>

የባንዲራ ቀን እና ያለንበት ሁኔታ!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የባንዲራ ቀን እና ያለንበት ሁኔታ!!!
ያሬድ ሀይለማርያም
የአንድ ዘመን፣ የአንድ አገር ወጣቶች፤ በተቃርኖ ውስጥ የሚኖሩ የሁለት አለም ሰዎች፤ ለምን ?
በአገር ደረጃ የባንዲራ ቀን ተብሎ በዚህ ሳምንት ሲከበር ነበር። በዚሁ ሳምንት እነዚህን ከሥር የምታዩዋቸው ፎቶዎች ብቅ ብለዋል። ፎቶዎቹ ብዙ ይናገራሉ። በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ባንዲራ ኮፍያ ዝቅ ተደርጎ ሲሰገድለት እናያለን። በሌላ በኩል ደግሞ ይሔው ባንዲራ ከተለጠፈበት መኪና ላይ ፍቆ ለማስለቀቅ በንዴት እና በጥላቻ ስሜት ወጣቱ ሲታገል እናያለን። እነዚህ በሁለቱም ምስል ላይ የሚታዩት ወጣቶች በተመሳሳይ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ እንደሆኑ መገመት ይቻላል። አንደኞቹ ከዚህ ባንዲራ ምን ትርፍ አግኝተው ወይም ምን አስገድዷቸው ነው ዝቅ ብለው እና እሱን ከፍ አርገው የሚያከብሩት? ሌሎቹስ ምን ሆነው ነው ጥላቻ እና ቁጭት በተሞላው ስሜት ባንዲራውን ለማስወገድ ብለው የሰው ንብረት እስከማበላሸት እና የባለ ንብረቱን መብት እስከ መደፍጠጥ የደረሱት።
የዛሬዋ ኢትዮጵያ እንዲህ ጉራማይሌ በሆነ ትውልድ ግራ የተጋባች ይመስለኛል። እንግዲህ ለንጽጽር ይረዳ ዘንድ አመት ከመንፈቅ በፊት በቡራዩ የተፈጸመውን አስነዋሪ ጭፍጨፋ ተከትሉ ብዙ ሰው የተጎዳባቸው የጋሙ ብሔረሰብ ወጣቶች አርባ ምንጭ ላይ እሳት ጎርሰው   ለሰልፍ በወጡ ጊዜ አንድ የኦሮሚያ ክልል ሃብት የሆነ ባንክ ሊያወድሙ ነበር። ይሁንና የአገር ሽማግሌዎቹ ቄጤማ ይዘው እና በጉልበታቸው ተንበርክከው ባህላቸው በሚፈቅደው መሰረት ወጣቶቹን ሲማጸኑ ልጆቹም ቀዝቀዝ ብለው ጥቃቱን ከማድረስ ተቆጥበው ተቃውሟቸውን ብቻ በጨዋ ደንብ ገልጸው ወደየቤታቸው ተመለሱ። አዛውንቱም ከፍተኛ ክብር በአገር ደረጃ አገኙ ተሸለሙም። ለነገሩ መሸለም የነበረባቸው አዛውንቱ ብቻ ሳይሆኑ ወጣቶቹም ነበሩ። ሽማግሌ ማክበር ብርቅ በሆነበት በዚህ ዘመን እንደ እነዛ አይነት የጋሙ ወጣቶችን ማየት ደስ ይላል።
በተቃራኒው በጎንደር አንዲት ወረዳ ለጥናት ያቀኑ የመሃል አገር ሰዎችን በድንጋይ ቀጥቅጠው የገደሉ፣ በሻሸመኔ ከተማ አንድ ወጣት በመቶዎች በሚቆጠሩ ወጣቶች ቁልቁል ዘቅዝቀው ያሰቃዩ፣ በአዋሳ ሰው በእሳት ሲያቃጥሉ የነበሩ ወጣቶችን ታዝበናል። ተዉ ብሎ ያስጣለ ሽማግሌም አልነበረም። በተለይም በሻሸመኔ ከተማ እንዲሁ ከአመት በፊት በአንድ መስጊድ ግቢ ውስጥ በርካታ ወጠምሻ መንጋ ጎረምሶች የአካባቢው ሽማግሌዎች እያሯሯጡ እና መሬት ለመሬት እያዳፉ ሲቀጠቅጧቸው የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን አይተናል። በእነዚህ አንገት በሚያስደፉ እና አሳፋሪ ተግባር በፈጸሙ ወጣቶች ያዘነውን ያህል የአርባ ምንጭ ወጣቶች ደግሞ ለሽማግሌዎች እና ለአካባቢው ባህል ያላቸውን አክብሮት እና ከፍ ያለ የሞራል ልዕልና ስናይ ተጽናናን።
በተቃርኖ ውስጥ ያለ፣ ስለ አገሩ የተዛባ ምልከታ ያለው፣ አያቶቹ ስለሞቱለት ባንዲራ በመሰሪ ፖለቲከኞች ትርክት ተጠልፎ የተዛባ ምልከታ ያለው፣ ለአገር ባህልና ወግ የማይገዛ፣ ሕግ የማይዳኘው፣ ሽማግሌ እና አዋቂ የማያከበር አስፈሪ ወጣት ከየት መጣ?
ለማንኛውም እባካችሁ ፖለቲከኞች ዛሬ እንደቀልድ የዘራችሁት ጥላቻ እና ለፖለቲካ ህልማችው ማሳለጫ እንዲሆን እሳት ውስጥ የምትሞጅሩት ወጣት ነገ የራሳችሁም መጥፊያ መሆኑን ከወዲሁ ብታስብበት መልካም ነው። መልካም ተናግራችው፣ እውነት መስክራችው በሰላም የሚትጦሩባት፣ ትውልድ ከመንጋነት ወደ ላቀ ስብዕና ከፍ የሚልባትን አገር ፍጠሩ።
የዛሬዋ ኢትዮጵያ እንዲህ በተቃርኖ የሚኖር ትውልድ አፍርታለሽ፤ የነገዋስ?
Filed in: Amharic