>

የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 38ኛ መደበኛ ጉባኤ የመክፈቻ ውሎ!!! (ብርሀኑ ተካለአረጋይ)

የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 38ኛ መደበኛ ጉባኤ የመክፈቻ ውሎ!!!
ብርሀኑ ተካለአረጋይ
* ብጹእነታቸው በቤተክርስቲያን የሀብት ሽሚያ እያቆጠቆጠ በመምጣቱን  ይህ አባዜ “የራሳችንን ቤተክህነት እናቋቁማለን” ወደሚል ስርአት አልበኝነት እንደወሰደም አስታውሰዋል!!!!
ጥቅምት 5/2012 ዓ/ም ከጠዋቱ 2:30 ጀምሮ ከመላው አለም የመጡ ተሳታፊዎች ወደ መንበረ ፓትርያርክ አዳራሽ እየገቡ ነው። ከጉባኤው ተሳታፊዎች በተጨማሪም በመክፈቻው እንዲገኙ የተጋበዙ ተሳታፊዎችም በአዳራሹ ተገኝተዋል። ግቢውና አዳራሹ ከወትሮው በተለየ በቤተክርስቲያኒቷ አርማና በሀገሪቷ ሰንደቅ አላማ ተውቧል። እያንዳንዱ ተሳታፊ ወንበር ላይ “ወነአምን በአሀቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን” የሚል ቃለ ሀዋርያት የሰፈረበትና የአመቱን የሰበካ ጉባኤ ሪፖርት የያዘ መፅሄት ተቀምጧል። ቀድመው የገቡ ብፁአን አባቶችም በለሆሳስ ፀሎታቸውን ያደርሳሉ። ሚዲያዎች ካሜራቸውን ተክለው የፕሮግራሙን መጀመር ይጠባበቃሉ። ቀስ በቀስ አዳራሹ ሞላ የፕሮግራሙ መሪ ሊቀ ማዕምራን ፋንታሁን ወደ መድረኩ መጥተው ቅዱሳን ፓትርያርኮች ወደ አዳራሹ እየገቡ መሆኑን አሳወቁ።ሁለቱ ፓትርያርኮች በብፁአን አባቶች ታጅበው ወደ አዳራሹ ከገቡ በኋላ በቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ መሪነት የመክፈቻ ፀሎት ተደርጎ፣ ወንጌል ተነቦና ፀሎተ ኪዳን ተደርሶ ስብሰባው ተጀመረ።
ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት ብፁእ አቡነ ማትያስ ሲሆኑ የንግግራቸው ይዘትም የቤተክርስቲያንን ብቻ ሳይሆን የሀገርን ወቅታዊ ችግር የተረዳ ለአማሳኝና መዝባሪዎች የማስጠንቀቂያ ምልክተት የሰጠና “የሚጠሉን ጥቂቶች ናቸው ቅዱስ ፓትርያርኩ ይደግፉናል” እያሉ ለሚያወናብዱት የኦሮሚያ ቤተክህነት መስራች ነን ባዮች በግልፅ መልስ የሰጠ ወቅታዊ ንግግር ነበር።
ቅዱስነታቸው በንግግራቸው መግቢያ የነቢዩ ዳዊትን ቃል በመጥቀስ “ምንተ ገብሩ እሉ አባግዕ ዘአነ ኖላዊሆሙ ዳዕሙ ለትረድ እዴከ ላእሌየ ወላእለ ቤተ አቡየ”(እረኛቸው ጠባቂያቸው የሆንኩላቸው እነዚህ በጎች ምን አደረጉ? እጅህ በኔና በአባቴ ቤት ላይ ትውረድ) በማለት ብፁአን አባቶችና የስብሰባው ተሳታፊዎች እስከቤዛነት የሚደርስ የመሪነት ብቃት መላበስ የሚያስፈልግበት ወቅት መሆኑን አስገንዝበዋል። ሃገራችን በታላቅ ስጋትና ተስፋ መሀል ተወጥራ የምትገኝ መሆኑንና የቤተክርስቲያን ማእከላዊ መዋቅር በተለያዩ ቡድኖች እየተፈተነ መሆኑን አውስተው በዚህ ፈታኝ ወቅት የቤተ ክርስቲያን ቀዳሚ ስራ ትዕግሥትና ብልሀትን ተጠቅማ ልጆቿን ወደአንድነት መሰብሰብ መሆኑን አስታውሰዋል። በተጨማሪም ቤተክርስቲያን ከፖለቲካ ንክኪ ፍፁም ነፃ ሆና እንድትቀጥል የሁሉም አባቶች አገልጋዮችና ሰራተኞች ተግባር ነው ያሉ ሲሆን ይህን ስንል ግን ስለሰው ልጆች ደህንነትና ሰላም የእግዚአብሄርን ቃል መሰረት አድርጋ ማስተማርና መምከር እንዳለባት ግን መርሳት የለብንም ብለዋል።
