>
6:45 am - Tuesday July 5, 2022

ውስጣችን የቀረው "ህወሃታዊነት'  (በሙስጠፌ ዑመር)

ውስጣችን የቀረው “ህወሃታዊነት’ 
በሙስጠፌ ዑመር 
ለሀገራችን ፓለቲካ ዘላቂ ‘ ፈውስ’ የምንሻ ከሆነ አንድ ነገር ማድረግ ሳይኖርብን አይቀርም። ህወሃት የተሰኘውን ፓርቲ ረስተን ህወሃት ከተባለው ክስተት/ዘይቤ phenomenon ጋር ትግል ማድረግ ይኖርብን ይሆናል። ህወሃታዊው ዘይቤ/ ልማድ በቀላሉ ከኢትዮጵያ የፓለቲካ ባህል ውስጥ በቅርቡ የሚጠፋ አይመስልም። ይህ አስተሳሰብ እኛ ብዙም ትኩረት ያልሰጠነው ስፍራ እንደ አሜባ ተደብቋል – ያ ስፍራ እኛው መሀል ወይንም እኛው ውስጥ ነው ማለት ይቻላል። ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ በመሀከላችን የተዘራው የጥላቻ ፣ ቁጣ ፣ በቀል ፣ የመከፋፈል ሀሳብ በሁላችንም አዕምሮ እና ደም ውስጥ ዘልቆ ገብቷል። ሁላችንም ውስጥ ትንሹ ህወሃት ነግሷል ማለት ይቻላል ። በጭለማ ውስጥ የሚያደባው ይሄ ህሳቤ ክፉ ቀን ብቻ ነው የሚጠብቀው። ቀን ወደ እኛ ያጋደለ ሲመስለን ጠላት ያልናቸው ላይ የቁጣ በትራችንን እንሰነዝራለን።
ሁላችንም ” የእምነት የለሾችን መርሆዎች ” ( pagan ethos) የጭካኔና ጎሰኛ አመለካከቶችን ወይ ወርሰናል አልያም ጊዜ እንዳመጣው የመኖር ጥበብ ተቀብለን እየኖርን ነው። Robert Kalpan እንዳለው ገዢው ሎጂክ የእኔን ወይም የብሄሬን ጥቅም sectarian interests ካስጠበቀ ነውረኛም ተግባር ቢሆን ግዴለም ይሁን እያልን ይመስላል። Kalpan , Warrior Politics: Why Leadership Demands Pagan Ethos በተሰኘው ጽሁፉ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የአሜሪካ ኤምፔሪያሊዝም የአይዶዮሎጂ መሰረቶችን ለማግኘት ደፋ ቀና ብሏል። እነዚህ ” የኢ-አማኞች የሞራል መሰረቶች” ተብለው የተቀነቀኑት ራስ ወዳድ ህሳቤዎች በመሰረቱ የምዕራቡ አለም ሲሰብከን ከኖረው አለም አቀፍ ሰብአዊ ህሳቤዎች በእጅጉ ያፈነገጡ ናቸው።
ህወሃታዊው ” አውሬ ” ወደሚሄድበት ላይመለስ ሄዷል። ነገር ግን ትቶልን የሄደው ራሱን እየበላ ያለ የጸጥታ መዋቅርና የብሄር መሪ ነን ባዮችን ethnic oligarchs እዚሁ ከእኛው ጋር አሉ ። ይህ ሀይል ደግሞ በውስጡ ያለውን እርስ በእርሱ የሚጋጭ የአስተሳሰብና አደረጃጀት ችግር አስታርቆ እንኳን ሀገርን ወደፊት ሊያስኬድ የራሱንም ህልውና ማስጠበቅ የሚችል አይደለም። ከፊታችን ያለው ሁለት አማራጭ ብቻ ነው። ወይም ዲሞክራሲያዊ ስርአትን እንከተላለን አልያም የለየለት ወታደራዊ አገዛዝ ስር እንወድቃለን።
እስካሁን የደለበውን ዘንዶ እናስወግደው ዘንድ ምናልባትም ከእርሱ የበለጠ አውሬ ያስፈልገናል እንል ይሆናል። ከዚያ የተሻለው አማራጭ በ”ህወሃታዊውን አስተሳሰብ ” የወረስናቸውን ውስጣችን ያሉትን ትናንሽ ‘ሰይጣናዊ’ አስተሳሰቦችንና ልማዶችን በታሰበበት እና ተከታታይነት ባለው መልኩ ከውስጣችን ልናነጻ ያስፈልገናል። ያ ባልሆነበት ሁኔታ በማያባሩ ” ህወሃታዊ ‘ ሂደቶች ሽክርክሪት ውስጥ መቀጠላችን አይቀርም። ህወሃት ‘ሄደ’ ብንልም የፓለቲካ ስልጣኑን በኖርንበት ልማድ የሚመሩ የተለያዩ ግለሰቦች ፣ ሰብዕናዎች ወይም የብሄር ድርጅቶች ይመጡበት ይሆናል ። ነገር ግን ያንኑ ‘ ህወሃታዊ ‘ መንገድ ነው የሚከተሉት። ስለሆነም በዚህ ወቅት ቁምነገራችን መሆን ያለበት የሄድንበትን መንገድ ማውገዙ ላይ ሳይሆን እርሱ እውስጣችን ጥሎት የሄደውን የአስተሳሰብ ሰንኮፍ መንቀል ላይ ነው። ያንን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው ከግጭትና ጥላቻ እሽክርክሪት መውጣት የምንችለው።
Filed in: Amharic