>
4:29 am - Friday July 1, 2022

ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወይም መለሲዝም ወደ ገዳ፣ ኦሮሙማ፣ መደመር ወይም ዐቢይዝም. . .  (አቻምየለህ ታምሩ)

ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወይም መለሲዝም ወደ ገዳ፣ ኦሮሙማ፣ መደመር ወይም ዐቢይዝም. . . 
 አቻምየለህ ታምሩ
መደመር በአማርኛና በኦሮምኛ 
 
ቻይና እስካሁን ድረስ በማኦይዝም እየተገዛች ትገኛለች። ማኦይዝም የቻይና  አገራዊ የፖለቲካ ፕሮግራም በመሆን  የአገር አይዲዮሎጂ ሆኖ እስካሁን ድረስ የቀጠለው በአፈናና  ከማኦ እስከ አሁን ያሉቱ  የእምነቱ ተጋሪዎች የአንድ ነገድ ሰዎች በመሆናቸው ነው። የአፈና ቀንበር ተሰብሮ የነጻነት ነፋስ በቻይና ሲነፍስ ማኦኢስም አፈር ድሜ ይበላል።
በድርጅታቸው ውስጥ ከአንድ ነገድ በላይ የሆኑ ሰዎችን ያቀፉት የነስታሊንና የነሌሊን ድርጅቶች ከነሱ በኋላ በመጡ ተረኞች ስታሊኒዝምና ሌሊንዝም አገር አፈረሰ። ባገራችንም እስካሁን ድረስ  አገር ሲያፈርስ የኖረው  አብዮታዊ ዲሞክራሲ ወይም መለሲዝም የሚባለው ማጭበርበሪያ እስካሁን ድረስ የቆየው  አንድም በአፈና ተጭኖ  ነው፤  ሁለትም ከመለስ ወገን የሆኑ ሰዎች አገራችንን ከዳር እስከ ዳር  ስለተቆጣጠሯት ነው።
ከመለስ ነገድ ውጭ የሆኑት የዛሬዎቹ ተረኞች ደግሞ ገዳና ኦሮሙማን መደመር ወይም ዐቢይዝም የሚባል የዳቦ ስም ሰጥተው  በቅጡ ያልተጤነ  ሌላ ማጭበርበሪያ ይዘው መጥተዋል። መደመር መመለክ ስለመሆኑ ሽፋኑ  ላይ ያለው ፎቶ ይናገራል። በመለስ ዜናዊ አብዮታዊ ወይም በመለሲዝም የታሰረችው ኢትዮጵያ የተዋቀረችበት ርዕዮተ ዓለም የወለደው ሕገ መንግሥት እስካልተቀየረ ድረስ መደመር በሚለው የዐቢይ ማጭበርበሪያ የመለስ ዜናዊ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የቆላንን ከማሳረር  በስተቀር አንዳች ጠብ የሚልልን ነገር ይዞ ሊመጣ አይችልም።
መደመር  is simply a transformation from one cult leader (Melesism) to another cult leader (Abiysm)! 
ኢትዮጵያ የተዋቀረችበት የሕገ መንግሥት መሰረት ሳይቀየር ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወይም መለሲዝም ወደ መደመር ወይም ዐቢይዝም የተደረገው ሽግሽግ  እንደ ለውጥ ተደርጎ ከየመጣው ጋር አሰላለፋቸውን በሚያስተካክሉ ሆዳም ምሁራንና ሽርጉድ በሚወዱ  አርቲስቶች ሲለፈፍ ቢውል ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ በሚሄደው የኢትዮጵያ ችግር ላይ ግን ከማባባስ በስተቀር  የሚያሳድረው አንዳች አዎንታዊ ተጽዕኖ የለውም።
በኢትዮጵያውያን ኑሮ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ማምጣት የሚቻለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ  የሕገ ከለላ የማግኘት፣ የንብረት ባለቤትነት፣ ደኅንነቱ ተጠብቆ የመኖር፣ በየትም ቦታ የመወከል፣ የመወከልና የመመረጥ መብቱ ሕገ መንግሥታዊ እውቅና ሲሰጠው ብቻ ነው።
ኦሕዴድ በሕወሓት ላይ ዛሬ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሰነዘረው ቢጡ ግን  እንዲመዘገብ ይሁን! ይህ በሕወሓት ላይ የተሰነዘረው ቡጢ መመዝገብ ያለበት የኦሕዴድ መኳንንት እየዘረጉት ያለውን የአፓርትያድ ሥርዓት  ሕዝቡ ወደ ቀልቡ ተመልሶ  አፍንጫው ማሽተት ሲጀምርና  ከትናንቱ የሚገማውን  የአፓርታይድ  አገዛዝ  መቃወም ሲጀምር ባለጊዜዎቹ  በሕወሓት  የተለመደ ዘይቤ  የሚነሳባቸውን ተቃውሞ  ማፈናቸው  ስለማይቀር ያኔ እንድናስታውሳቸው  ነው።
እነሆ ኦሕዴድ በሕወሓት ላይ የሰነዘረው ቡጢ፤
«ሕወሓት ኢትዮጵያዊ ማንነት የተገመደበትን ገመድ፣ የታሰረበትን ካስማ በመንቀል ሳይገታየተጋመደበትን ገመድ በፈጠራ ትርክት ለመበጣጠስ ያልፈነቀለው ድንጋይ ያልቧጠጠው አቀበት የለም። የትግራይን ሕዝብ ከቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመነጠል በፈጠራ ታሪክ፣ በአልባኒያ ሶሻሊዝምና በነሌሊንና ስታሊዝ አብዮታዊ ዲሞክራሲ፤ በማኪያቬሊያዊ የሥልጣን ቀመር ቀለም በመበጥበጥ ተርኳል። ላለፉት 27 ዓመታት ሀገሪቱ በነበረው ፍጹም አምባገነናዊ፣ ሙሰኛና ሴረኛ አገዛዝ ላይ ሕዝብ በአመጽ በተነሳ ቁጥር በትግራይ ሕዝብ ላይ የተነሳ ለማስመሰል በሒትለር የፕሮፓጋንዳ አስገድዶ የማጥመቅ ኅልዮት ለብቻው በተቆጣጠራቸው ሜዲያዎች ሲለፍፍ ኖሯል።»
[ምንጭ፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፥ አጀንዳ አምድ፥  ጥቅምት 7 ቀን 2012 ዓ.ም.]
 
