>

የዘር ፖለቲካን አቀንቃኞቹ አገር አፍራሾች  ሊነግሩን የማይፈልጉት የቅድመ 1966 ዓ.ም. ኢትዮጵያ እውነት!!!  (አቻምየለህ ታምሩ)

የዘር ፖለቲካን አቀንቃኞቹ አገር አፍራሾች  ሊነግሩን የማይፈልጉት የቅድመ 1966 ዓ.ም. ኢትዮጵያ እውነት!!! 
አቻምየለህ ታምሩ
ያ ትውልድ የዘመተባት ያባቶቻችን ኢትዮጵያ ከምትከሰስባቸው የኃጢአት ክሶች መካከል «ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋ እውቅና አልሰጠችም፣ ቋንቋቸው እንዳይነገር አድርጋለች፣ ጨፍልቃለች፣ አጥፍታለች፣ ጨቁናለች» ወ.ዘ.ተ የሚለው ትምህርቱን በቅጡ ያልጨረሰው የዋለልኝ መኮንን የድንቁርና አስተምህሮ ዋናው ነው!!!
ከታች የታተመው በሚኒስትሩ በጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ ይመራ የነበረው የሕዝባዊ ኑሮ እድገት ሚኒስቴር በ1948 ዓ.ም. በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የጥናት መጽሔት ላይ ያሳተመው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ዝርዝር እንደሚያሳየው በወቅቱ ማለትም በ1948 ዓ.ም. በኢትዮጵያ 80 ቋንቋዎች ይነገሩ እንደነበር ከነ ቋንቋዎቹ ስም ዘርዝሯል።[ከታች የታተሙትን ዶሴዎች ይመለከቷል]
የኢትዮጵያ መንግሥት በ1948 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የሚነገሩ 80 ቋንቋዎችን ዘርዝሮ ነው እንግዲህ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሀገር በቀል ወኪሎቹ እነ ዋለልኝ መኮንን ኢትዮጵያን «የብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦችን ቋንቋ እውቅና ያልሰጠች፣ ቋንቋቸውን እንዳይነገር ያደረገች፣ የጨፈለቀች፣ ያጠፋች፣ የጨቆነች አድርገው ‹የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እስር ቤት› ያደረጓት።
የሕዝባዊ ኑሮ እድገት ሚኒስቴር በ1948 ዓ.ም. «ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚነገሩት ቋንቋዎች ቁጥር ለጊዜው የታወቁትን ሰማንያ አንድ ስለኾኑ ዝርዝራቸው እንደሚከተለው ነው» በሚል ያዘጋጀው የጥናት መጽሔት ከታተመ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ በ1957 ዓ.ም. የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲቋቋም የድርጅቱ መሥራች ሀገራትን ዋና ዋና ነገሮች «የአፍሪካ አልማናክ» ተብሎ የተሰየመ መጽሐፍ ታትሞ ነበር። መጽሐፉ እያንዳንዱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባል ሀገሩን ለዓለም የሚያስታውቅበት መዝገብ ነበር።
በዚህ «የአፍሪካ አልማናክ» ተብሎ በተሰየመው በፈረንሳይኛ፣ በእንግሊዚኛ፣ በዐረብኛና በአማርኛ ቋንቋዎች በተዘጋጀው ባለ 169 ገጽ መጽሐፍ ውስጥ በመጀመሪያ ገጽ ላይ ኢትዮጵያ ለዓለም የተዋወቀችው በዚህ መልኩ ነበር፡-
_______________________________________________________________
ኢትዮጵያ
