>
5:29 pm - Wednesday October 10, 2857

ግልፅ ደብዳቤ ለዶክተር ዓቢይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር (ታዬ ቦጋለ)

ግልፅ ደብዳቤ ለዶክተር ዓቢይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር
ታዬ ቦጋለ
 
የትላንቱ ቄሮ ለህዝብ ፍትህ ግንባሩን የሚሰጥ ሲሆን – የዛሬው ቄሮ ህዝብን ወግሮ በአሰቃቂ ሁኔታ የሚገድል ሆኖ ተከሰተ። የትላንቱ ቄሮ የሙስና ሠፈሮችን የሚፃረር – የዛሬው ቄሮ መሬት የሚወርር ሆነ። በጥቅሉ አደገኛው የሁለቱ ጣምራ ኃይሎች  ሀገር መበጥበጫ ‘ማሺን’ “ቄሮ” ተብዬው – ከትላንቱ ቄሮ ጋር ጠረኑ የማይመሳሰል አደገኛ አረመኔ ቡድን በቸልታ መታለፍ ጀመረ።
ክቡር ዶክተር ዓቢይ ሆይ፦
በመጋቢት ወር 2010 ማገባደጃ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ እጅግ አሰቃቂ ግፎችን ሲፈፅም የነበረውን የወያኔን መንግሥት – በመረረ የህዝብ ትግል ተክተው በትረ መንግሥቱን ሲቆጣጠሩ ከህፃን እስከ አዋቂ (ከሰይጣን መልዕክተኞች በስተቀር) ያልተደሰተ አለ ብዬ አልወስድም።
*
እርስዎ ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ ሀገርና የከበረ ህዝቧን ይመሩ ዘንድ –  ከፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ እና መምህር አሰፋ ማሩ ጀምሮ – ልጃቸው አስከሬን ላይ እንዲቀመጡ እስከተገደዱት የነቀምት እናት ድረስ ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል።
ቄሮ ፋኖ ኮንሶ ዘርማ እና አያሌ ወጣቶችና ዜጎች በስናይፐር በአደባባይ ህይወታቸው ተቀጥፏል፤ በየማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ታሪክ የማይዘነጋቸው በደሎች ተፈፅመዋል። (Bookworm እንደመሆንዎ ዝርዝሩን ‘መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ’ ከሚለው መፅሐፌ ማንበብዎን፤ ይልቁንም ከዚያ በላይ ርቀው እንደሚያውቁ ስለምገነዘብ ይጠፋዎታል ብዬ አልወስድም።)
*
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ ሆይ፦
ይህንን ትግል ወደላቀ ደረጃ በማሸጋገር ረገድ የቲም ለማና የቲም ገዱ ጥምረት ላይ – በህይወትዎ ተወራርደው ጭምር ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽዖ ታላቅ ግምት አለኝ።
ይልቁንም፦
“የፈሰሰው የኦሮሞ ደም የእኔም ነው!” በሚል መፈክር አንግበው ጀርባቸውን ሳይሆን ግንባራቸውን ለጥይት አረር ሰጥተው የወደቁት የባህርዳርና ጎንደር የአማራ ወጣቶች – የፍቅር መስዋዕትነት – ከቄሮ ፈጣን “ጣና የመተሳሰሪያ ገመዳችን ነው” ምላሽ ጀምሮ የአበው ወእመው ፍቅር እየተመለሰ ነበር።
