>
4:53 pm - Tuesday May 25, 7751

የጦር መሳሪያሰዎችን የማስፈታቱ ዘመቻ ያስከተለው  ስጋት!!! (በታምሩ ገዳ)

የጦር መሳሪያሰዎችን የማስፈታቱ ዘመቻ ያስከተለው  ስጋት!!!
በታምሩ ገዳ
ታስረው እንደተለቀቁ የሚናገሩት አቶ ሸገዲን አስተያየታቸውን ሲያራዝሙም”የመንግስት ሀይሎች ወደ መንደሮቻችን  ሲመጡ  እሮጦ ለማምለጥ የሞከረ ሰው የጥይት እሩምት ይከፈትበታል፣ ያለአንዳች ምክንያትም ይገድሉናል “ሲሉ በጸጥታ ሀይሎች ደርሶብናል ያሉት    የሰብአዊ መብት ጥሰትን አጋልጠዋል!!!
 ለ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አርብቶ አደር  ጠመንጃ  ማለት እራሱን እና ከብቶቹን ከጠላት እና ከአስፈሪ የዱር አራዊት መከላከያ ብቻ ሳይሆን የጀግንነት እና የክብር መግለጫው  ተደርጎ ይታመናል። ለአርብቶ አደሩ ጠመንጃ ማለት ሁሉም ነገሩ ነው ማለቱ ይቀላል።
ሰሞኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ፣በታችኛው የኦሞ ወንዝ አካባቢ በመከላከያ ሰራዊት እና በክልሉ ፖሊስ የተጀመረው ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻ የህይወት ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን የአካባቢው አዛውንቶች አምርረው ይናገራሉ።
የፈረንሳዩ የዜና አገልግሎት( ኤኤፍ ፒ) ጋዜጠኛ ያነጋገራቸው  የቦዲ ጎሳ አዛውንት የሆኑት ሸገዲን   እንደሚሉት ከሆነ  በዚህ በጥቅምት ወር አጋማሽ  ውስጥ ብቻ  ከአርብቶ አደሮች የጦር መሳሪያ ለማስፈታት በተጀመረው ዘመቻ  “ከአርባ በላይ አርብቶ አደሮች ያለ አንዳች ምክንያት ተገድለዋል፣በርካታዎችም ለቀናት  ታስረዋል፣ተደብደበዋል” ሲሉ ያማርራሉ።
ለደህንነታቸው  ሲሉ ሙሉ ስማቸውን ከመናገር የተቆጠቡት ፣ታስረው እንደተለቀቁ የሚናገሩት አቶ ሸገዲን አስተያየታቸውን ሲያራዝሙም”የመንግስት ሀይሎች ወደ መንደሮቻችን  ሲመጡ  እሮጦ ለማምለጥ የሞከረ ሰው የጥይት እሩምት ይከፈትበታል፣ ያለአንዳች ምክንያትም ይገድሉናል “ሲሉ በጸጥታ ሀይሎች ደርሶብናል ያሉት    የሰብአዊ መብት ጥሰትን አጋልጠዋል። ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል መባሉን  በተመለከተ አንድ ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የፖሊስ አባል ” ፍጹም ሀሰት”ሲሉ ውንጀላውን  ያስተባብላሉ።
የደቡብ ኦሞ ዞን መናገሻ ከተማ በሆነችው ጅንካ የሚገኙ ባለስልጣናት በአካባቢው ልማት እና ጽጥታ ለማስፈን ሲባል ህገወጥ  ትጥቅ ማስፈታቱ አግባብነት እንዳለው ይገልጻሉ ።
በአካባቢው  100ሺህ ሄክታር  በላይ ለም መሬት ከሚካሄደው የሸንኮራ አገዳ ተክል፣ የስኳር ፋብሪካ እና በግልገል ግቤ ሶስተኛው የሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ምክንያት “ለዘመናት የኖርንበትን መሬትን  በአዲስ ሰፋሪዎች ተነጠቅን ” የሚሉት የቦዴ ማህበረሰብ ነዋሪዎች ከመንግስት ጋር አይን እና ናጫ ከሆኑ ከራርመዋል።