ቅዱስ ፓትርያርኩ በንግግራቸው ማገባደጃ በቤተክርስቲያን የሀብት ሽሚያ እያቆጠቆጠ መምጣቱን ገልፀው ይህ አባዜም “የራሳችንን ቤተክህነት እናቋቁማለን” ወደሚል ስርአት አልበኝነት እንደወሰደም አስታውሰዋል።የጥያቄውን መነሻ ሲያብራሩም”ይህ ጥያቄ ሊመጣ የቻለው እውነት ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክህነት ጽ/ቤት ያላቋቋመችበት አካባቢ በኢትዮጵያ ኖሮ ነውን? ክርስቲያን ልጆችዋ በሚሰሙት ቋንቋ እንዳይማሩስ እውነት ከልክላ ነውን? መከልከል ቀርቶ መጽሐፉን አስተርጉማና አሳትማ ሳታሠራጭ ቀርታ ነውን? ብለው ከጠየቁ በኋላ  ይህ ሁሉ ፍጹም ሐሰት ነው፡፡ነገር ግን ከዚህ በስተጀርባ ያለው ሐቅ ሌላ ነው ፤የተለየ ቤተ ክህነት አቋቁመን ሀብት እናድልብ ነው ጥያቄው፤ ይህ አዝማሚያ የቤተ ክርስቲያንን ምጣኔ ሀብት የሚያሽመደምድ፣ አንድነትዋንም የሚፈታተን ስለሆነ ሁሉም ወገኖች ለኛ ማለትን ያቁሙና ለቤተ ክርስቲያናችን የሚለውን ቅን መርህ ይከተሉ፤” ብለዋል። በመጨረሻም ይህ ጉባኤ በቤተክርስቲያን ህልውናና በሃገር ሰላምና ልማት በህዝቦች እኩልነትና አንድነት ጉዳይ የሚመክር መሆኑን አውስተው ጠንክሮ እንዲሰራ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከቅዱስ ፓትርያርኩ በመቀጠልም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ስራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ያሬድ ዘለግ ያለ የበጀት አመቱን ሪፖርት አቅርበዋል። በንግግራቸውም ላይ ጉባዔው በቤተ ክርስቲያን አገልግጋዮችና በተከታዮቿ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ፣በዘርና በቋንቋ ሽፋን የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና አስተዳደራዊ መዋቅርን ለማፍረስ እየተደረገ ባለው የፀረ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ ላይና የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔና መግለጫዎች በመንግሥት በኩል ተገቢውን ትኩረት አለማግኘታቸውም ላይ በትኩረት አቅጣጫነት እንዲመክር ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ጉባኤው በጠዋቱ ውሎው የአክሱም፣የሲዳማና የማእከላዊ ጎንደር ሪፖርቶችን የሰማ ሲሆን በተለይም የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሪፖርት ቤተክርስቲያን የደረሰባትን ግፍ ያወሳ ተሳታፊዎችንም እምባ አውጥቶ ያስለቀሰ ሪፖርት ነበር። ጉባኤው በቀጣይ ቀናትም የሁሉንም ሀገረ ስብከት ሪፖርት የሚያዳምጥና ውይይት የሚያደርግ ሲሆን በመጨረሻም የአቋም መግለጫ አውጥቶ የሚጠናቀቅ ይሆናል።
Filed in: Amharic