(ይህ የዘመናት አብሮነት ተዘንግቶ – በአንድ አኖሌ ትርክትና የሁላችንም አያቶች ከዘመናት በመልካም ሰበዝና አለላ የተሰናኘ የፍቅር ጎጆ፤ የወየበ የመሰለው እየተጎለጎለ ለጠብ ምንጭ ሆነ። ጉዳዩ የመገፋት አለመገፋት ሳይሆን ከኋላ የሚዘውረው አደገኛ እጅ መሆኑን ተጠራጥሬ አላውቅም። አንድነትና መተሣሠር፦ “መርህ አልባ የጎንዮሽ ጉድኝት” ሲባልም ነበርንና እናውቃለን።)
*
ክቡር ሆይ፦
በምኒልክ ቤተመንግሥት ውስጥ ከተሰየሙ ጊዜ ጀምሮ ያበረከቷቸውን ታላላቅ ፍፃሜዎች በመዘርዘር አልቆይም። ዓለም ያደነቀው፤ ማንም ሊፍቀውና ሊሰርዘው የማይችል… የሚገባዎትን የኖቤል ሽልማት ጭምር ሊቀዳጁ እንደሆነ ሳውቅም ደስታዬን ደጋግሜ ገልጫለሁ። (እነ ፀጋዬ አራርሳ ‘በአንድ ስታተስ ከ70 – 700 ብር እየተከፈላቸው አንዳንድ አክቲቪስቶች በከንቱ ያደንቋቸዋል’ እስኪል ድረስ የማልፀፀትበትን ተገቢ ሙገሣ አዥጎድጉጃለሁ። በቤተ መንግሥትዎ የመጀመሪያው የእራት ግብዣ ከመሳተፌና ያለ አበል በፅህፈት ቤትዎ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሳተፍሁበት “የአዲስ ወግ” መርሐ ግብር በስተቀር ፀጋዬ በራሱ ደረጃ እንዳያስበን – ቆማጣን ቆማጣ ካላሉት አብሮ ይፈተፍታልና ነግሬው ልለፍ – ዱዲ ዲናር ወስደን አናውቅም።) ለህሊናችን በባዶ እግራችን እየኳተንን – የረባ ጃኬት ሳንቀይር በድህነት መኖሩ ክብራችን ነው።
*
በአጭሩ፦ ከሚያዝያ 2010 እስከ ዛሬዋ እለት የሠሯቸውንና ወደፊት ሊያመጧቸው ያቀዷቸውን ከብዛታቸው የተነሳ ለመቁጠር እስኪያዳግተኝ ድረስ አጀብ ብቻ አስብለው እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭኑ ተግባራትን አከናውነዋል።
*
ወደ ጉዳዬ ልለፍ፦
ይህ ልፋትዎ ሁሉ በህዝብ የልቡና ሠሌዳ የሚፃፈው ግን የመጀመሪያውንና ከሁሉም ቀዳሚውን የመንግሥትና የህዝብ የአብሮነት ቃልኪዳን ትሥሥር ውል (Contractual agreement) ሲተገብሩ ነው። ይኸውም የህግ የበላይነትን ማስከበር፤ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ፣ ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ ነው።)
ዶክተር ዓቢይ ሆይ፦ እርስዎ ኃላፊነትዎን ሲረከቡ ያጋጠመዎን ከባድ ፈተና ያለፉበት ጥበብ ይገርመኛል። ከቤተመንግሥት እስከ ደህንነት ፅህፈት ቤት የነበረውን የደህንነት መዋቅር መበጣጠስ፣ ሪፐብሊካን ጋርድ ማቋቋም፣ የኢኮኖሚ አሻጥሩን ደረጃ በደረጃ ፍርክስክሱን ማውጣት፣ የኮንትራባንድን ጉሮሮ ፈርጥቆ መያዝ፣ ወያኔ ምንም እንኳ ረጂም እጇ እስከ ቤተመንግሥት ድረስ የተዘረጋ ቢሆንም ከደደቢት እንድታንጯልቅ ማድረግ፣ በፍርድ ቤት፣ በምርጫ ቦርድ፣ በወሳኝ መዋቅሮች ያስመዘገቧቸው ድሎች፤ የማስታረቅ ሥራ፤ አርቆ በሚያስተውለው ህሊናዎ ምስራቅ አፍሪካዊ ትብብር… ታሪክን ማክበር፤ ኢትዮጵያን በከፍታዋ ልክ ማውሳት…