 ፩. ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፡- ከሦስት ሺሕ ዓመት በላይ ነጻነትዋን ጠብቃ የኖረችውና በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ የምትገኘው ኢትዮጵያ በሰሜን ከሱዳን ሬፑብሊክና ከቀይ ባሕር፣ በምሥራቅ ከፈረንሳይ ሱማሌና ከሱማሌ ሬፑብሊክ፣ በደቡብ ከሱማሌ ሬፑብሊክና ከኬንያ በምዕራብ ከሱዳን ሬፑብሊክ ጋር ትዋሰናለች፡፡
 ፪. ስፋት፡- 450,000 ስኩዌር ማይልስ
 ፫. የሕዝብ ብዛት፡- 20,000,000
 ፬. ዋና ከተማ፡- አዲስ አበባ ሌሎች ከተሞች፡ አሥመራ፣ ምጽዋ፣ አሰብ፣ ሐረር፡ ድሬደዋ፣ ጂማ፣ ጋምቤላ፣ ጐንደርና የቀሩትም፡፡
 ፭. ቋንቋ፡- ኦፊሲዬል አማርኛ ሌሎች ጋልኛ ትግሪኛ ሱማልኛና የቀሩትም፡፡
 ፮. የመንግሥቱ አስተዳደር፡  ንጉሠ ነገሥታዊ መንግሥት ሆኖ የሕግ መወሰኛና የሕግ መምሪያ የሚገኝበት በሕገ መንግሥት የተመሠረተ ምክር ቤት አለ፡፡ የሕግ መምሪያው አባሎች ወይም የሕዝብ እንደራሴዎች በጠቅላላ ምርጫ ለአራት ዓመት ጊዜዎች ይመረጣሉ፡፡ ከአገልግሎት ዘመናቸው በኋላም እንደ ገና ለመመረጥ በዕጩነት ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ የእነዚህም የሕዝብ እንደራሴዎች ቁጥር አሁን ፪፻፲ ነው፡፡
የሕግ መወሰኛው አባሎች ደግሞ በንጉሠ ነገሥቱ ይሾማሉ፡፡ የሕግ መወሰኛው አባሎች ቁጥር ከሕዝብ እንደራሴዎቹ ቁጥር ከግማሹ መብለጥ የለበትም፡፡ ማናቸውም ሕግ የሚፀናው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ተስማምቶበት ንጉሠ ነገሥቱ ሲያጸድቁት ነው፡፡
 ፯. መሪ፡- ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፡፡
በዓለም ታሪክ ከተመዘገቡት ሁሉ በጣም ብዙ ዘመን ከኖረውና በንጉሣዊ የዘር መሥመሩም እጅግ ከረዘመው ዘርፍ ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣው ንጉሣዊ ቤተሰብ የሚወለዱት ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በጥቅምት ፳፫ ቀን ፲፱፻፳፫ ዓ.ም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንገሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው ነገሡ፡፡
 በሐምሌ ፲፮ ቀን ፲፰፻፹፬ ዓ.ም በሐረር ኤጄርሣ ጐሮ የተወለዱት ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ከንጉሥ ሰሎሞንና ከንግሥተ ሳባ ሲወርድ ሲዋረድ ተያይዞ የመጣው የሣህለ ሥላሴ ንጉሠ ሸዋ የልጅ ልጅ ናቸው፡፡ የዳግማዊ ምኒልክ ታማኝ ዲፕሎማትና (የፖለቲካ ዐዋቂ) ጀግንነት የተመላባቸው የነበሩት አባታቸው ልዑል ራስ መኰንን በታላቁ የዐድዋ ጦርነት ላይ ባ፲፰፻፹፷ ዓ.ም ትልቅ ጀብዱ የሠሩ ስመ ጥሩ ጀግና ናቸው፡፡
 ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርታቸውን በሚገባ አከናውነው ከጨረሱ በኋላ ገና ከወጣትነታቸው ጊዜ ጀምረው የሀገሪቱ መሪ እስከ ሆኑበት ጊዜ ድረስ በልዩ ልዩ ከፍተኛ የአስተዳደር ሥልጣን ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ ግርማዊ ንገሠ ነገሥት በ፲፱፻፲፮ ዓ.ም ሀገራቸው የዓለም መንግሥታት ማኅበር አባል ትሆን ዘንድ ሊመሩዋት ቻሉ፡፡
 በጥቅምት ፳፫ ቀን ፲፱፻፳፫ ዓ.ም ነግሠው ከሰባት ወር ጊዜ የሆነውን ሕገ መንግሥትና የሕግ ምክር ቤት ለሕዝባቸው በገዛ ፈቃዳቸው ምክር በመስጠታቸው ራሳቸውን በሕገ መንግሥት የተመሠረተ ንጉሥ አደረጉ፡፡
 በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም የኢጣሊያ ፋሺስቶች ኢትዮጵያን በወረሩ ጊዜ በሰኔ ወር ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጄኔሻ ላይ በዓለም መንግሥታት ማኅበር ፊት ስለ ሀገራቸው መወረርና ወደዚያውም ስለ ኢንተርናሽናል የሞራል ሁኔታ አቤቱታቸውን አሰሙ፡፡ ምንም እንኳ የዓለም ማኅበር ለዚህ ታሪካዊ ንግግራቸው የዝኆን ጆሮ ይስጠኝ ብሎ ዝም ቢልም ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያላቸውን ፍጹም የሆነ እምነት ትግላቸው የተነሣ የነጻነት ቀን የሆነው ሚያዝያ ፳፯ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም በመምጣቱ ፋሺስት ሀገሪቱን ከወረረበት ያምስት ዓመት ጊዜ በኋላ ጀግኖች የሆኑትን አርበኞቻቸውን እየመሩ በእንግሊዝ የጦር ወታደሮች እርዳታ በታላቅ ድል አድራጊነት ከንጉሠ ነገሥት ግዛታቸው ዋና መናገሻ ከተማ ተመልሰው ገቡ፡፡
 ከነጻነት በኋላም በሀገር ውስጥና በውጭ ጉዳዮች ሁሉ የአዲሲቱ ኢትዮጵያ መሥራችና ሠሪ መሆናቸውን ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በተግባር አሳይተዋል፡፡ ወደ ሀገራቸውም እንደ ተመለሱ ሀገሪቱ በጦርነት ተሠቃይታና ፈራርሳ በማግኘታቸው ወዲያውኑ ለሀገሪቱ ሕይወትን ለመመለስ ብለው ሰፊና አድካሚ በሆነ የሥራ ዐቅድ (ፕሮግራም) ላይ ራሳቸውን አዋሉ፡፡ ከዚህም የተነሣ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን ከፈቱ፣ ዘመናዊ ሆስፒታሎችን አቋቋሙ፣ አዳዲስ መንገዶችን ሠሩ፣ ብዙ የመገናኛ ሁኔታዎችንም አሻሻሉ፣ የነገሡበትን ፳፭ኛውን በዓል ሲያከብሩ በብር ኢዮቤልዩዋቸው ዕለት በጥቅምት ፳፫ ቀን ፲፱፻፵፷ ዓ.ም ራሳቸው በፈቃዳቸው አዲስ የተሻሻለውን ሕገ መንግሥት ውስጥ ለሀገሪቱ ጠቅላላ የሕዝብ ምርጫ የጋዜጣና የንግግር ነጻነት መስጠታቸው ተመልክቷል፡፡
 የተባበሩት መንግሥታት አጥብቆ ደጋፊ በመሆናቸው ግርማዋ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በአደስ አበባ የተባበሩትን መንግሥታት የአፍሪካ ኤኮኖሚክ ኰሚሽን በመረቁበት ዕለት ባደረጉት ንግግር የዓለም ሕዝቦች ግርማዊነታቸወ ስለ ሁለት መሠረተ ሀሳቦች መጠበቅ ጉዳይ ራሳቸውን ያዋሉ ሰው ናቸው፡፡ እነርሱም “ኰለክቲቭ ሴኪዩሪቴና ለተጨቆኑ ሕዝቦች ነጻነት እንዲሰጥ” የተባሉት ናቸው፡፡
 የአፍሪካን ናሽናሊዝም (ሀገርን የማፍቀር ስሜት) በብርቱ የሚደግፉት ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በቤተ መንግሥታቸው ብዙ የአፍሪካ ናሽናሊስቶችን በየጊዜው እየተቀበሉ ያስተናግዳሉ ሀገራቸው በፋሽስት በተወረረች ጊዜ ከውጭ እርዳታን ለመጠየቅ በስደት ሄደው ከነበሩበት ከእንግሊዝ ሀገር በ፲፱፴፫ ዓ.ም ከተመለሱበት ጊዜ ጀምሮ ስለ አፍሪካ ክፍለ ዓለም ነጻነት ራሳቸውን በተጋድሎ ላይ አዋሉ ጥቅምት ፳፫ ቀን ፲፱፻፶፩ ዓ.ም ስለ አፍሪካ ነጻነት በመጥቀስ ቀጥሎ ያለውን ተናገሩ፡፡ “የነጻዪቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቻዋን መገኘት ለአፍሪካ የነጻነት በር ይከፍታል ብለው ያምኑ የነበሩት አፍሪካውያን ሁሉ በዚህ እምነታቸው እንዳልተሳሳቱ ጊዜ መሰከረላቸው፡፡ ዛሬ የአፍሪካ ነጻ መንግሥታት ቁጥር በታላቅ እርምጃ እያደገ ይሄዳል፡፡ ይህንንም የእርምጃ ፍጥነት የሚያግድ ምንም ኀይል በምድር ሊኖር አይችልም፡፡”
