>

በስልጣን ጥም አይናቸው በተጋረደ ግለሰቦችና ፈረሶቻቸው  ዜጎች እየተዳጡ በወጡበት እየቀሩ ነው!!! (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)

በስልጣን ጥም አይናቸው በተጋረደ ግለሰቦችና ፈረሶቻቸው  ዜጎች እየተዳጡ በወጡበት እየቀሩ ነው!!!
ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ
.
የፖለቲካ ፈረስ ጋላቢዎች ወደ ስልጣን የሚጋልቡበት መስመር ላይ አልተግባቡም፡፡ አይንና ቀልባቸው መድረሻ ያሉት ላይ ነው፡፡ መድረሻ ስልጣን ላይ አይንና ቀልባቸውን ተክለው ይሸመጣጣሉ፤ የትኛው መንገድ ካሰቡበት ሊያደርሳቸው እንደሚችል፣ የትኛው ገደል እንደሚጨምራቸው አያስተውሉም፤ መድረሻ ግባቸው እንጂ መገስገሻ መንገዳቸው አያስጨንቃቸውም፡፡ ይኸው አንድ አመት! እርስ በርስ ሲላተሙ፣ ከየጉድባው ሲወታተፉ ከተነሱበት ነጥብ ፈቀቅ ሳይሉ አሉ፡፡ ቋንቋቸውም ያው እንደ መጋለቢያ መስመራቸው ለየቅል ነው፤ የጋራ አንደበት የላቸውም፡፡ ዛሬ ለሰላሙ ሱባኤ የገቡለትን፣ ዱአ የዋሉለትን ወዳጅ ጀንበር ሳትጠልቅ መርፌ ሰክተው ይመግኑታል፤ እጣን አጢሰው ያሳቅሉታል፡፡ ትላንት ጠላት ብለው ጦር ከሰበቁበት ዛሬ ወዳጅ ሆነው እሼሼ ገዳሜ ይላሉ፤ ለጥፋት ይሰለፋሉ፡፡
.
የራስን ባንዲራ ታቅፎ – የሌላውን ባንዲራ አንጥፎ ለመቀጠል ካሰብን ጥላቻ የሚዘመርበት እንጂ፣ ቄጠማ የምጎዘጉዝበት መስከረም ዳግም ሊጠባ አይችልም፡፡ ከደጃፋችን የነቀልነውን የአንባገነንነትና የጭቆና መዝጊያ ሌላው በር ላይ ለመግጠም ከፈለግን ምንግዜም ነጻ አንወጣም፡፡ በመሆኑን፣ የጠቅላይ ሚንስትራችን ትልቁ የዚህ አመት ተግባር ለነዚህ የፖለቲካ ጋላቢዎች እርስ በርስ የማያላትም ቅቡል መስመር፣ ተነጋግረው የሚግባቡበት የጋራ ቋንቋ መፍጠር ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን እነዚህ ሀይሎች በስልጣን ጥም አይናቸው በተጋረደ ፈረሶቻቸው እየተዳጡ ዜጎች በወጡበት እየቀሩ፤ በተናገሩት ሰላማቸው እየደፈረሰ፣ ፈረሰኞቹ ቢፈቅዱት እንኳን፣ መሪ እንደመሪ – ህዝብ እንደህዝብ- አገርም እንደ ሀገር ሊቀጥል ሊቀጥል አይችልም፡፡
Filed in: Amharic