የቤተመንግሥቱን ከፊል ገፅታ ከኢትዮጵያ ጠብታ ሳንቲም ሳይወስዱ ከበርካታ የሥራ እድልና ገቢ ጋር “የአንድነት ፓርክ” ውለታ ቢስ አይደለሁምና ስዘረዝር ውዬ ላድር እችላለሁ።
*
በተቃራኒው ይህ ሁሉ የሚሠራው ለህዝብ ሆኖ ሳለ ህዝብዎ ሲገፋና ሲበደል በቸልታ ማየትዎ ከትዕግስት በላይ ሆነብኝ። ሻሸመኔ ቡራዩ ሐዋሳ ቀቤና ጌዴኦ ራያ ወልቃይት ጎጃም ወለጋ አለታ-ወንዶ ሁላ ይርጋለም… ወገን አረመኔያዊ ተግባር ተፈፀመበት።
ይበልጡኑ ዛሬ ቄሮ የሚባለውን የኦሮሞን ወጣት ስነልቡና የማይወክል መንጋ ያደራጀው ህቡዕ (ግን ደግሞ በግልፅ የሚታወቅ ኃይል) ለህዝብ ስጋት ብቻ ሳይሆን መልአከ ፅልመት ሆኖ በተንቀሳቃሽ ምስል ጭምር እየቀረፀ የሚለቅ – ከአሸባሪው አይሲስ (ISIL) ያልተናነሰ ኃይል ሆኖ ገንግኖ ወጣ።
የትላንቱ ቄሮ ለህዝብ ፍትህ ግንባሩን የሚሰጥ ሲሆን – የዛሬው ቄሮ ህዝብን ወግሮ በአሰቃቂ ሁኔታ የሚገድል ሆኖ ተከሰተ። የትላንቱ ቄሮ የሙስና ሠፈሮችን የሚፃረር – የዛሬው ቄሮ መሬት የሚወርር ሆነ።
በጥቅሉ አደገኛው የሁለቱ ጣምራ ኃይሎች  ሀገር መበጥበጫ ‘ማሺን’ “ቄሮ” ተብዬው – ከትላንቱ ቄሮ ጋር ጠረኑ የማይመሳሰል አደገኛ አረመኔ ቡድን በቸልታ መታለፍ ጀመረ።
*
የመንግሥት ዋነኛ ኃይል (Legitimate monopoly of overwhelming force) ከሌላው በተነፃፃሪ መልኩ የተሻለ ቁመና ያለው ኃይል በእጁ መያዙና የህዝብ ይሁንታው ነው።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የመጀመሪያው በእጅዎ ያለ ሲሆን፤ ቀጣዩ በየእለቱ ድጋፉን እየነፈገዎ መምጣቱን ዕያዩ – ወያኔ ብልጥ እንጂ ብልህ አልነበረቺምና የምንቆጥርላት ሳይኖር “እንደወደቀች” ሁሉ፤ የርስዎም መንግሥት በመደመር ያስመዘገባቸው ድሎች በመቀነስ እንዳያጣፋ ሰጋለሁ።
*
ብዙ ሊገነቡ የጣሩት ስብእና (Personality Cult) = በርግጥ መሆን ያለበት ያለማቋረጥ እየተሸረሸረ መሄድ አስጊ ሆኖብኛል። አይጠራጠሩ እየሆነ በዐይኔ በብረቱ እየታዘብኩ ነው።
*
መፍትሔዎች፦
1. የእንጀራ የጡት አበልጅ የቤትልጅ የለምና ሶማሊ አፋር ጋምቤላ… የሁሉም ወገን የተካተተበት “የኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲ ውህደት” እጅግ ይፋጠን።
2. የየክልሉ ፖሊስ “ህገመንግሥታዊ” ስለሆነ እንደተጠበቀ ሆኖ የየክልሉ ልዩ ኃይል – ህግ ስለማይከለክል – በአፋጣኝ ተሰባጥሮ ህብረብሔራዊ አደረጃጀት ይያዝ። አድማ በታኙ ፖሊስም ተመሳሳይ አደረጃጀት ይፈጠርለት። የየክልሉ ፖሊስ ቁጥር ከዓላማው አንፃር በምርመራና በውስን ህግ ማስከበር ሥራ ላይ እንዲሠማራ ይሁን።
3. በየከተሞች ከህዝብ የተውጣጣ ድሮ አብዮት ጥበቃ እንደሚባለው ሁሉንም ብሔረሰብ ያካተተ “የመደመር ጥበቃ” ኃይል ተቋቁሞ ከህዝብ ጋር እየመከረ – አካባቢውን ይጠብቅ፤ ህዝብ ይምከር!
