>

በአፋር የተለያዩ መረዳዎች የሃገር መከላከያ ሚኒስቴር ያወጣውን መግለጫ በመቃወም ሰልፍ ተካሄደ!!!

በአፋር የተለያዩ መረዳዎች የሃገር መከላከያ ሚኒስቴር ያወጣውን መግለጫ በመቃወም ሰልፍ ተካሄደ!!!
የኢትዮ 360 መረጃ
 (ኢትዮ 360 – መስከረም 4/2012) በአፋር የተለያዩ መረዳዎች የሃገር መከላከያ ሚኒስቴር ያወጣውን መግለጫ በመቃወም ሰላማዊ ሰልፎች መካሄዳቸው ተገለጸ።
 በክልሉ ስድስት ወረዳዎች የተካሄደው ሰልፍ የሃገር መከላከያ በአፋር ክልል ህዝብ ላይ የደረሰውን የውጭ ጥቃት በግጦች ሳር የመጣ ግጭት ለማስመሰል የሄደበት ርቀት የአፋርን ህዝብ አስቆጥቶታል ብለዋል ነዋሪዎቹ ለኢትዮ 360።
 ጥቃቱ በውጭ ሃይል ስለመካሄዱ በቂ የሆነ መረጃ መኖሩ እየታወቀ እንዲህ አይነት መግለጫ መሰጠቱ የአፋርን ህዝብ መናቅና በተኛበት በአሰቃቂ ሁኔታ የተፈጀው የአፋር ህዝብ በፌደራል መንግስቱ ምንም አይነት ቦታ እንዳልተሰጠው የሚያሳይ ነው ብለዋል።
 የሟቾቹ ቁጥር 17 በደረሰበት የተጎዱት ሰዎች ህይወት በሞትና በህይወት ባለበት ሁኔታ ውስጥ እንዲህ አይነት መግለጫ መስጠት የሚያሳዝንና ዜጋን እንደዜጋ ያለማክበር ችግር መኖሩን በግልጽ ያሳየ ነው ሲሉ ተናግረዋል ለኢትዮ 360።
 በድንበር የሚገቡና ለሃገር አደጋ የሆኑ ህገወጥ አሰራሮችን ሲዋጋ ለኖረው የአፋር ህዝብ ይሄ አይገባውም ሲሉም ተናግረዋል።
 እንደ ሃገር መጣ የተባለው ለውጥ የት ጋ ነው ያለው ሲሉ የጠየቁት ነዋሪዎቹ በእውነትም ለውጥ ከመጣ የአፋር ህዝብ ሊደርሰው ይገባል ብለዋል።
 በተደጋጋሚ በአፋር ህዝብ ላይ የሚደርሰው ግድያና በደል እስካሁን አልቆመም፣ለዚህም የሚከራከርለት አካልን አላገኘም፣ ስለዚህ የአፋር ህዝብ መብቱን ለማስከበር የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል ነዋሪዎቹ።
 ዛሬ የተጀመረው ሰልፍ በዚሁ አያበቃም እስከ ቅዳሜ ይቀጥላል የሚሉት ነዋሪዎቹ ከዚህ ጎን ለጎንም የሚከናወኑ የተቃውሞ ርምጃዎች መኖራቸውን ተናግረል።
 መንግስት በትክክል በአፋር ህዝብ ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያና በደል እንዲሁም ድርጊቱን የፈጸመውን አካል በግልጽ ካላሳወቀ የአፋር ህዝብ መንገድን ከመዝጋት ጀምሮ የተለያዩ የተቃውሞ ርምጃዎችን ይወስዳል ብለዋል።
 የሃገር ድንበር ያስከብራል፣የህዝብ ደህንነትን ይጠብቃል የሚባለው የሃገር መከላከያ መስሪያ ቤትም እውነቱን አውጥቶ የአፋር ህዝብን ይቅርታ መጠየቅ አለበት ሲሉ አስተያየታውን ለኢትዮ 360 ሰተዋል።
Filed in: Amharic