 ፰. የኤኮኖሚ ልማት፡- ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የእርሻ ሀገር እንደ መሆኗ መጠን በንግድና በኢንዱስትሪም ደኅና እርምጃ በማሳየት ላይ ነች፡፡ ከሀገሪቷም አብዛኛው ክፍል ለምለም ስለሆነ በብዙ ቦታ ባመት ሁለት ጊዜ ሰብል ይገኛል፡፡ በዚህም አኳኋን ከመሬቶቿ በብዛት የሚገኙት ቀጥሎ ያሉት ናቸው የባሕር ማሽላ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ዘንጋዳ፣ ጥጥ፣ የሸንኰራ አገዳ፣ ጤፍ፣ የቃጫ ተክሎች አታክልትና ቡና፡፡
 በኢንድስትሪም ረገድ በሀገሩ ውስጥ የሚያስፈልጓትን ነገሮች ራሷ ለመሥራት ብዙ ትንሽ ኢንዱስትሪዎችን አቋቁማለች፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው ነገሮች ቡና፣ ቆዳ፣ እህል፣ የቅባት እህሎች፣ ሥጋ፣ ወርቅና ፕላቲንዩም ሲሆኑ ከውጭ ሀገር የምታስመጣቸው ነገሮች ደግሞ ብረታ ብረት፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ ተሽከርካሪ መኪናዎች፣ የእርሻ መሣሪያዎች መድኀኒትና ከቤንዚን ዘይት የሚገኙ ነገሮች ናቸው፡፡
 ፱. ገንዘብ፡- የኢትዮጵያ ብር፡፡
 ፲. ሃይማኖት፡-  ክርስትያን፣ እስላምና አረመኔ፡፡
 ፲፩. መከላከያ፡- ኢትዮጵያ የጦር ኀይሎችዋን በሦስት ክፍል እንደ ገና በደንብ አደራጅታለች፡፡ እነዚህም የምድር ጦር ኀይል፣ የአየር ኀይልና የባሕር ኀይል ናቸው፡፡ የምድር ጦሩ የጦር ሠራዊትንና የክብር ዘበኛን ሠራዊት የያዘ ሲሆን የአየር ኀይሉ ደግሞ ዘመናዊ ጄት የሆኑ ተዋጊና ቦምብ ጣይ አይሮፕላኖች የሚገኙበት ነው፡፡ የባሕር ኃይሉ ደግሞ ምንም እንኳ የተመሠረተው በቅርቡ ቢሆንም ታላቅ እርምጃን በማሳየት ላይ ነው፡፡ በነዚህም ላይ በተጨማሪ የብሔራዊው ጦር በደንብ በመደራጀት ላይ ነው፡፡ የነዚህን ጦር ኃይሎች የመከላከያ ሁኔታ የሚቆጣጠረው የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ያገር መከላከያ ሚኒስቴር ነው፡፡ ስለ ሀገሪቱ መከላከያ መስፋፋት የሚችልበት ሁሉ ተጠንቶ ይሠራበታል፡፡
_______________________________________________________________
ተራ ቁጥር አምስት(፭) ላይ ሰፍሮ እንደሚታየው ቋንቋን በሚመለከት ኢትዮጵያ ለዓለም የተዋወቀችው ኦፊሲያላዊውን ቋንቋ አማርኛ ጨምሮ ጋልኛ፣ ትግሪኛ፣ ሱማልኛና ሌሎችንም ቋንቋዎች የምትናገር ሀገር ተደርጋ ነው። ሃይማኖትን በሚመለከትም የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ኾነው ለዓለም የተዋወቁት ክርስትና፣ እስልምናና አረመኔ (paganism) እንደኾኑ በግልጽ ይታያል። አፍ ነጠቆቹ እነ ዋለልኝና ደቂቆቻቸው ግን ኢትዮጵያ ለዓለም ስትተዋወቅ የኖረችው አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባሕል፣ አንድ ሃይማኖት፣ ወ.ዘ.ተ እያሉ ሲያላዝኑብን አርባ አምስት ዓመት ኾናቸው።
