>

ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመወርቅ የጥፋተኛነት ውሳኔ ተላለፈበት! ጉዳዩንም እስር ቤት ሆኖ እንዲከታተል ታዟል!

ጋዜጠኛ ፍቃዱ የጥፋተኛነት ውሳኔ ተላለፈበት! ጉዳዩንም እስር ቤት ሆኖ እንዲከታተል ታዟል!!!
 ግዮን መጽሄት
* በየ አስራ አምስት ቀኑ ገበያ ላይ ትውል የነበረችው “ግዮን መጽሔት”ም ህትመቷ ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጡንም ከቅርብ ምንጮች የገኘነው መረጃ ይጠቁማል!
ጋዜጠኛው ፍቃዱ በዛሬው ዕለት (ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም) ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፡ ስምንተኛ ወንጀል ችሎት ተፈርዶበት መታሰሩ ታውቋል። ጋዜጠኛው ጥፋተኛ  ነው ሲል ፍርድ ቤቱ የበየነበት በመሆኑ፣ በመጭው ማክሰኞ ይግባኝ እስኪል ድረስ እስር ቤት ውስጥ እንዲቆይ ተወስኖበታል።
የግዮን መጽሔት ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመወርቅ ሕወሓት ነጻ ፕሬሱን ለማሸማቀቅ ከአምስት ዓመታት በፊት በዕንቁ መጽሔት በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት ይሰራ በነበረበት ጊዜ  በተመሰረተበት ክስ ዛሬ ጥፋተኛ ተብሎ ታሰረ።
ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመወርቅ ሰሞኑን ሕወሓት ስልጣን ላይ ሳለ የተመሰረተበት ነጻ ፕሬሱን ለማፈን የተደረገ ክስ የለውጥ ሀይል የሚባለው ስልጣን ላይ ከወጣ በሁዋላ እንደ ሌሎቹ ክሱ እንዲሰረዝ ጠይቆ እንዳልተሳካለት ይህንንም ለፍትህ የሚታገሉ ወገኖቹ ሁሉ እንዲያውቁ የፍትህ ያለህ ሲል በኢትዮጲስ ጋዜጣ  ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመወርቅ በነጻ ፕሬስ ውስጥ  ከሃያ ዓመት በላይ የተለያዩ ጋዜጦችን በማሳተምና በማኔጂንግ ኤዲተርነት ያገለገለ ሲሆን በቅርቡም ግዮን መጽሔትን በተመሳሳይ ሀላፊነት ሙያዊ አድተዋጽዎውን እያደረገ ነበር።
ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመወርቅ በሙያው ሳቢያ በየጊዜው የተለያዩ ጫናዎችን ሲያስተናግድ የቆየ ሲሆን ትላንት ቃሌ ብሎ ባወጣው ጽሁፍ የለውጥ ሀይሉ በወያኔ የፈጠራ የአሸባሪነት ክስ በእስር ላይ የነበሩትን ሁሉ ሲፈታ የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ላይ በጊዜው የተከፈተውን ክስ ባለበት እንዲቀጥል ማድረጉ በለውጡ ላይ ጥርጣሬ የሚጋርጥ መሆኑን ገልጾ በእሱም ላይ የተመሰረተው የነጻ ፕሬስ የሕትመት ውጤቶችን ወይ በግብር ወይ በሽብር ክስ ለማጥፋት በተደረገው ጥረት ተመስርቶ የቆየ መሆኑን አስታውሶ ዛሬ ለውሳኔ መቀጠሩን ገልጾ እውነታውን ሕዝብ እንዲያውቀው ክሱ በ2006 ዓም የተመሰረተበትን ሂደት እና በዚያ ሳቢያ ለስደት እና ለእንግልት የተዳረጉ ጋዜጠኞችን ጉዳይ ጭምር በዋቢነት  ጠቅሶ አስታውቆ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጋዜጠኛው እስር ሳቢያ በየሳምንቱ የምትታተመው ግዮን መጽሔት ለህትመት እንደማትበቃ ለማወቅ ተችሏል።
Filed in: Amharic