስደን ሐውልት በመገንባት ለግፉአን መታሰቢያ እናቁም ቢባል የሐውልቱ ብዛት ከኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት ይተርፋል።
‹ተው ማነህ ተው ማነህ የተኛ ሰው አለ ትቀሰቅሳለህ› የሚል የኢትዮጵያ ብኂል አለ። እነ ተስፋዬ ገብረ አብ ለጫኗቸው ጭነት ያቆሙትን ሐውልት እየዞሩ እጃቸው እንደተቆረጠ ሊነግሩን የሚሹ ነውር ጌጡዎችን አባቶቻችን በምትሏቸው ጦረኛ አባ ዱላዎችና አባ ገዳዎች ተነግሮ የማያልቅ ግፍና መከራ የደረሰበት በጣም ከፍተኛ ሕዝብ አለና ተዉ የተኛ ሰው አትቀስቅሱ፤ ያ ቢነሳ ደግ አይደል እንላለን! የነ ተስፋዬን ፈጠራ እያመነዠኩ አኖሌ አኖሌ የሚል ጸብ አጫሪነት እየደጋገሙ ሲጭሩ የሚውሉ ጎበዞች  ‹አባ ገዳዎች ለተፈጸመው ጭካኔ ሁሉ መታሰቢያ ይቁም› የሚል  የእውነተኛ ተበዳዮች ሀገራዊ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር እየሰሩ መኾኑን ልብ ያሉት አይመስልም።
ተስፋዬ ገብረ አብ ፈልስሞ እንካችሁ ያላቸውን ሸቀጥ ሳይመረምሩ ተቀብለው የአኖሌ ትርክትን እንደ ታሪክ ለሚቆጥሩ ጎበዞች፣ አባቶቻችን ከሚሏቸው አባገዳዎች መካከል አንዱ የኾነው የጎማው አባ ገዳ፣ የሰዎችን እጅና እግር ሲቆርጥ፣ አንፍጫ ሲፎንን እና ዘግናኝ የጭካኔ ተግባሮችን ሲፈጽም መኖሩን ያውቁ ዘንድ ታሪኩን እነሆ ጋብዣቸዋለሁ። ባለታሪኩ አባ ዱላ የጎማ ገዢ የነበረ ሲኾን ስሙ አባ ዱላ አባ ረቡ ይባላል።  የአባ ረቡ ግዛት ጎማ ‹5ቱ የጊቤ አካባቢ ግዛቶች› ከሚባሉት መካከል አንዱ ነበር። የጎማው አባ ዱላ አባ ረቡ ከታች የቀረበውን ጭካኔ ሲፈጽም የኖረው ዳግማዊ ምኒልክ ሳይወለዱ በአያታቸው በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዘመን ነበር።
የአባ ረቡን ጭካኔ በጉዞ ማስታወሻቸው ከመዘገቡ የምዕራብ ሀገር ተጓዦች መካከል እግሊዛዊው ሻለቃ ኮርንዋሊስ ሐሪስ አንዱ ነው። ሻለቃ ሐሪስ እ.ኤ.አ. 1840ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ከሸዋው ንጉሥ ከሣህለ ሥላሴ ጋር የንግድና የወዳጅነት ስምምነት ለመፈራረም በእንግሊዝ መንግሥት የተላከውን ልዑክ እየመራ ነበር። ሻለቃ ሐሪስ ጎማን ጨምሮ በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል ያደረገውን ጉብኝት ጨርሶ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ እ.ኤ.አ. በ1844 ዓ.ም. በሦስት ቅጽ ባሳተመው «The Highlands of Ethiopia» መጽሐፉ ሦስተኛው ቅጽ፣ ገጽ 60 ላይ ስለ ኦሮሞው የጎማ ገዢ ስለ አባ ዱላ አባ ረቡ የጭካኔ ተግባር የሚከተለውን ጽፏል፡-
“The cruelties practiced by the chief of the Góma are almost incredible. Offenders are deprived of hands, nose, and ears; and their eyes having been seared with a hot iron, the mutilated victims are paraded through the market place for the edification of the populace. The sight of all prisoners taken in war is similarly destroyed; and a stone having been tied about the neck, they are thrown by hundreds into a river formerly styled Daama”
ሻለቃ ሐሪስ በዚህ ምስክርነቱ አባ ረቡ የሚፈጽመው ጭካኔ ለማሰብ የሚከብድ ዘግናኝ መኾኑን ነግሮናል። የሰዎችን እጅ፣ አፍንጫና ጆሮ እየቆረጠ፣ ዐይናቸውን በጋለ ብረት እያፈረጠ የሚዝናና saddist እንደኾነ ምስክርነቱን ሰጥቷል። የአባ ረቡ ጭካኔ በዚህ አያበቃም። እጃቸውን የቆረጣቸውን፣ አፍንጫቸውን የፎነናቸውን እና ጆሯቸውን የጎመዳቸውን፣ ዐይናቸውን በጋለ ብረት ያፈረጣቸውን ሰዎች ‹እኔን ያየህ ተቀጣ› የሚል መልዕክት ‹ተጽፎባቸው› በገበያ መሀል ያሳልፋቸዋል። ወረራ ፈጽሞ በምርኮ የያዛቸውን ምስኪኖች ደግሞ መቶ መቶውን እያቆራኘ አንገታቸው ላይ ድንጋይ ያስርባቸውና ዳባ ተብሎ ወደሚጠራው ጥቅል ወንዝ ከተራራ ላይ ይወረመራሉ።
በጎማ ይፈጸም የነበረው ይህ ጭካኔ የቆመው ለዐፄ ምኒልክ የገበረው የጎማው  የመጨረሻው ጨካኝ ገዢ አባ ቦካ በአዋጅ እንዲተው ከተገደደ በኋላ ነው። እንዲህ ዓይነቱ በዘመኑ የዐይን ምስክር የተመዘገበ በአባ ዱላዎች ሲፈጸም የነበረ የሰዎችን እጅ፣ አፍንጫ እና ጆሮ እየቆረጠ፣ ዐይናቸውን በጋለ ብረት እያፈረጠ ማውጣትን ለመሰለ ጭካኔ ግን አንድም ቦታ ለመታሰቢያ የሚኾን የቆመ ሐውልት የለም። ሳይመረምር እንደወረደ የሰለቀጠውን የተስፋዬ ገብረ አብን ፈጠራ እውቀት በማሳከል፣ ዳግማዊ ምኒልክን የጭካኔ መለኪያ ባሮሜትር አድርጎ ከማስረጃ ይልቅ በጩኸት የነ ተስፋዬን የአእምሮ ፈጠራ ለማሳመን ሲጥር የሚውለው የቁቤ ትውልድ፣ በተጨባጭ የነበረው ግፍ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ያስቀሩት የአባ ረቡ ዓይነት የኦሮሞ አባ ዱላዎች በጭካኔ፣ በሥርዓታቸውና ወጎቻቸው እየተመሩ በንጹሐን ላይ ሲፈጽሙ የኖሩትን የአረመኔ ተግባር እንጂ፣ የአኖሌ ትርክት ዓይነት የዐፄ ምኒልክ ታሪክ በዘመኑ በተመዘገበ የታሪክ ማስረጃ ሊቀርብ እንደማይችል በማስታወስ ‹ወሬ ሲነግሩህ ሐሳብ ጨምርበት› የሚለውን የአያቶቻችን ጥልቅ ምክር በመለገስ  ለጊዜው ልሰናበት!
Filed in: Amharic