ሌላው አስገራሚ ነገር ኢትዮጵያ በዚህ መልክ ለዓለም የተዋወቅችበትን መግለጫ ለአፍሪካ አልማናክ መጽሐፍ ዝግጅት ክፍል የሰጠው የመንግሥት መስሪያ ቤት «የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ልዩ ካቢኔ» እንደኾነ መጠቀሱ ነው። እነ ዋለልኝ ኢትዮጵያን የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እስር ቤት አደረጋት ብለው የኃጢአት ክስ ካወረዱበት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መስሪያ ቤት ክፍል ውስጥ የንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ካቢኔ ቀዳሚው ነው። ዶሴው ሲገለጥ ግን የምናገኘው እውነት ኢትዮጵያን ብዙ ቋንቋዎች የምትናገርና የብዙ ሃይማኖቶች ሀገር እንደኾነች አድርጎ ለዓለም ያስተዋወቀው የንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ካቢኔ ነበር። በ1957 በእንግሊዚኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በዐረብኛና በአማርኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀው የአፍሪካ አልማናክ መጽሐፍ በመጀመሪያ ገጽ ሀተታው ይህንን እውነት መዝግቦታል!
በ1957 ዓ.ም. የንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ካቢኔ ኢትዮጵያ በዚህ መልኩ ያስታወቀበት የአፍሪካ አልማናክ መጽሐፍ በዓለም ከመሰራጨቱ ከአንድ ዓመት በፊት በ1956 ዓ.ም. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ15 የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እስከ 1966 ዓ.ም. ሲሰጥ የቆየውን  የብሔራዊ የፊደል ሠራዊት መርሐ ግብር ጀምሮ ነበር። በዚህ መርሐ ግብር በማስተማሪያ ቋንቋነት ከዋሉት 15 የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መካከል ኦሮምኛ አንዱ ሲኾን በቋንቋው የተዘጋጀ መጽሐፍ ባለመኖሩ ለማስተማሪያ መጽሐፍነት ጥቅም ላይ የዋለው መጽሐፍ፣ መንፈሳዊው መጽሐፈ ቁልቁሉ እንደነበር የመርሐ ግብሩ አስተባባሪ የነበሩት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ ስለ መርሐ ግብሩ ታሪክ በጻፉት ማስታወሻ አውስተዋል። ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ ራሳቸው በነጉሡ ዘመን በ1956 ዓ.ም. በብሔራዊ የፊደል ሠራዊት ፕሮግራሙ የታቀፉ ተማሪዎችን ወለጋ ውስጥ በኦሮምኛ በሚያስተምሩበት ወቅት ዋቢ አድርገው ይጠቀሙበት የነበረው የኦሮምኛ ጽሑፍ መጽሐፈ ቁልቁሉ እንደኾነ ጠቅሰዋል። ስለብሔራዊ የፊደል ሠራዊት መርሐ ግብር የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት በ1956 ዓ.ም. «ብሔራዊ የፊደል ሠራዊት ማኅበር» በሚል የታተመውን  ባለ 22 ገጽ መመሪያ ያነቧል።
እነ ዋለልኝ ዩኒቨርሲቲ ሳይገቡ ኢትዮጵያ የዘመኗን ቻሌንጅ ለማሸነፍ በትምህርት ረገድ ይህንን ሁሉ ጥረት ብታደርግም እነሱ ግን ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ የበለጠ በመደንቆር ታላላቆቹ ወደፊት እያዩ ከዐረብ፣ ከምሥራቅና ከምዕራብ ዓለም ኃያላን ጋር እየተፋለሙ የገነቧትን ሐገር የጠላቶቿን ትርክት የራሳቸው በማድረግ ወደኋላ እያዩ አፈረሷት።
Filed in: Amharic