4. በወያኔ/ ትህነግ ላይ ፅኑ አቋም ይያዝ
5. ኦነግ/ ሸኔ እና ዘዋሪዎቹ በህግ የሚዳኙበት ሁኔታ ይፈጠር
6. የምሁራን ዝግ የምክክር መድረክ ይዘጋጅ
7. የህዝብ አስተያየት በምሥጢር ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ይሰብሰብ…
*
8. በመጨረሻም ህግና ሥርአት ማስከበር ካልተቻለ ሀገር ወደ ባሰ ቀውስ ታመራለችና ቁልፍ አሠራር ይቀመጥ። ህዝብ የትላንቱን ቄሮ የደገፈው ለነፃነት ይታገል ስለነበረ ነው። የዛሬው በግልፅ ህግ እየጣሰ ነውና የትኛውም እርምጃ ቢወሰድበት በአራቱም ማዕዘናት ያለ ህዝብ ከጎንዎ ይቆማል። ህዝብ በአማናዊ ቀዬው እየተገደለ፣ መንገድ እየተዘጋ፣ ወሮበላነት እየገነነ… ዝምታው እስከመቼ? ለምን? ነገሮች ዕያየናቸው ከቁጥጥር ውጪ እየወጡ ነው።
*
ሀገር ፈርሳ ባትፈርስም፤ ደም መገበራችን አይቀርም። ሩዋንዳም እኮ አልፈረሰቺም በ100 ቀናት 80 እጁን ቱትሲ (800,000) አጣች እንጂ። ሊቢያ ሶርያ የመን /እኛም ያው ነን። “ሳይቃጠል በቅጠል” – እየተቻለ ለምን?!
*
ክቡርነትዎ ሳጠቃልል፦
ዝምታዎ ከቀጠለ እኛም ጭምጭምታውን ተቀብለን ኦነግ የመንግሥትን ይሁንታ እንዳገኘ አምነን…
የኦነግና ወያኔ ሰማንያቸው ላይቀደድ – እንደ ብሪታኒያው የ1930ዎቹ ማብቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኒቨሌ ቻምበርሊን ሂትለርን ለማብረድ የልምምጥ ፖሊሲ (Appeasement Policy) አያዋጣም። ይልቁኑ ተክቶት የተከሰተው የዊንስተን ቸርችል የመርህ ሰውነት እና ቆራጥ እርምጃ የበለጠ አዋጪ መሆኑን ልነግርዎ ወስኛለሁ።
*
እንደ አንድ 70,000 የፌስቡክ ተከታይ እንደሚያስተናግድ ግለሰብ ለሀገሬ ስል የመጨረሻዋን እምነቴን በርስዎ ድጋፍ ይዤ (Staunch supporter) – ሁኔታዎች ቀስ በቀስ ወደ ጠነከረ ተቃዋሚ (Ardent opponent) ሊገፉኝ እየታገሉ ነው።
*
እመኑኝ በመለማመጥ ፦
እርስዎ ቤተመንግሥት ሲያስመርቁ – አኖሌ ላይ ምኞታቸውን በምስል ያሳዩንን
እርስዎ የኖቤል ሽልማትዎን ስነስርአት ሲያካሂዱ – መንገድ የዘጉትን ልብ አያገኙትም።
ይልቅ የገዙትን የህዝብ ልብ መልሰው በሌቦች እንዳያጡት ተንበርክኬ እማፀንዎታለሁ።
*
የፈጠረኝ አንድ አምላክ ምስክሬ ነው። መምከር ችዬ ሳይሆን ሀገሬን መውደዴ አላስችል አላስተኛ አላስቆም አላስቀምጥ ብሎኝ ነው።
*
NB. ለማድነቅ የፈጠነ ልቡና የሌላቸው ታላቁ ልእለሰብእ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ጭምር ዛሬ በሀዘን መጎዳታቸው ለምን ይመስልዎታል?!
Filed in: Amharic