የቦዴው የአገር ሽማግሌ  ሸገዲን ቅሬታ አዘል እማኝነታቸውን ሲቀጥሉም  ” አንድ ወንድሙን  በቅርቡ በሞት የተነጠቀ የአካባቢያችን ነዋሪ  ሀዘኑን በባህላዊ መንገድ  ለመግለጽ  ሲል  ጸጉሩን እና ጢሙን  ማሳዳጉን የተመለከቱ የጸጥታ ሀይሎች  ግለሰቡ ጸጉሩን እንዲላጭ  በማስገደድ የገዛ ጸጉሩን እንዲበላ አስገድደውታል።እንደዚህ መሰል ጭካኔ በእድሜያችን አላጋጠመንም”ይላሉ።በአካባቢው የታወቁ አንድ መንፈሳዊ መሪ አክሬንም እንደዚሁ ተቆፍሮ ከወጣ በሁዋላ “ለመቀጣጫ” ተብሎ አስክሬኑ በጥይት እንዲደበደብ ተደርጓል የሚለው ወቀሳንም የኤኤፍ ፒ ዘገባ ጠቃቅሶታል።
የጅንካ  ዞን መስተዳድር አማካሪ የሆኑት ሎሬ ካኩታ በበኩላቸው በቅርቡ በስኳር ፍብሪካ ሰራተኞች ላይ የተሰነዘረው ጥቃትን ተከትሎ የመከላከያ እና የአካባቢው ታጣቂዎች በርካታ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎችን በመውረስ ላይ መሆናቸውን እና ዘመቻውም  ዘጠና ከመቶ(90%) መሳካቱን ገልጸው ።እነዚህ ክላሼን ኮቭ(Ak-47s) ጨምሮ የተያዙት የጦር  መሳሪያዎች ምንጫቸውም በእርስ በርስ ጦርነት የምትናጠው ጎረቤት ደ/ሱዳን መሆኗን  ባለስልጣኑ አክለው  ተናግረዋል።  ይሁን እንጂ የመሳሪያዎቹ ብዛት ለጊዜው ይፋ አልተደረገም ።
ህገወጥ የጦር መሳሪያ የማስፈታቱ ዘመቻ ወደ አጎራባች የሙርሲ ጎሳዎች እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን “ቦዴ ላይ የተፈጸመው  እስራት ግድያ እና ግርፋት እዚህም ሊፈጠር ይችላል” የሚል  ስጋት ያለባቸው የማህበረሰቡ ተወካዮች አልጠፉም።
የመብት ተሟጋቹ ሂዩውማን ራይት ዎች  ተወካይ የሆኑት  ላቲታ ባድር በበኩላቸው ህገወጥ የጦር መሳሪያዎችን የማስፈታቱ ዘመቻ  ዜጎችን ለማሸማቀቅ ሳይሆን፣የማህበረሰቡን ምክክር እና ይሁንታን ማግኘት አለበት  ሲሉ  ያስጠነቅቃሉ።
ባሳለፍነው ሳምንት አንድ መቶ ኛውን  የአለም የሰላም ኖቤል ሽልማትን  በመቀበል አርሳቸውም ሆኑ  ደጋፊዎቻቸው የደስታ ፍንጥዝያውን ገና ያላጣጣሙት ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ    እና አስተዳደራቸው የመከላከያ እና የጸጥታ ክፍሎች ሰላማዊ ዜጎችን በማዋከብ የሚያደርሱት በደል እና ጭካኔ  የኖቤል ሽልማቱ ትርጉምን እንዳያደበዝዘው የሚሉ ወገኖች  መኖራቸውን ኤኤፍ ፒ በዘገባው ላይ አካቷል።
በደቡብ ክልል  ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን  በአራቱም ማእዘናት እንደ ጎርፍ እያጥለቀለቀ የሚገኘው የህገወጥ የጦር መሳሪያዎች   ዝውውር ለምን ተፈጠር?፣ እንዴትስ እና በማን አማካኝነት ሊቆም ይችላል  ብለው ይገምታሉ?!!!።
Filed in: Amharic