መደመር በአማርኛ:-
«መደመር ማለት ትናንት ከኖርንበትና ዘመናት ከገፋንበት የእርስ በእርስ ሽኩቻ፣ ጥላቻ፣ ትንቅንቅ፣ መጠፋፋት፣ መወነጃጀል፣ የቂም በቀል ኋላቀር ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ በመውጣት፤  ሁሉንም የትናንትን መጥፎ ቅሪቶች በማራገፍና በመርሳት በአዲስ መንፈስ፣ ለአዲስ ሀገራዊ ግንባታ በሰላም፣ በፍቅር፣ በወንድማማችነት እጅ ለእጅ ተያይዘን በመነሳት ወደቀድሞው ገናናነት መወንጨፍ እንችል ዘንድ የሚያሸጋግረን መወጣጫ መሰላል ነው»
[ ዐቢይ አሕመድ ለኢትዮጵያ ሕዝብ  ከተናገረው ]
መደመር በኦሮምኛ፤
«መደመር የኦሮሞ ሕዝብ እሴቶችን [ገዳን መሆኑ ነው] ከኦሮሚያ አልፎ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ብሎም በአፍሪካ እንዲስፋፋ የሚያደርግ ፍልስፍና ነው»
[ ሽመልስ አብዲሳ  በነቀምቴ ከተማ እየተካሔደ ባለው የመደመር መጽሐፍ ምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ከተናገረው]
መደመር በቅጡ ያልተጤነ እንጭጭ ዝባዝንኬ ነው ያልነው ለዚህ ነው። የመለስ ዜናዊ አብዮታዊ ዲሞክራሲም እንደዚያ ነበር። ለዚያም ነው ሽግሽጉ ከመለሲዝም ወደ ዐቢይዝም ነው ያልነው።  ለዚያም ነው መደመር እና አብዮታዊ ዴሞክራሲ የማይለያዩት። ሁለቱም ወጥ ትርጉም የሌላቸው፣ ቃላትን የሚያባክኑ፣ ሕዝብን ግራ የሚያጋቡ ቅዠቶች ናቸው።
ዐቢይ እና ሽመልስ እርስ በርስ የሚምታታባቸውና የሚያምታቱት ለዚህ ነው። መለስ ዜናዊ  ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሲናገር  አብዮታዊ ዲሞክራሲ ይል ነበር፤ በትግርኛ ሲናገር ደግሞ  አብዮታዊ ዲሞክራሲ የትግራይ እሴት ለማስመሰል «ወያናይ ዲሞክራሲ» ይለው  ነበር። እነ ዐቢይና ሽመልስም  በአማርኛ መደመር እያሉ በኦሮምኛ ሲያወሩ ግን ገዳ፣ ሞጋሳ፣ ኦሮሙማ የሚሉት  በግብርም  በአስተሳሰብም የሱ ዲቃሎች ስለሆኑ ነው።
Filed in: Amharic